አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአግባቡ ማልማት ካልቻሉ ባለሃብቶች 571 ሄክታር መሬት ተነጥቆ ለመሬት ባንክ ገቢ መደረጉም የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ከኢንቨስትመንት ማግኘት የተቻለው 9ነጥብ9 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል እንደገለፁት፤መሬት ወስደው ወደ ስራ መግባት ባልቻሉና ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ማድረግ ካልቻሉ 65 ባለሃብቶች ላይ 571 ሄክታር መሬት መነጠቁንና ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዞኑ ከፍተኛ የሆነ ሃብት ቢኖርም የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ዝቅተኛ መሆኑን እና በ2011 በጀት ዓመት 11 ባለሃብቶች ብቻ ወደ ዞኑ መምጣታቸውን ገልፀው፤ በዞኑ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጠረው የሥራ ዕድልም 3000 ብቻ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ወይዘሮ አስቴር የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ 276 ባለሃብቶች በሥራ ላይ ናቸው፡፡ 45 ደግሞ በተለያየ ምክንያት ሥራ አቁመዋል፡፡ 15 ደግሞ ሂደቱን አጠናቀው ወደ ሥራ እየገቡ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ኃላፊዋ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተሰራው ሥራም በጣም ዝቅተኛና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የቆየ ነው፡፡ የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን ኢንቨስትመንት ከፍተኛ አቅም ያለው ቢሆንም በዚህ ላይ በትኩረት ሲሠራ አልነበረም፡፡
ዞኑ በኦሮሚያ ካሉ ዞኖች ከአዲስ አበባ 112 ኪሎ ሜት ርቀት የሚገኝና አመቺ መልክዓ ምድር ያለው ቢሆንም የዞኑን ዕምቅ ኃብት ለባለሃብቶች ለማስተዋወቅ ባለመቻሉና ለባለሃብቱም የሚሰጠው መስተንግዶ የተንዛዛ መሆኑ በዞኑ ያለው ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሊዳከም መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የአመራር አቅም ውስንነትና ትኩረት አለመስጠት፣ የቢሮክራሲ መብዛት፣ ከፌዴራልና መንግስት ጀምሮ ባለሃብቶችን ወደዞኑ እንዲመጡ ከማበረታታት ይልቅ ወደሌላ አካባቢ መላክና ሌሎች ችግሮች መኖራቸው የገለፁት ኃላፊዋ፤ ይመጡ የነበሩትም አብዛኞቹ ባለሃብቶች ሳይሆን ኪራይ ሰብሳቢዎች ነበሩ፡፡ በተለይም ብድር ወስደው ለሌላ ዓላማ የሚያውሉ እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤ ከላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል ለአንድ ሄክታር 500ሺ ብር እንዲከፍል የሚያዝ እንደነበርና ይህም አርሶ አደሩን የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ ለመተግበር አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞን ቅምብቢት ወረዳ ላይ ሰፋፊ መሬት ታጥሮ ለዓመታት የማን እንደሆነ ሳይታወቅ ተቀምጦ መቆየቱንም አብራርተዋል፡ ፡ በተደጋጋሚ ማስታወቂያ ሲወጣ ‹‹የእኔ ነው›› የሚል አካል አለመኖሩን አስገንዝበዋል፡፡ በ44 ባለሃቶች ስም ታጥሮ የነበረ 10 ሄክታር መሬትና ንብረት መወረሱንና ለመንግስት ገቢ መደረጉን፤ ጥፋቱን የፈፀሙ አካላት ደግሞ በህግ ከለላ ሥር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አንድ ከተማ መስተዳድር እና 13 ወረዳዎችን ያካተተ ሲሆን፤ 8ሺ989 ኪሎ ሜትር ስኩዩር ስፋት ይሸፍናል፡፡ ላይም ስቶን፣ ሳንድ ስቶን፣ እምነበረድ በመሳሰሉ ማዕድናት የበለጸገ አካባቢ ሲሆን በእንስሳትና እንስሳት ተዋፅኦ ከፍተኛ ሃብት ያለበትና ሰፋፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉት ዞን መሆኑን ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር