አዲስ አበባ፡- የታክሲ አሽከርካሪዎች የአገር ገፅታን በሚገነባ መልኩ አገልግሎት በመስጠት በአገሪቷ እድገት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጠየቀ።
የታክሲዎች ማህበር የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት አበረከተ።
የታክሲዎች ማህበር ለዝቅተኛ ህብረተሰብ ተደራሽ መሆን በሚል ትናንት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ በከተማዋ የሚገኙ ታክሲዎች ህብረተሰቡን ከማገልገል በዘለለ ወደ አገር የሚገባ የውጭ ዜጋን በመንከባከብ እና በኢትዮጵያ የመቆያ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ በማመቻቸት በአገሪቱ እድገት ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
‹‹በቅርቡ አዳዲስ ታክሲዎች ይገባሉ›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ የውጭ አገር ዜጋ ወደ አገር ሲገባ በሚሰማውና በሚያየው ነገር ተበሳጭቶ የቆይታ ጊዜውን እንዳያሳጥር መልካም አገልግሎት በመስጠትና መረጃዎችን በመንገር የቆይታ ጊዜውን አራዝሞ እንዲሄድ በማድረግ አገራቸውን በቱሪዝሙ ዘርፍ አትራፊ እንድትሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።
ቀደም ሲል በአገሪቱ የታክሲ አሽከርካሪዎች በፖለቲካና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰው፤ ወደ ፊትም እራሳቸውን የከተማዋ ሞተር በማድረግ ለውጭና ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የንግድ እንቅስቃሴ ያለ ታክሲ አይታሰብም ካሉ በኋላ፤ ያለባቸውን ትልቅ ሃላፊነት በመገንዘብ ለከተማዋ እድገትና ብልፅግና ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ተናግረዋል። በተለይ ለውጭ አገር ዜጎች የሚያኮራ መስተንግዶ በመስጠት የቱሪዝሙ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ከሚያበረክተው አነስተኛ አስተዋፅኦ እንዲወጣ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።
አቶ ኦባንግ አክለውም፤ በዘርና በጎሳ ከመጋጨት ይልቅ ሁሉም እኩል ሰው መሆኑን በመገንዘብ፤ በሥራ ህብረት በመፍጠር የተገኘውን ለውጥ በፖለቲካውም ሆነ በልማቱ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የታክሲዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበባው ካሳ እንደተናገሩት፤ አሽከርካሪዎች ለአገር ከሚያበረክቱት ዕድገት በተጨማሪ ሰዎችን ሲያገለግሉ ስነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ ማሽከርከር አለባቸው። አገልግሎት ሲሰጡ ህሙማንንና አቅመ ደካሞችን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል።
‹‹በቀጣይ ለዝቅተኛ የማህበረሰብ ክፍል በአነስተኛ ዋጋና በቀዳሚነት ለማገልገል እቅድ ይዘናል›› ያሉት አቶ አበባው፤ መታገዝ ለሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አክለውም አገሪቱ በትክክለኛ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የኖቤል ሽልማቱ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት አቶ አበባው፤ ለውጡ ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ አመልክተዋል።
በዕለቱ የታክሲ ማህበሩ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን አስመልክቶ ሽልማት ያቀረቡ ሲሆን፤ ተወካያቸው ተገኝተው ሽልማቱን ተቀብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ6/2012
ሞገስ ፀጋዬ