– ታህሳስ 10 እንደምትመጥቅ ተገለጸ
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የምታመጥቀው ሳተላይት ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዝና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደምትመጥቅም ተገልጿል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ትላንት ኢትዮጵያ የምታመጥቀውን ሳተላይት አስመልክቶ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት፤ አገሪቱ የምታመጥቀው ሳተላይት ለቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያግዝና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ ሳተላይት የማምጠቁ ተግባር አገሪቱ በቴክኖሎጂው ዘርፍ እያሳየች ያለችውን ለውጥ የሚያመላክት ሲሆን፤ አገሪቱ በዘርፉ ያላትን ሚና የሚያጎላ ይሆናል፡፡
ሳተላይት የማምጠቁ ተግባር ለአገሪቱ የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነችው ‹‹ኢ.ቲ.አር.ኤስ.ኤስ1›› የተሰኘችው ሳተላይት ህዳር አስር 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከቻይና ወደ ጠፈር የምታመጥቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሳተላይትዋ በቻይናና በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የለማች መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ወደ ጠፈር የማምጠቁ ሥራ ሲጠናቀቅ ሳተላይቷን የመቆጣጠር እና ሌሎች ስራዎች ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የሚተገበር መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ይህም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማድረግና አገሪቱ ወደፊት በራስ አቅም ሳተላይት አልምታ ማምጠቅ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር ጅማሮ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በማልማቱና በቁጥጥር ስራው ተሳታፊ የሆኑ ባለሙያዎች በቂ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው፤ በሳተላይት ማልማት ሥራ ላይ ከ20 በላይ ኢትዮጵያዊያን ኢንጅነሮች ተሳታፊ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግርን በማድረግ በኩል ያለው ሚና የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በዘርፉ በቂ የሰው ሀይል በማፍራት ረገድ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአገር ውስጥና በውጪ አገር በስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች ስልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ሳተላይቷን ማምጠቅ ለአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያስገኛል ያሉት ዶክተር ሰለሞን፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ክትትል፣ ለመሰረተ ልማት ቁጥጥር፤ ለመዓድን ፍለጋ፤ ለግብርና ስራና ለልዩ ልዩ መሰል አገልግሎቶች የሚውል መሆኑን ዘርዝረዋል፡፡
ሳተላይቷ በሚመጥቅበት ወቅት በቦታው ላይ ለመገኘት ከሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና ከፓርላማ የተወጣጣ የልዑካን ቡድን ወደ ቻይና የሚያመራ መሆኑን የተገለፀ ሲሆን፤ ታህሳስ አስር 2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ላይ የማመንጠቁ ተግባር የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማመንጠቅ ተግባሩን ለመከታተል እንጦጦ በሚገኘው መቆጣጠሪያ ጣቢያ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ6/2012
ተገኝ ብሩ