አዲስ አበባ፡- የጥምቀት ክብረ በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች (ኢንታንጂብል) ባህላዊ ቅርስ ወካይ ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እንደሚረዳ ተገለጸ::
የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ፋንታ በየነ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፤ በዓሉ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰው ልጆች የማይዳሰሱ ቅርሶች (ኢንታንጂብል) ባህላዊ ቅርስ ወካይ ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡን ገልጸው፤ የበዓሉን ሁነት ለማየት የሚፈልጉ የተለያዩ አገራት ዜጎች በሚያገኙት መረጃ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት እንዲጎበኙና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር እንደሚያግዝ ገልጸዋል::የቱሪስት ፍሰቱ እየጨመረ ሲመጣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል::
ባለሥልጣኑ ከተሰጠው ተልዕኮ ውስጥ አንዱ ቅርሶችን መመዝገብ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቅርሶችን በብሄራዊና ዓለም አቀፍ ደረጃ በማስመዝገብ የጥምቀት በዓል አራተኛው የማይዳሰሱ የኢትዮጵያ ቅርስ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡን አስታውቀዋል::ቅርሱ ከሃይማኖታዊ እሴቶች ባሻገርም በርካታ ባህላዊ እሴቶች ስላሉት የተለያዩ የዓለም የማህበረሰብ ክፍሎች በበዓሉ ላይ እንዲታደሙም ያስችላል ብለዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የጥምቀት በዓልን በዓለም አቀፍ ደረጃ በቅርስነት ማስመዝገቡ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሻለ የእኔነት ስሜት እንዲኖርና በአግባቡ ተጠብቆ በተሻለ ሁኔታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ይረዳል::
የበዓሉን እሴት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅም ፋይዳው የጎላ ነው::ቅርሱ ሲመዘገብ በዩኔስኮ ድረ ገጽና በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለሚተዋወቅ አገሪቷ በቅርሶቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲኖራት ተጨማሪ ግብዓት ነው::የአገሪቷን ማህበራዊ ትስስር ከማጠናከር አንጻርም ጠቀሜታው ጉልህ ነው::
እንዲህ ዓይነት ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገቡ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች የጥናትና ምርምር ስራቸውን በዚህ ላይ እንዲሰሩ በማድረግ፤ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እንዳለውና፤ ይህንን ታሳቢ በማድረግም በአገሪቷ በብሄራዊ ደረጃ እስካሁን የ76ቱም ብሄር ብሄረሰቦች የሆኑ ቅርሶች መመዝገባቸውንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::
ዳይሬክተሩ፤ ቅርሱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስመዝገብ አስቀድሞ በብሄራዊ ደረጃ የመመዝገብ ሥራ መሠራቱን በመጠቆም፤ በዓሉን የሚዳስሱ የተለያዩ ሰነዶችን የማዘጋጀት፤ በዩኔስኮ በሚዘጋጀው መጠይቅ መሠረትም ከቅርሱ ምንነትና ትርጉም ጀምሮ ቅርሱ ያለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዲዳሰሱ መደረጉንና ቅርሱን ሊገልጹ የሚችሉ 10 ፎቶዎችና የ10 ደቂቃ ቪዲዮ ለዩኔስኮ ቀርቦ በመጨረሻም ተቀባይነት አግኝቶ መመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል::
የጥምቀት ክብረ በዓል ቦጎታ – ኮሎምቢ በተሰየመው 14ኛው የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዓመታዊ ጉባዔ በሰው ልጆች የኢንታንጂብል ባህላዊ ቅርስ ወካይ ዝርዝር ውስጥ መመዝገቡ ይታወቃል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
አዲሱ ገረመው