አዲስ አበባ፡- የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተቀበሉት የሰላም የኖቤል ሽልማት ሰላምን ለሚፈልግ የሰው ዘር በሙሉ የተበረከተ ስጦታ እንደሆነ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኖቤል ሽልማቱ ሜዳልያና ዲፕሎማ ለብሔራዊ ሙዚየም ተበርክቷል፡፡
ሽልማቱ በትናንትናው ዕለት ለብሔራዊ ሙዚየም በተሰጠበት ወቅት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል፤ ሽልማቱ ሰላምን ለሚፈልግ የሰው ዘር በሙሉ የተበረከተ ስጦታ መሆኑን ጠቁመው፤ በሽልማቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም የኖቤል ሽልማት ኢትዮጵያውያንን በእኩል መንፈስ ያስደሰተ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤ ሽልማቱም በብሔራዊ ሙዚየም መቀመጡ በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያ ከወጣችበት የድል ማማ ላይ እንዳትነሳ ያስችላል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪሃት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ለውጡን ለማስቀጠል የተካሄደውን ርብርብ አስታውሰው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኖቤሉ በለውጡ ሂደት ዶክተር አብይ ባደረጉት የማይተካ ሚና የዓለም ህዝብ ለሥራቸው እውቅናና ይሁንታ የሰጠበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስትሯ ሽልማቱ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን፤ ለአፍሪካና አፍሪካውያን እንዲሁም በዓለም ላይ ሁሉ ላሉ ሰላም ፈላጊ የሰው ዘሮች በሙሉ የተሰጠ ገፀ በረከት ነው ብለዋል፡፡ የሽልማት ሥነሥርዓቱ ኢትዮጵያን በደማቅ ቀለም ማስፃፍ ያስቻለ እንዲሁም በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከፍ ያሉበት መድረክ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፤ ከፍተኛ ክብር ያለውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ሜዳልያና ዲፕሎማ ብሔራዊ ሙዚየም ለማስቀመጥ በመወሰኑ እና ቦታው በመመረጡ የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ በራሳቸውና በስራ ባልደረቦቻቸው ስም ገልፀዋል፡፡
የሰላም ኖቤል ሽልማቱን በተቀበሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መልካም ፍቃድ ሽልማቱን ከብሔራዊ ሙዚየም በተጨማሪ በሰላም ሚኒስትር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደተቀመጠ በመድረኩ ላይ ተነግሯል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ6/2012
ዳግማዊት ግርማ