አዲስ አበባ፡- የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የተለየዩ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ላለው የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፕሮጀክት የሚውሉ 122 ተሽከርካሪዎችን በድጋፍ ሰጠ፡፡
የእንስሳትና የአሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ብሄራዊ አስተባባሪ ዶክተር ቶማስ ቸርነት በግብርና ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ የተሽከርካሪ ርክክቡ በተካሄደበት ወቅት እንደገለፁት፤ ተሽከርካሪዎቹ በዋናነት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚደረግባቸው ስድስት ክልሎችና ሰባት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቶች ይከፋፈላሉ፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልነበሩ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡
ለተሽከርካሪዎቹ ግዥ 101 ሚሊዮን ብር በላይ በአለም ባንክ ወጪ መደረጉን የገለፁት ዶክተር ቶማስ፤ የተሽከርካሪዎቹ ድጋፍ በተለይም በደጋና በወይና ደጋ አካባቢዎች ለተደራሽነት አዳጋች በሆኑ ቦታዎች ላይ ሰፍረው የሚገኙ አርሶአደሮችንና አርብቶአደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ይህም ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚወስደውን ጊዜና ጉልበት የሚቀንስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዶክተር ቶማስ ማብራሪያ፤ የእንስሳትና የአሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክቱ እየተተገበረ የሚገኘው በስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 58 ወረዳዎች እና 1ሺ755 ቀበሌዎች ውስጥ ሲሆን 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን አርሶ አደሮችንንና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ በዋናነትም የስጋ፥ ወተት፥ አሳና ዶሮ ሃብት ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ አሰራሮችን፥ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል፡፡
ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ስድስት ዓመታት ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ አርሶአደሮችንና አርብቶአደሮችን የአመጋገብ ስርዓት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን አስተባባሪው ገልፀው፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም ለበርካታ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጠርም አስገንዝበዋል:: ይህም የገቢ አቅማቸውን ከማሳደግ ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ በ50 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል 176 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ በብድር መገኘቱን የገለፁት ዶክተር ቶማስ፤ በኢትዮጵያ መንግስትም 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር መበጀቱን ጠቁመዋል:: በተጨማሪም ተጠቃሚዎች በጉልበታቸው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት ፕሮጀክት በመሆኑ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሀሰን በበኩላቸው፤ በድጋፍ የተገኙት ተሽከርካሪዎች ዘመናዊና የፍጥነት መቆጣጠሪያ ጂፒኤስ የተገጠመላቸው በመሆኑ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲተገበርና ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም በተሽከርካሪ እጥረት ምክንያት በእንስሳት ጤና ላይ ይደርስ የነበረውን ጉዳት ለመቀነስ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ማህሌት አብዱል