ባለምርኩዟ ወይዘሮ ሰላም ማሞ በህፃንነት እድሜያቸው የአካባቢው ልጆች አላገለሏቸውም። ከሁሉም ጋር ድንጋይ ፈጭተው አፈር አብኩተው የአካል ድጋፋቸውን እስከ መስበር የደረሰ ልብ የሚያጠፋ ጨዋታ እየተጫወቱ አድገዋል። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲከታተሉም ጓደኛ አላጡም።
አስከፊው መገለልና ብቸኝነት የመጣው ኮሌጅ ሲገቡ ነው። ዕድሜያቸው ከፍ ያሉ ሰዎች ሊጠጓቸው አልወደዱም። መገለሉ ኮሌጅ ላይ አላበቃም፤ ይልቁኑ ተመርቀው ሥራ ሲያፈላልጉ በተግባር በተማሩ ሰዎች ጭምር በሚደርስባቸው የመገለል ድርጊት መጎዳት ጀመሩ።
‹ስወለድ አካል ጉዳተኛ አልነበርኩም። ታላላቆቼ በትከሻቸው እሽኮኮ እያሉ ሲያጫውቱኝ ትኩሳት ጀመረኝ። ህክምና ተወስጄ ቢሻለኝም ከተወለድኩ ከአንድ ዓመት በኋላ እናቴ ገላዬን ስታጥበኝ አንድ እግሬ ልምጥ ሲልባት የአካል ጉዳት እንዳለበኝ ታወቀ።›› የሚሉት ወይዘሮ ሰላም፤ አሁን በኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ማህበር የቦርድ አባል እና አካል ጉዳተኞች ላይ በሚሰራ አንድ ድርጅት ውስጥ ፀሃፊ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው።
‹‹በህይወቴ ፈታኙ ጉዳይ ሥራ ማግኘት ነበር››የሚሉት ወይዘሮ ሰላም፤ በወቅቱ በዲፕሎማ በቢዝነስ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ቢመረቁም ከእርሳቸው ጋር እንደተማሩት የአካል ጉዳት እንደሌለባቸው ሰዎች በቀላሉ ሥራ ማግኘት ከብዷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ተቋማት የሥራ ቅጥር ሲያወጡ ለማመልከት በሚሄዱበት ጊዜ ‹‹አይ ላንቺ አይሆንም›› ከማለት ጀምሮ፤ በሰጡት የትምህርት ማስረጃ ላይ ‹‹የአካል ጉዳተኛ ናት›› ብሎ በመፃፍ እንዳይቀጠሩ ይፈፀምባቸው የነበረው ተግባር እጅግ አማሯቸው እንደነበር ይገልፃሉ።
‹‹ የአካል ጉዳት ያልነበረባቸውና በብቃት የምበልጣቸው አብረውኝ የተማሩት ሰዎች ሥራ ሲያገኙ እኔ ሥራ አለማግኘቴ ተስፋ እስከ መቁረጥ አድርሶኝ ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ ሰላም፤ በመጨረሻም ‹‹በፈቃደኝነት ያለ ክፍያ ላገልግል›› ብለው በመስራታቸው ብቃታቸውን አይቶ ተቋሙ እንደቀጠራቸው ይናገራሉ። አሁንም ድረስ የእንቅስቃሴ አካል ጉዳት ያለባቸው ብቻ ሳይሆኑ መስማት የተሳናቸው፤ አይነ ስውራን እና ሌሎችም አካል ጉዳተኞች ስራ እያገኙ አይደለም ይላሉ።
‹‹በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት አልተሰጠም ከሚያስብለን ምክንያት አንዱ ቁጥራችን በትክክል አለመታወቁ ነው። ይህ ደግሞ ተገቢው በጀት እንዳይያዝና በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የተሳትፎ ድርሻችን እንዳይለይ አድርጎል›› የሚሉት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 የሚሰሩትና በዊልቸር የሚንቀሳቀሱት ወይዘሮ ዘነበች ጌታነህ ናቸው።
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን መፈረም፤ የተለያዩ የሥራ ቅጥርና የህንፃ ግንባታን በሚመለከት ህግ የማውጣት ተግባር መፈፀማቸው የተወሰኑ መሻሻሎች መኖራቸውን የሚያሳዩ ናቸው የሚሉት ወይዘሮ ዘነበች፤ አካል ጉዳተኞች በተለያየ መልኩ በማህበር ተደራጅተው መብታቸውን እንዲጠይቁ እገዛ እየተደረገ መሆኑን፤ መሰረተ ልማቶችም ምቹ መሆን መጀመራቸውን እና ለውጦች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ሆኖም ግን አሁንም አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት እያገኙ ነው ለማለት እንደሚያዳግት ይጠቅሳሉ።
በአሃዱ ሬዲዮ ‹‹አዲስ መንገድ›› የተሰኘ የአካል ጉዳተኞች ፕሮግራም የሚያዘጋጀው ባለምርኩዙ ተስፋዬ ገብረማርያም በበኩሉ፤ አካል ጉዳተኞችን እናካትታለን ከሚል ቃል ውጪ በተግባር የሚሠራው እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ‹‹ እንደውም ኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የምትመች አገር አይደለችም›› ይላል።
የብዙዎቹ ህይወት ሲታይ የኢኮኖሚ ደረጃቸው፣ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እና ተጠቃሚነታቸው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። አዲስ አበባ ላይ የተወሰኑ ጅማሬዎች አሉ። ክልሎች ላይ ግን ለአብነት 27ኛው የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል የተከበረባት በኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ የአካል ጉዳተኞች ዊልቸር አጥተው በከመነዳሪ እየተንፏቀቁ ሰዎች በጫማ የሚረግጡትን መሬት እነርሱ በሚበሉበት እጃቸው እየሄዱበት ማየት በራሱ ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኛ ሆኖ መኖር እጅግ ከባድ መሆኑን ማሳያ ነው በማለት ይናገራል።
‹‹ማህበራዊ ተቋማት እታች ድረስ ወርደው እየሰሩ አይደለም። ብዙ ጊዜ የተሰሩ ጥቂት ነገሮችን እንደ ትልቅ ጉዳይ የማስወራት ሁኔታ ይስተዋላል። በእርግጥ መንግስት ላይ ብቻ በማተኮር ወደ ላይ መንጠልጠል ሳይሆን ከታች ያሉት አመራሮች ምን ያህል አካታችነትን እየተገበሩት ነው? እኩል ተሳታፊ እኩል ተጠቃሚ ማድረግ አለብን ብለው ያስባሉ? የሚለው ያጠያይቃል›› ይላሉ።
የአካል ጉዳተኞች የቤተሰብ እገዛ ታክሎበት ተምረው ከአካል ጉዳተኛ ካልሆኑት በላይ መስራት ይችላሉ። ነገር ግን ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ሲወጣ መስፈርቱ ‹‹ሙሉ ጤነኛ የሆነ›› እያሉ አካል ጉዳተኝነትን ከበሽተኝነት ጋር እያቀላቀሉ ‹‹ቅጥር አንፈፅምም›› የሚሉ ብዙዎች መኖራቸውን በመጠቆም፤ አካል ጉዳተኞች በዲፕሎማም ሆነ በዲግሪ ተመርቀው ከፍተኛ ብቃት ቢኖራቸውም በተለያየ መልኩ የእነርሱን ሥራ ፈልገው በራቸውን የሚከፍቱ አይገኙም። በመንግስት ተቋማት በተወሰነ ደረጃ አይነስውራኖችን መቅጠር ቢጀመርም፤ የግል ዘርፉ ላይ ግን አብዛኛዎቹ አካል ጉዳተኞችን እንደማይቀጥሩ ይናገራል።
‹‹እምቅ አቅም እንዳላቸው እና አምራች መሆን እንደሚችሉ የማይረዱ ብዙ ናቸው።›› የሚለው ጋዜጠኛ ተስፋዬ፤ ጓደኞቹ የጋዜጠኝነት የትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም ተሯሩጣችሁ መስራት አትችሉም በሚል ሰበብ ስራ ማግኘት አለመቻላቸውን ይገልፃል። የሚያስገርመው ጉዳይ ደግሞ የአይነስውራን ማህበር፣ የሴት አካል ጉዳተኞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር እና ሌሎችም ስለአካል ጉዳተኞች እንሰራለን የሚሉ ማህበራት በዚህ በኩል የአካል ጉዳተኞችን መብት እና ጥቅም እያስከበሩ አይደለም ይላል።
በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ቁጥራቸው ባይታወቅም ትንሽ አይደሉም፤ በሚሊየን የሚቆጠር አካል ጉዳተኛ መኖሩ አይካድም። ነገር ግን እምቅ አቅማቸው በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል አልተደረገም። ተገልለዋል። የህግ ባለሞያዎች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ሰዓሊያንና በሌሎችም ሞያ ላይ የተሰማሩ እና በጥሰው መውጣት የቻሉ ቢኖሩም፤ ሌሎቹን ማሳተፍ ቢቻል ፤ህግ ላይ ያሉ ጉዳዮች ቢተገበሩ እና መሰረተ ልማቱ ምቹ ቢሆን አካል ጉዳተኞች ኢትዮጵያን በአግባቡ መጥቀም ይቻሉ እንደነበርና አቅማቸው እየባከነ እንደሆነም ነው ጋዜጠኛ ተስፋዬ የተናገረው።
በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ህዝብ 17 በመቶ አካል ጉዳተኛ እንደሆነ፣90 በመቶ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ስራ እንደማያገኙና 80 በመቶ ህጻናት ደግሞ ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ መሆናቸው በመስኩ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ6/2012
ምህረት ሞገስ