• አገሪቱ በዘርፉ በዓለም 93ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች
አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የተመራማሪ-ህዝብ ጥምርታ 1 ለ 4587 (ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 218 ተመራማሪዎች) መሆኑ ተገለጸ::አገሪቱ ከሳይንሳዊ ምርምር ተቋማት ጥራት አንጻርም በዓለም ላይ ከሚገኙ 142 አገራት በ93ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ተጠቁሟል::
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ሽግግር ተመራማሪና የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙሉጌታ ውቤ በዘርፉ ያደረጉትን ጥናት መነሻ አድርገው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የተመራማሪ ህዝብ ጥምርታው በአገሪቱ ያለው ተመራማሪ ቁጥር ከአጠቃላይ የህዝብ ብዛት አንጻር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን ያሳያል::
ለንጽጽር ከተመረጡት አገሮች ማለትም ኬንያ 1ሺ 529፣ ደቡብ አፍሪካ 1ሺ108 እና ሴኔጋል 856 ተመራማሪዎች ያላቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ለአንድ ሚሊዮን ዜጎቿ 218 የምርምር የሰው ሀይል ብቻ በመያዝ ከመጨረሻዎቹ ተርታ መሰለፏን አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል::በተጨማሪም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር ከሰሀራ በታች ከሚገኙ አገሮች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል::
እንደ አቶ ሙሉጌታ ማብራሪያ፤ ካሉት ተመራማሪዎችም 49 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑትን የመንግስት ተቋማት፤ 47 ነጥብ 8 በመቶዎቹን ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀጥረው የሚያሰሩ ሲሆን፣ የቢዝነስ ኢንተርፕራይዞችና ለትርፍ ያልተቋቋሙ የግል ተቋማት ደግሞ በቅደም ተከተል ዜሮ ነጥብ 6 በመቶ እና ሁለት በመቶ ቀጥረዋል::
በአገሪቷ የግል
ሴክተሩ በምርምር ላይ አነስተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ከ 142 የዓለም አገራት 133ኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ፤
አሃዙም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ዝቅተኛ መሆኑንና ይህም የሚያመላክተው በኢትዮጵያ የግል ቢዝነስ ሴክተሩ
ምርምር ላይ ያለው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አብራርተዋል::
ይህ ደግሞ አገሪቱ በዘርፉ በምርምር ጥራት በዓለም ከሚገኙ 142 አገራት 93ኛ ደረጃ ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል::
እርሳቸው እንዳሉት፤ ከምርምሮቹ ውስጥ ግብርና ትልቁን ድርሻ በመውሰድ 38 በመቶ የሚሆኑትን ተመራማሪዎች ይዟል::29 በመቶውን ድርሻ የያዘው ደግሞ የማህበረሰብ ሳይንስ ሲሆን፤ የኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂና የህክምና የምርምር ዘርፎች በቅደም ተከተል ስምንት በመቶ፣ አምስት በመቶና አራት በመቶ በመያዝ አነስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ::
አቶ ሙሉጌታ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጥምረት ወይም በኮንትራት የተከናወነ ምርምርና ውጤት ሲታይም 90 በመቶ ምንም የጋራ ሥራ እንዳልተሰራ ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያላቸው ትስስር ሲዳሰስም ተማሪዎች ኢንዱስቱሪዎች ላይ ሄደው ትምህርት እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር በጥናትና ምርምር ረገድ በሚገባ እየሰሩ አለመሆናቸውን ገልጸዋል::
የምርምር ሥራ ክፍል ከፍተው ወደ ሥራ የገቡ አብዛኛዎቹ የግልና የመንግስት ኢንዱስትሪዎች የሰለጠነና በተጨባጭ የምርምር ሥራዎችን የመስራት ልምድ ያካበተ የሰው ሀይል ያለመኖርና የምርምር አመራር ክህሎት ማነስ ችግሩን እንዳባባሰው አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል::
የተመራማሪዎች ቁጥር ሲያንስ በተዘዋዋሪ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልምምድ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ውስንነትንም እንደሚፈጥር ያስገነዘቡት ባለሙያው፤ በቂ ክህሎትና አቅም ያላቸውን የተመራማሪዎች ቁጥር ማሳደግና በሁሉም ዘርፍ የሚደረገው የምርምር ሥራ መበልጸግ እንዳለበት ጠቅሰዋል::ተመራማሪዎችን ብቻ ሳይሆን የምርምር መሰረተ ልማት ተግዳሮቶችንም መቅረፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
አዲሱ ገረመው