ከዓመት በፊት ነበር ወይዘሮ ሙሉእመቤት አለሙ (ስማቸው የተቀየረው) የባላቸው የኖረ ጸባይ እየተቀያየረባቸው ሲመጣ ባላቸውን በስውር ወደ መከታተሉ የገቡት። ከወራት በኋላም የልባቸው ትርታ የነገራቸው ሁሉ እውን ሆኖ ያገኙታል፡፡ እናም ከባላቸው ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ ሲመጣ ወግ ማዕረግ አይተው ልጅ ወልደው ያቀኑት ትዳር ይናጋና የቤተሰባቸው ህልውናም አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ይገነዘባሉ። ወይዘሮ እመቤት ነገሩን እያብሰለሰሉ ውለው ካደሩ በኋላ ችግሩ የባሰ ከመበላሸቱ በፊት መፍትሄ ባገኝ ብለው ለጉዳዩ መፍትሄ ይሰጡኛል ወዳሉት የቤተሰብ ጉዳዮች አማካሪ ያቀናሉ፤ ለባለሙያውም የሆዳቸውን ያጫውቷቸዋል።
ባለሙያውም ባለቤታቸውን አቶ ገረመው ይስሀቅን (ስማቸው የተቀየረ) ጥሪ ያደርጉላቸውና ጊዜ ወስደው ይነጋገራሉ። በውይይቱም አቶ ጌታቸው የሆነው ነገር ሁሉ ጥፋት እንደሆነ በማመን የትዳር አጋራቸውን ይቅርታ ለመጠየቅ ይስማማሉ። በስምምነቱም መሰረት ለወይዘሮ ሙሉእመቤት የተፈጠረውን ነገር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይናዘዛሉ። የወይዘሮ ሙሉእመቤት ጥያቄ ግን አንድ ብቻ ነበር «ያለፈው አልፏል፤ ከዚህ በኋላ ግን እንዳይደገም» ሲሉ ቃል ያስገባሉ። ለመፍረስ ዳር ደርሶ የነበረው ቤተሰብ ቀና ይልና ለመበተን ቀናትን ይጥብቁ የነበሩትም ልጆች ወደቀደመ የእናት አባት እቅፍ ፍቅራቸው ይመለሳሉ። ይንን ታሪክ ያጫወቱን የቤተሰብ ጉዳዮች አማካሪ ባለሙያ የሆኑትና የጋብቻና የቤተሰብ አማካሪ በመሆን ላለፉት ሃያ ዓመታት የሰሩት፤በጠቅላይ ፍርድ ቤት የቤተሰብ ጉዳይ አስማሚ የሆኑት፤ በዚሁ ጉዳይ ላይም የሚመክር የሬድዮ ፕሮግራም ባለቤት አቶ ይመስገን ሞላ ናቸው።
የቤተሰብ ጉዳይ ዘወትር እየኖርንበት ትኩረት የማን ሰጠው ጉዳይ ነው የሚሉት ባለሙያው ዛሬ ዛሬ የትዳር መፍረስ ዜና ከየጓዳው እንደቀልድ ይሰማል ይላሉ። “እከሌና እከሊት ተለያዩ፤ ፍቺ ፈጸሙ ስንባል በመደነቅና በመገረም የምንሰማበት ጊዜ አይደለም። በቤተሰብ ውስጥ አለመስማማትና ግጭት መፈጠሩ የተለመደ ነው፤ ነገር ግን ችግሩ በወቅቱ ካልተቋጨ መዘዙ ብዙ ነው። በጋብቻ መፍረስና በቤተሰብ መለያየት ደግሞ ቀዳሚ ተጎጂ የሚሆኑት ልጆች ከልጆችም ለአቅመ አዳምና ሄዋን ያልደረሱት ናቸው። የቤተሰብ መፍረስ ደግሞ ለማህበረሰብ ብሎም ለሀገር የሚተርፍ ተጽእኖ ይፈጥራል” ይላሉ ባለሙያው አቶ ይመስገን ሞላ፡፡ ለትዳር መፍረስና ለቤተሰብ መበተን መነሻ ያሏቸውን ምክንያቶችና መፍትሄዎቻቸውን እንደሚከተለው አብራርተውልናል።
ጋብቻ በግለሰቦች ይመሰረትና ወደ ቤተሰብ ከቤተሰብ ደግሞ ማህበረሰብን ይመሰርታል። ጋብቻም ሆነ ቤተሰብ ጥሩ የሚሆነው የጥንዶች የህይወት፤ አመለ ካከትና አስተሳሰብ የተስተካከለ ሲሆን ነው የእነሱ አስተ ሳሰብ ደግሞ በአብዛኛው አስተዳደጋቸውን መሰረት ያደረገና የኖሩትን ቤተሰብ የሚመስልም ነው። ቤተሰብ ማለት እናት፤ አባትና ልጆች ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል ነገር ግን ቤተሰብ በአንድ ቤት ውስጥ ያለውን ሰው፤ እሴት ባህልና ሌሎች ክንውኖችንም የሚያካትት ሲሆን አንድ ግለሰብ ማህበረሰቡን ለመቀላቀል የመኖርን መንገድ የሚማርበትና የሚቀረጽበትም ተቋም ነው።
እንደሚታየውም በተስተካከለ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ሰው ፍቅር፤ እንክብካቤ፤ ይቅርታንና ማህበረሰቡ ጥሩ የሚላቸውን እሴቶች የሚማር ሲሆን ማህበረሰቡን ሲቀላቀልም ሆነ የራሱን ቤተሰብ ሲመሰርት እነዚሁ ማንነቶቹ ይከተሉታል። ባልተስተካከለ ቤተሰብ የሚያድግ ደግሞ የዚህን ተቃራኒ ጸባይ ይዞ ይገኛል። ይሄ ሆኖ ሳለ ለብዙዎቻችን ቤተሰብ በየቀኑ ያለንበት ግን የማናስታውሰው፤ ዘወትር የምንገኝበት ነገር ግን ዘወትር ትኩረት የማንሰጠው ሆኖ ይገኛል።
በመሆኑም አብዛኛው የተስተካከለ ቤተሰብ ነገ ለሚፈጠረው የተስተካከለ ማህበረሰብ መሰረት ሲሆን፤ ባልተስተካከለ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ጥንዶች የሚመሰርቱትም ቤተሰብ የተስተካከለ የመሆኑ እድል የጠበበ ነው። ሰላም የሌለው ቤተሰብ በበዛ ቁጥር ደግሞ እንደ ማህበረሰብ በሰዎች የእለት ከእለት ግንኙነት ላይ ብሎም እንደሀገር የሚፈጥረው ተጽእኖ የጎላ ነው።
ከዓመታት በፊት የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው በጋብቻ መካከል ቅራኔን ከሚፈጥሩት ነገሮች መካከል አንደኛ በጾታዊ ግንኙነት አለመጣጣም ሁለተኛ የገንዘብ ችግር በሶስተኛ ደረጃ የሌላ ወገን ጓደኛና ቤተሰብ ጣልቃ ገብነትና ሌሎች ትንሽ ድርሻ ያላቸው መሆናቸው ተቀምጧል። ከእነዚህ ውስጥ አለመታመንና ደጋግሞ ወደ ሌላ መሄድ ለይቅርታም ለመስማማትም አስቸጋሪ ቢሆንም ሌሎቹ አብዛኞቹ ምክንያቶች ግን ለትዳር መፍረስ በቂ ምክንያቶች ሆነው ሳይሆን በወቅቱ በተገቢው መንገድ ባለመያዛቸው የሚከሰቱ ናቸው። ለዚህም ነው አንዳንድ ጥንዶች እየተዋደዱም መግባባትና መረዳት እየቻሉ ተቀራርቦ ባለመነጋገር ብቻ ለመለያየትና ቤተሰብ ለመበተን የሚደርሱት። ብዙ ሰዎችም ከተፋቱ በኋላ ራሳቸው ምክንያቱ በቂ እንዳልነበረ ይናገራሉ። በአንድ ወቅት በፍርድ ቤት ለፍቺ ቀርበው ከነበሩት 280 ሰዎች 210 ሳይፋቱ ተመልሰዋል። በመሆኑም ቢቻል የጋብቻ ትምህርት መማር ካልሆነም ከባድ ውሳኔዎችን ከመወሰን በፊት ጊዜ ወስዶ ደጋግሞ ማሰብና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
ምንም እንኳ የቤተሰብ መፍረስ ሊገጥም የሚችለው በውስጣዊና በውጪያዊ ምክንያቶች ሊሆን ቢችልም በሁለቱም ቢሆን በአብዛኛው ችግሩ ተቀራርቦ ባለመነ ጋገርና ባለመደማመጥ የሚባባስ ነው። በመሆኑም ጥንዶች በመካከላቸው በተለያዩ ጉዳዮች ትንንሽ አለመስማማቶች ሲፈጠሩና በግንኙነታቸው ደስተኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ በወቅቱ ካለ ይሉኝታ ክፍተቱን ለማጥበብ ተቀራርበው መወያየት ይጠበቅባቸዋል። ካልሆነ ሰው በባህሪው ደስታውን የሚያካፍለው ችግሩን የሚያዋየው አጋር ስለሚያስፈልገው በሥራ ቦታ፤ በሰፈርና በእምነት ተቋማት ካሉ ሌሎች ጓደኞች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ይገደዳል። ይህ ግንኙነት እያደገና እየተጠናከረ ሲመጣ ደግሞ የትዳር አጋርን የሚወክሉ ሚስጥሮችንም ማካፈል ይጀመራል፤ ይህም ቀስ በቀስ ወደ ፍቅር ግንኙነት ያድግና የባሰ ችግር ይፈጠራል።
እንደ ውጪያዊ ተጽእኖ ደግሞ የሀገራችን ማህበራዊ ግንኙነት ጠንካራ ከመሆን አልፎ በከፍተኛ ሁኔታ ጣልቃ መግባት ስለሚስተዋልበት ጥንዶች አዲስ ቤተሰብ ሲመሰርቱ በተቻለ መጠን በገቢም በአካልም ከመጡበት ቤተሰብ ጋር ጥገኛ ባይሆኑ ይመረጣል። ባልና ሚስት ከቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የግላቸው አለመሆኑን በመረዳት የትዳር አጋራቸውን እያዋዩ በስምምነትና በምክንያት ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። ትኩረትም ጊዜም ቅድሚያም መስጠት ያለበት አዲስ ለተመሰረተው የራሳቸው ቤተሰብና የትዳር አጋር መሆን አለበት። በርካታ ቤተሰቦች ደግሰው የዳሯቸውን ልጆች ፍርድ ቤት አስቁመው ሲያፋቱ ይታያል፡፡ ሆኖም ከቤተሰብ ጋር የሚኖረው መቀራረብ በገደብ መሆን አለበት። ለጓደኝነትም ተመሳሳይ ነው፤ የትኛውም ጓደኛ አፈር ፈጭተን አድገናል ብሎ ትዳርን እንዲፈጭ መፍቀድ ተገቢ አይደለም። በዚህ መልኩ ጥንዶቹ የራሳቸውን ግንኙነት ባጠ ናከሩ ቁጥር የውጪውን ጣልቃ ገብነት መቆጣጠር ይችላሉ።
ዛሬ ዛሬ ደግሞ እንደ ቀልድ የምንመለከተውና በየቤተሰቡ እየገባ ያለው ጉዳይ ከማህበራዊ ሚድያ ጋር ያለው ገደብ የለሽ ትስስር ነው። በዚህ ረገድ በአንድ በኩል እንደ ፌስ ቡክ ያሉ ድረ ገጾችን ለረጅም ጊዜ በመከታተል ለቤተሰብ ጊዜ አለመስጠት የሚፈጥረው ክፍተት ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ትክክለኛ ላልሆኑና ቤተሰቡን ለሌላ ድርጊት የሚገፋፉ መረጃዎች መመልከትን ያካትታል። እኛ በድረ ገጽ የምና ያቸው አለባበስ፤ አጊያጌጥ፤ የወን ድና የሴት የሥራ ድርሻ፤ መብት ማስከበር ሁሉ የራሳቸው ተጽእኖ አላቸው። በዚህ ረገድ ባህላዊው አኗኗር አንጻራዊ በሆነ መልኩ የተረጋጋ ሲሆን ዘመናዊነት በተስ ፋፋባቸው አካባቢዎች ተስፋ ፍቶ ይታያል። እኛ ያለንበትን ሁኔታ ጨርሰን ዘመናዊ ወይም ባህላዊ ሳንሆን መሀል ላይ ቀላቅለን ስለያዝነው ሁሉም ችግሮች ይመለ ከቱናል። በመሆኑም እነዚህን የመገናኛ መንገዶች መጠቀሙ ችግር ባይኖረውም ትልቅ ጥንቃቄን ግን ይፈልጋሉ።
በህጉም በኩል በየፍርድ ቤቱ ተግባራዊ ሲደረግ የሚታየው ችግ ር ሲፈጠርና ፍቺ ሲጠየቅ ብቻ ውሳኔ ማሳለፍ ነው። ነገር ግን ለምሳሌ ጋብቻ ለመፈጸም በመንግሥት አካል በኩል የፊርማ ሥነሥርዓት ሲደረግ ስለህጉ የተወሰነ ጭብጥ እንዲኖራቸው ቢደረግ መልካም ነው። በተጨማሪ በህጉ መሰረት ጋብቻው እንዲቀጥል ለማድረግ ለፍቺ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለማስማማት ትኩረት የሚሰጥበት አካሄድ ቢመቻች ተመራጭ ነው። የቤተሰብ ህጉንም በየወቅቱ እየተከታተሉ መፈተሽና እንደ የአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና እንደየወቅቱ ማስተካከል ይጠበቃል።
ትዳር የቤተሰብ ምስረታ መጀመሪያ ነው የሚሉት አቶ ይመስገን ትዳር እንዴት መመስረት እንዳለበት ሲናገሩም “ጋብቻ በሁለት ጥንዶች መካከል የሚፈጸም የቃል ኪዳን ስምምነት ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ ትዳር ሊመሰርቱ ሲነሳ ለምን አገባለሁ? ምን ይጠበቅብኛል? ብሎ ማወቅ አለበት። አንድ ወንድ ጥሩ ባል ብሎም ጥሩ አባት ለመሆን ራሱን ማዘጋጀት ሴቷም ብትሆን ጥሩ ሚስትና ጥሩ እናት ለመሆን እስከ ህይወት ፍጻሜ የሚደርስ አላማ ሊኖራቸው ይገባል። ቀላል የሚመስሉን ወሳኝ የትዳር ግንኙነቶችን ለምሳሌም መቼ ልጅ እንውለድ፤ ስንት ልጅ እንውለድ፤ …. ህይወታችንን እንዴት እንመራለን፤ በሚሉት ጉዳዮች ላይ ሁሉ በግልጽና በጥልቀት በመወያየት ከውሳኔ መድረስ ይጠበቅባቸዋል” ይላሉ።
ጥንዶቹ ትዳር ሲመሰርቱ እንደ ሰርግና ቁሳቁስ ማሟላት ላይ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን በመፈተሽ እስከ ህይወት ፍጻሜ ለሚዘልቀው ጉዞ ብቃቱ አለኝ ወይ ብለው ራስን ማዘጋጀቱ ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው። ሠርግና ጋብቻ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ ሠርግ የተስተካከለ ነው ማለት ትዳር የተስተካከለ ነው ማለት አይደለም። ሠርግ ለጋብቻ ዋስትና አይሆንም። አቅም እስከፈቀደና የወደፊት ህይወትን በማይነካ መልኩ እስከሆነ ድረስ በቤተሰብ በሃይማኖት ተቋማትም በማዘጋጃም ይሁን ሠርግ ማዘጋጀቱ በራሱ ችግር የለውም፤ እንዲያውም ጥሩ ነው፡፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ባልና ሚስት ብሎ በመቀበል ተገቢውን ክብር እንክብካቤ እንዲያደርግና የጥንዶቹን ግንኙነት ይፋ በማድረግ በቤተሰብና ማህበረሰቡ ዘንድ እንደባለትዳር ያላቸውን ተቀባይነት የሚያጎላ ነው።
ነገር ግን ሁሌም መታሰብ ያለበት የቀጣዩ ህይወት መሰረት ነው። በአንድ በኩል ለሠርግ የሚዘጋጁ ጥንዶች ስለሚጠራው ሰው፣ ስለ ምግቡ ፣ስለ ልብሱና ሌሎች ስለ አንድ ቀን ውሎ መርሀ ግብር ብቻ ያስባሉ፤ ይዘጋጃሉ። አንዳንዶች ደግሞ ለማግባት የሚያስቀምጡት ቅድመ ሁኔታ ከትዳር ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ ስመረቅ፤ 30 ዓመት ሲሆነኝ፤ ቤት ስሰራ…. ወዘተ። ነገር ግን በቅድሚያ መታሰብና መዘጋጀት የሚያስፈልገው ለወንዱ ባልና አባት ለመሆን ሴቷም ጥሩ ሚስትና እናት ለመሆን ነው። ለዚህም ትዳር የመግቢያ በር እንጂ መውጫ በር እንደሌለው አድርጎ በአእምሮው ይዞ መጀመር ይጠበቃል።
ይህም ሆኖ በትዳር ዓለም ከሌላው ጊዜ በተለየ ትእግስትና መቻቻል ሊኖር ይገባል። ትእግስት ማለት ግን ችግር ችሎ መኖር ማለት ሳይሆን አንዱን ወገን ትክክል ካልሆነው አካሄድ አልያም ባህሪ ወደትክክለኛው እስኪመጣ ላለው ጊዜ እያገዙ መቆየት ማለት ነው። ችግር ያለበት ካለ በግልጽ መንገርና ለለውጡ መተባበር ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ የትዳር አጋርን ብዙ ገጽታዎች ማወቅ የሚጠበቅ ሲሆን ፤ ሰውን ለማስተካከል ሳይሆን የሆነውን በመረዳት ራሳችንንም ለማረቅ መስራት ይጠበቃል።
ማንኛውንም ሰው ቢሆን መረጃ ሰብስቦ ባህሪውን ማወቅ አዳጋች ቢሆንም በጋብቻ የመጀመሪያው ወቅት የጫጉላ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ያለው ፍቅር ብቻ በዚህ ወቅት ሙሉ ለሙሉ የመተዋወቁም ሆነ ትክክለኛ ጸባይን የማወቂያ እድሉ አነስተኛ ነው። ሁለተኛው የማገናዘቢያ ጊዜ ሲሆን በዚህ ጊዜ ነገሮች በታሰበውና በተገመተው ደረጃ ሳይሆን በትክክለኛ ገጽታቸው ይገለጻሉ። በነዚህ ጊዜያት ብዙ ጊዜ የሚታየው አጣታለሁ ወይም አጣዋለሁ በሚል አስተሳሰብ ወይንም ፍቅረኛን ለማስደሰት ሲባል የውሸት ማንነትን ማስመዝገብ ነው። ውሸት አንድ የትዳር መፍረስና የቤተሰብ መበተን ምክንያት በመሆኑ ራስን ለመግለጽ በምንም ቀመር ለትዳር አጋር ዋሽቶ መቅረብ አይገባም ። ከዋሸን አንድ ቀን ሚስጥሩ ሲወጣ የወደድነውን ማጣታችን አይቀርም፡፡ ካለብን ችግርም ለመላቀቅ እድሉንም አናገኝም። ስለዚህ መታመንና አለመዋሸት ተመራጩ ብቻ ሳይሆን ብቸኛውም የትዳር ማጽኛ መንገድ ነው።
የቤተሰብ መፍረስ ፍቺን የሚከተል ሲሆን ጅማሬውም በሀሳብ ያለመገናኘትና መራራቅ ነው። ቤተሰብ የመሰረቱ ሁለት ጥንዶች በሀሳብ ከተፋቱ በስሜትም መራራቃቸው አይቀርም፡፡ አካላዊ ፍቺ የሚመጣው ከዚህ በኋላ ነው። በሀሳብ ከተራራቁ በኋላ በሶስት መንገድ የፍቺ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ። የመጀመሪያው ይፋዊ በሆነ መንገድ በህግ አግባብ የሚለያዩት ሲሆኑ እነዚህ ያላቸውን ንብረት አንዳንዴም ልጆች ተከፋፍለው በየወገናቸው የራሳቸውን ኑሮ የሚኖሩ ናቸው።
ሁለተኞቹ ደግሞ ህጋዊ ፍቺ አይፈጽሙም፤ ሀብትም አይከፋፈሉም፤ በአብዛኛው ልጆች ከእናታቸው ጋር ይሆናሉ፤ አባት ግን ሌላ ቦታ የራሱን ህይወት ይመራል፡፡ ብዙም ባይሆን ቤታቸውን ጥለው የሚሄዱም ሴቶች አሉ። በሶስተኛ ደረጃ ግን አንድ ቤት ውስጥ እየኖሩ ለአካባቢው ነዋሪና ለቤተሰብ ሰላም የሚመስሉ ነገር ግን እቤት ውስጥ አብረው የማይኖሩ፣ በአንድ ማዕድ የማይቆርሱ፣ አልጋ ለይተው የሚተኙ ናቸው። የእነዚህ ጥንዶች የቤት ውስጥ ኩርፊያ በእነሱ ግንኙነት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን ልጆችንም ጤና የሚነሳ ሲሆን የትኛውም የቤተሰብ አካል እቤት ውስጥ የሚያሳልፈው ጊዜ እንዲኖር አይፈቅድም። በተጨማሪም ግንኙነቱ የተዳፈነ ስለሚሆን ለማስማማት ለሚፈልግም ሶስተኛ ወገን አዳጋች ይሆናል። ይህም ሆኖ ፍቺ ለየትኛውም ችግር መፍትሄ ካለመሆኑ ባሻገር በትክክለኛ ምክንያት ተፋታን የሚሉ እንኳ ቢኖሩ የፍቺ መዘዝ የሆኑት ማህበረሰባዊ፣ ቁሳዊና አካላዊ ችግሮች ሰለባ መሆናቸው አይቀርም።
የቤተሰብን ሥራ እያከናወኑ ያሉ በርካታ ግለሰቦችና ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች አሉ። በእነዚህ ቦታዎች የምናገኛቸው ልጆች በአብዛኛው የቤተሰብ መበተን ገጥሟ ቸው ማረፊያ ያጡ ናቸው። በመሆኑም ጤነኛ ቤተሰብ መመስረት ከተቻለ የእነዚህን ተቋማት ሸክም በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ይቻላል። ጠንካራ ቤተሰብ የጠንካራ ማህበረሰብ ጠንካራ ማህበረሰብ የጠንካራ ሀገር መሰረት ነው።
ይሄ እንዳለ ሆኖ እንደ ሀገር የቤተሰብ ችግርን ለመቀነስም የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን አልሰሩም የሚሉት አቶ ይመስገን የሃይማኖት ተቋማት ህብረተሰቡ በሃይማኖት ተቋማት ላይ እምነት ስላለው የሃይማኖት አባቶች በስብከት ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም በተግባር እያሳዩ፤ ማስታረቁ ጥሩ ቢሆንም ከማግባታቸው በፊት ስለትዳርና ቤተሰብ፤ ኑሮም ከጀመሩ በኋላ ችግር ከተፈጠረ ከመባባሱ በፊት እየተከታተሉ መገንባት ይጠበቅባቸዋል። በትምህርት ቤቶችም እያንዳንዱ የትም ህርት አይነት የየራሱ ሥነ ምግባር ስለሚኖረው ለየጉዳዩ ከሚያቀርቡት ምሳሌ ጀምሮ ስለቤተሰብና ግብረገብነት አካቶ ማስተማር ይጠበቃል ሲሉ አቶ ይመስገን አስገን ዝበዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ታህሳስ 3/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ