-የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሽልማት አስመልክቶ በብሄራዊ ቤተመንግሥት የእራት ግብዣ ተደርጓል
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያገኙት የኖቤል ሽልማት መላ ኢትዮጵያውያን አንገታችንን ቀና እንድናደርግ ያደረገ ታላቅ ድል መሆኑን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለፁ::
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በብሄራዊ ቤተመንግሥት የእራት ግብዣ አድርገዋል::
በዝግጅቱ ላይ ፕሬዚዳንቷ ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በኦስሎ ኢትዮጵያ ከፍታ ላይ እንድትወጣ ኢትዮጵያውያንም አንገታችንን ቀና እንድናደርግ አድርገዋል ብለዋል።
ሽልማቱ ለመላው ሰላም አክባሪ አፍሪካውያን የተበረከተ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አሁን ያለበትን የተረጋጋ ሁኔታ ለአለም ህዝብ ማሳየት የተቻለበት እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን የተጋረጡብንን ችግሮች በጋራ ከመፍታት ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ደስታው ተባብረንና ተደጋግፈን አገራችንን ለመገንባት ቃል የምንገባበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በስነስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር እኛ ኢትዮጵያውያን ተከባብረንና ተፈቃቅረን ከሰራን የማንሻገረው ዳገት አይኖርም ብለዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እደገለፁት እብሪትና ፉከራ ብቻውን ዋጋ የለውም:: ቢያንስ ልጆቻችን ከተመፅዋችነት ወደ ረጂነት እንዲሸጋገሩ ተግተን መስራት ይገባናል ሲሉም መልዕክት አስተላፈዋል::
የደሃ ሃገር ዜጋ ሲተኛ አያምርበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተግተን በመስራት ይህችን
አገር ለማበልፀግ ልባችን የሰፋ፣ ትከሻችን ብዙ መሸከም የሚችል ልናድርገው ይገባልም ብለዋል::
በቅርቡ ሳተላይት እናመጥቃለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የብልፅግናችን የመጀመርያ ምዕራፍ እንደሆነም ጠቁመዋል::
ከልመና ወጥተን ወደ ብልፅግና እንድንሄድ ከመላው የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ህዝቦች ጋር በትብብር መስራት ይኖርብናል፣ ያኔ ምናልባትም ከ10 ዓመታት በኋላ ከልመና እንወጣለን ፤ ይህንንም የሚያቆም አይኖርም ሲሉም ተናግረዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 3/2012
ድልነሳ ምንውየለት