አዲስ አበባ፡- በተያዘው የምርት ዘመን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በከፍተኛ ርብርብ ከተዘራ ሰብል ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነውን ምርት መሰብሰብ መቻሉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፤ በምርት ዘመኑ በመኸር በአገር አቀፍ ደረጃ 13 ነጥብ 55 ሚሊዮን ሄክታር በማልማት 382 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ 13 ነጥብ 51 ሄክታር በዘር መሸፈን ተችሏል፡፡
ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተዘራው ሰብል ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በተደረገው ርብርብ በአጠቃላይ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር ወይም 60 በመቶ ያህል መሰብሰብ ተችሏል፡፡
የመኸር ሰብል በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እየተሰበሰበ ሲሆን፤ በአማራ ክልል 61 ነጥብ 2 በመቶ፣ በኦሮሚያ ክልል 52 ነጥብ 5 በመቶ፣ በትግራይ ክልል 81 በመቶ፣ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል 55 ነጥብ 6 በመቶ በቤንሻንጉል ክልል 24%፣ በሐረሪ ክልል 92 እንዲሁም በጋምቤላ ክልል መቶ በመቶ ተሰብስቧል፡፡
ከብሄራዊ ሜትዎሮሎጂ ኤጀንሲ ያገኘው መረጃ፤ የታህሳስ ወር የአየር ጠባይ ቅድመ ትንበያ በአዛኛው አካባቢ ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ጠባይ እንደሚያመዝን ቢሆንም፤ በተከሰተው የአየር ለውጥ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እንደተከሰተ ነው ግብርና ሚኒስቴር የገለጸው፡፡
በኦሮሚያም ክልል ምዕራብ እና ምሥራቅ ወለጋ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ አርሲ እና ባሌ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ የጉጂ እና የቦረና ዞኖች፤ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ፣ አብዛኛው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፤ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ የደቡብ እና የሰሜን ወሎ ዞኖች ፣ ሰሜን ሸዋ፤ የደቡብ ትግራይ ዞን፣ በሶማሌ ክልል የሚገኙት አብዛኛዎቹ ዞኖች በአብዛኛው መደበኛውና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 4/2012
ዋለልኝ አየለ