በሰው መነገድንና በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻ ገር ወንጀልን ለመከላከል ከጎረቤት ሀገራት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ዓቃቤ ህግ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ዓቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ከበደ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት በሰው መነገድ እና በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እንዲሁም ህገወጥ የስራ ስምሪቶችን ከመካሄድ ጋር በተያያዘ በየዕለቱ በርካታ ወንጀሎች የሚፈጸሙ ሲሆን በዚህም በርካቶች ለሞት፤ለአካል መጉደልና ለስነለቦና ቀውስ መዳረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም አቅም ኖሮት ሀገር ውስጥ ሊሰራ የሚችልን ወጣት ኃይል በማታለል ከሀገር በማስወጣት ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች እንዲጋለጥ የሚያደርጉ በርካታ አካላት በዚህ ተግባር ላይ እንደሚሳተፉ የገለጹት ዳይሬክተሩ የእነዚህ ህገወጥ አካላት ተሳትፎም ከመንደሮች ጀምሮ እስከ ድንበሮች ድረስ በተዘረጋ ሰንሰለት የሚመራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሀገሪቱ በርካታ መውጫ በሮችም በየጊዜው በሰው መነገድ እና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል እንደሚፈጸምባቸውም አስረድተው ዋናዋና መውጫ በሮች በሚባሉት በአፋር ፤በመተማ፤በሞያሌ፤በሶማሊ ክልል በርካታ ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ አቶ ዝናቡ ተናግረዋል፡፡
በሰዎች ሲነግዱና በህገወጥ መንገድ ሰው ሲያሻግሩ የተደረሰባቸው 128 ግለሰቦች ተይዘው ፍርድ ማግኘታቸውንና በቀጣይም በዚህ ወንጀል ውስጥ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላትን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጥምረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
መንገሥት ከተለያዩ አካላት ጋር ጥምረት ፈጥሮ በሰራቸው ስራዎችም በደላሎች ተታለው ከሀገር ሊወጡ የነበሩና ለተለያዩ ወንጀሎችና ህገወጥ ድርጊቶች ሰለባ ሊሆኑ የነበሩ 1986 ዜጎችንም ማዳንና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የሚሰጠው ብይን ጥፋቱን የሚመጥንና አስተማሪ ያለመሆኑ በሰው መነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻ ገር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲበራከት ምክንያት መሆኑን ያስረዱት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ይህንኑ ችግር የሚቀርፍና በአጥፊዎች ላይ እስከ ሞት ድረስ ቅጣት የሚያስጥል ህግ በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
እስማኤል አረቦ