አሮጌ ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ሲገባ በዓመቱ የነበሩ ሁነቶችን መዳሰስ የተለመደ ነው፡፡ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የፈረንጆቹ 2019 የኢትዮጵያ ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠራበት ዓመት ነው፡፡
በፈረንጆቹ 2019 የዓለም መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያን ስም ደጋግመው ጠርተዋል፡፡ በርሃብና በጦርነት ስሟን ይጠሩ የነበሩ መገናኛ ብዙኃን የአሸናፊነት ዋንጫ ከፍ አድርገው የያዙ ኢትዮጵያውያንን አሳይተዋል፡፡ በአትሌቶቻችን ከፍ ይል የነበረው ሰንደቅ ዓላማ በምርምርና በኪነ ጥበብ ሥራዎችም ከፍ ያለበት ዓመት ሆኗል፡፡ በአትሌቶቻችን የደስታ እንባ ሳንወሰን በመሪዎቻችንና በተመራማሪዎቻችንም ብድግ ብለን በኩራት ባንዲራ ማውለብለብ ጀምረናል፡፡
ተከብረው ያስከበሩን ብዙ ጀግኖችን ሀገራችን አፍርታለች፡፡ከነዚህ ጀግኖች መሃል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አንዱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በበዓለ ሲመታቸው በፓርላማ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም እንደሚመጣ በገቡት ቃል መሰረት ሰላም አምጥተዋል፡፡ ለዘመናት የቆየውን የሁለቱ አገራት ቁርሾ ወደ ሰላም በመመለሳቸውም ይህን ዓለም አቀፍ የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል:: 100ኛው ተሸላሚ መሆናቸው ደግሞ አይረሴ ያደርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሽልማቱን በተቀበሉበት ዕለት ባደረጉት ንግግር፤ የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን አመስግነዋል፡፡ ሽልማቱን ማግኘት የተቻለው በሁለቱም ወገን የሰላም ፍላጎት በመኖሩ ነው፡፡
ሌላኛው ጀግና ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ናቸው፡፡አቶ ተወልደ ገብረማርያም የዓመቱ የአየር መንገዶች ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ሽልማቱን ያገኙት ካፓ (CAPA) በተባለው ታዋቂ ዓለም አቀፍ የአቪየሽን ተቋም አማካኝነት ነው። ዋና ስራ አስፈጻሚው በአመራርነት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለሽልማት አብቅቷቸዋል።
ፍልቅልቋ አትሌት ደራርቱ ቱሉም በአትሌትነት እንዳኮራችን ሁሉ ዛሬም በሌላ መድረክ እራስዋንና ሀገሯን በዓለም መድረክ ማኩራት ችላለች፡፡ ሻለቃ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የዓመቱ ምርጥ ሴት በሚል ዘርፍ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባካሄደው የ2019 የዓለም አትሌቲክስ ሽልማት ላይ ታዋቂዋን ሻለቃ አትሌት ደራርቱ ቱሉን በትራክ ላይ ስኬቷና ከውድድር ከራቀች በኋላ ባስመዘገበችው የአመራር ብቃት የ2019 ምርጥ ሴት ዘርፍ ሽልማት ተበርክቶላታል።
የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ አምሃ መኮንን የዘንድሮውን የፈረንሳይ ጀርመን የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ሽልማት ማሸነፋቸው ሌላው የዓለምን ትኩረት የሳበ ዜና ነው። ጠበቃ አምሃ መኮንን በኢትዮጵያ በነበረው አስቸጋሪ ወቅት እና ጊዜያት ሁሉ ለዜጎች ሰብዓዊ መብት እና ነጻነት መከበር ላበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ሽልማቱ የተበረከተላቸው።ሽልማቱን የጀርመንና የፈረንሳይ አምባሳደሮች ያበረከቱት ሲሆን በስነ ስርዓቱ ላይ ቤተሰቦቻቸው፣ ጓደኞቻቸው እና የሙያ ባልደረቦቻቸው ተገኝተዋል።
አቶ አምሃ መኮንን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አማካሪና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅትና የሰብዓዊ መብቶች ጠበቆች እና በኢትዮጵያ የዲጂታል መብቶች አውታር መረብ መስራች ናቸው። አቶ አምሃ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ (ቪ ኦ ኤ) እንደገለጹት፤ ሽልማቱ የተሰጣቸው በሽብር ተከሰው ለነበሩ ጋዜጠኞች ጠበቃ የሚሆን ሰው በጠፋበት ጊዜ ጠበቃ ሆነሃል በሚል ነው፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ስራ ፈጣሪ ፍሬወይኒ መብራህቱ የአሜሪካው ዜና ማሰራጫ ጣቢያ (ሲ ኤን ኤን) የ2019 ጀግና ሽልማትን አሸናፊ ሆናለች። ፍሬወይኒ በአሜሪካ ሀገር የኬሚካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፤ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሴቶች የፅዳት መጠበቂያዎችን ዲዛይን ያደረገች እና የፈጠረች ድንቅ ሴት ናት።
‹‹ማሪያም ሳባ›› የተሰኘ የፅዳት መጠበቂያ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ በመቐለ ያቋቋመቸው ፍሬወይኒ መብርሃቱ ፤ በዚህ ስራዋም የሲ ኤን ኤን የ2019 ጀግና በመሆን ተመርጣለች፡፡ ከህይወት ልምዷ በመነሳት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ማምረቻ ያቋቋመች ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2006 በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የንፅህና መጠበቂያ የባለቤትነት ማረጋገጫ በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተሰጥቷታል።
በአጠቃላይ በፈረንጆቹ 2019 ከሃያ በላይ ኢትዮጵያውያን ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የ‹‹ዲፌንድ ዲፌንደርስ›› የ2019 የሰብዓዊ መብት ሽልማት ተሸላሚ ናቸው፡፡ ማርታ ገበየሁ የ2019 የወክማ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የውሃ ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ዶክተር ሐረገወይን አሰፋ የአሜሪካ የኬሚስትሪ ማህበረሰብ የኬሚስትሪ ጀግና ተብለው ተሸልመዋል፡፡
ዶክተር ይሁን ድሌ እና ዶክተር አብዩ ወርቅሉል የ2019 የዓለም አቀፍ የምግብና እርሻ ልማት ቦርድ ሽልማት አሸናፊዎች ናቸው፡፡
የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማህበር ‹‹ምርጥ ወንድ ወጣት አትሌት›› ሲል አትሌት ሰለሞን ባረጋን ሸልሟል፡፡ ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም የ2019 የሀርቫርድ የሳይካትሪና ባዮ ስታቲስቲክስ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በተመሳሳይ ዶክተር አረጋይ ግርማይ የሰሜን ካሮላይና ሐኪሞች አካዳሚ የዓመቱ ምርጥ የቤተሰብ ሐኪም ሽልማት ተሸላሚ ናቸው፡፡ ዶክተር ዘቢብ የኑስ የ‹‹Future Leaders African Independ¬ent Researcher (FLAIR) Fellowship Award›› አሸናፊ ሆነዋል፡፡
አርቲስት አብርሃም በላይነህ የ2019 የአፍሪካ ሙዚቃ ሽልማት የአፍሪካ ባሕላዊ ሙዚቃ ዘርፍ አሸናፊ፣ አርቲስት አቡሽ ዘለቀ የ2019 ‹‹Star of A Generation Award›› አሸናፊ፣ አርቲስት መላኩ በላይ የ2019 ‹‹Visa for Music Award›› ተሸላሚ፣ በፍቃዱ ኃይሉ የ2019 የ‹‹International Writer of Cour¬age Award›› አሸናፊ፣ ሔኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ) የHotel Show Africa/MICE East Africa Forum & Expo ምርጥ የቱሪዝም ጋዜጠኛ ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ዋለልኝ አየለ