– ዩኒቨርሲቲዎቹ ውሳኔው ተገቢ ነው ብለዋል
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ፖሊስ በሁሉም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እየገባ ሲሆን በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ደግሞ አስተማማኝ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በበኩላቸው የሚኒስቴሩ ውሳኔ አግባብነት ያለው ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ ስለዝግጅት ክፍሉ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች መካከል ግጭት እየተከሰተ በመሆኑና በዩኒቨርሲቲዎች ያለው የግቢ ፖለ.ስ ጥበቃ ብቻውን ጸጥታ ለማስጠበቅ ብቁ ባለመሆኑ በፌዴራል ፖሊስ መጠበቁ አስፈላጊ ሆኗል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ችግር ለማስቆም በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቅ ሰሞኑን ውሳኔ መተላለፉን አስታውሰው፤ በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ፌዴራል ፖሊስ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ በተቀሩት ውስጥም በመግባት ላይ ሲሆኑ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ገብቶ እንደሚጠናቀቅ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ ደቻሳ ገለፃ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ አካባቢዎችና ክልሎች የሚገኙ ቢሆኑም ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግስት እስከሆነ ድረስ መንግስት ጥበቃውን የማስተካከልና ጸጥታ የማስጠበቅ ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የነበሩ የክልል ፖሊሶች በፌዴራል ፖሊስ መተካታቸውን ጠቁመዋል:: ይሁንና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የክልል ፖሊሶች ወደ ግቢ ገብተው የሚያግዙበት ዕድል እንደሚኖር አረጋግጠዋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ ግቢ የገቡት የፌዴራል ፖሊሶች ቀደም ሲል ግቢ ይጠብቁ የነበሩ የዩኒቨርሲቲ ፖሊሶችን አቅም የሚያሳድግ ሥልጠና እንደሚሰጡና በትብብር አስተማማኝ ፀጥታ ለማስፈን በጋራ እንደሚሰሩ አቶ ደቻሳ አብራርተዋል፡፡
ምንም እንኳ የፌዴራል ፖሊስ ዋንኛ ተልዕኮው ዩኒቨርሲቲዎችን መጠበቅ ባይሆንም፤ አስተማማኝ ሠላም እስኪመጣ ድረስ ግን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ከክልሎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከሥምምነት ላይ መድረሱንም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምሸት ተሾመ እንደሚሉት፤ በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ባይኖርም በሌሎች አካባቢዎች የተፈጠረው ችግር ወደ ግቢው የመዛት አዝማሚያ በማሳየቱና በዘላቂነትም በዩኒቨርሲቲው ጸጥታ ለማረጋገጥ የፌዴራል ፖሊስ መግባቱ ወሳኝ ነው፡፡
አቶ አለምሸት አክለው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ ግቢ እንዲገቡ መወሰኑ ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች የሚያቃልል መሆኑን አብራርተዋል፡ ፡ ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲውን ይጠብቁ ከነበሩ ፖሊሶች ውስጥ በስራቸው ላይ ቸልታ ያሳዩና አድሎዓዊ ተግባር ያከናወኑትንም ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ በቀጣይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሠራ እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔም አግባብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በበኩላቸው፤ የፌዴራል ፖሊስ በዩኒቨርሲቲዎች መመደቡ አግባብ መሆኑን ጠቁመው ዋነኛው ማጠንጠኛ ህግ ማስከበሩ ላይ ያተኮረ መሆን እንዳለበትና ችግሮች እስከተቃለሉ ድረስም ማንኛውም አካል ቢገባ ችግር እንደማይኖረው አስገንዝበዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዎች ፎረምም ላይ በተደጋጋሚ ይህ ጥያቄ ሲነሳ እንደነበርና ጥበቃውም በፌዴራል መንግስት እንዲሆን ተደጋጋሚ ጥያቄና ውትወታ እንደነበር አስታውሰው አሁን ባለው ሁኔታ የዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎችና ሰራተኞች በአብዛኛው በአካባቢያቸው ስለሚቀጠሩ ሥርዓትን ከማስከበር ይልቅ በመላመድና ከመተዋወቅ የተነሳ ህግ የማስከበሩ ሂደቱ እየላላ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አካባቢው ሠላም ሆኖ ዩኒቨርሲቲዎች እየተረበሹ ነው፡፡ ይህም ካለማወቅ የመነጨ ሳይሆን በማወቅም ወደ ችግሩ እየገቡ ነው፡፡ ይህ አግባብ ካለመሆኑም በተጨማሪ ችግሩን እየከፋ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ዩኒቨርሲቲዎች በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠበቁ መደረጉ አግባብ ነው ብለዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ በየጊዜው እየተቀያየረ የሚሰራ ሲሆን በይሉኝታና መላመድ ብሎ ችግሮችን በችልታ እንደማያልፉ ጠቁመዋል፡፡
ይሁንና ከላይ ጀምሮ ለተማሪዎች፣ አስተዳደር ሠራተኞችና የወጣው ህግ ሙሉ ለሙሉ ካልተተገበረ በፌዴራል ፖሊስ ብቻ መጠበቁ እልባት አይሰጥም፡፡ ዕርምጃዎችም ሲወሰዱ በዘርና ሃይማኖት የማላከክ አባዜዎች እንደአገር እየሰፉ ስለሆነ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር