– ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል የፕላስቲክ ከረጢት 75 በመቶ ደርሷል
– በዓመት ከ200 እስከ 250 ሺህ ቶን የፕላስቲክ ምርት ቆሻሻ ነው
አዲስ አበባ፡- የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) አመራረትና የቆይታ ጊዜ አስመልክቶ የወጣውን አዋጅ መሰረት አድርጎ የሚያመርት አንድም ፋብሪካ ባለመኖሩ በአካባቢና በሰዎች ላይ የከፋ አደጋ እያስከተለ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽኑ አስታወቀ፡፡ በዓመት ከ200 እስከ 250 ሺህ ቶን የፕላስቲክ ምርት ቆሻሻ ነው።
የኮሚሽኑ የደረቅና አደገኛ ቆሻሻ ህግ ተከባሪነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በፕላስቲክ ከረጢቶች ሊደርስ የሚችለውን ብክለት እና ብክነት ለማስቀረት የደረቅ ቆሻሻ አዋጅ 513/99 ቢወጣም እስካሁን ድረስ አንድም ፋብሪካ አዋጁን መሰረት አድርጎ እያመረተ አይደለም።
በመሆኑም የሚመረተው ፕላስቲክ ውፍረቱ ከ0 ነጥብ 03 ሚሊ ሜትር በታች እና በስብሶ ከአፈር ጋር የሚዋሀድ አይደለም።
‹‹የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት ወይም ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ፈቃድ የሚሰጠው ውፍረቱ ከ0 ነጥብ 03 ሚሊሜትር በላይ የሆነና በስብሶ በመዋሃድ የአፈር ለምነትን የማያዛባ መሆኑ ሲረጋገጥ ነው›› በሚል በአዋጁ ላይ ቢቀመጥም በአገር ደረጃ ይህንን ህግ ተከትሎ የሚያመርት አንድም ድርጅት የለም። በዚህም ምክንያት በአገር ላይ የአካባቢ ብክለት አስከትሏል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አዋጁ የፕላስቲክ ጥንካሬና ውፍረት እንዲሁም በአፈር ውስጥ መበስበስ እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም መስፈርቱን አሟልተው የሚሰሩና ፈቃድ ያገኙ አምራቾች የሉም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ልዩ ልዩ የፕላስቲክ ምርቶችን በህጋዊ መንገድ እናመርታለን በሚል ሽፋን በህገወጥ መንገድ የፕላስቲክ ከረጢት የሚያመርቱ ተበራክተዋል፡፡ ይህም የአካባቢ ብክለትን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንዲመጣ አድርጓል፡፡
በአገር ደረጃ ማንኛውም የፕላስቲክ ከረጢት አምራች ህጋዊ ፈቃድ እንዳልተሰጠው የሚያነሱት አቶ ግርማ፤ ልዩ ልዩ ፕላስቲክ አምራቾች ላይ ድንገተኛ ፍተሻ በሚደረግበት ጊዜ የሚጠቀሙት ግብዓት ተመሳሳይ ስለሆነ በህጉ መሰረት እየሰሩ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ በዚህም ህጋዊና ህገወጦችን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ ችግር ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡
ድንገተኛ ፍተሻ የሚነገርለትን ያህል ባይሆንም ውጤት እያመጣ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ግርማ፤ አምራቾቹ እንዲያስተካክሉ ሲነገራቸው ዘርፍ እስከመቀየርና ስራውን እስከማቆም መድረሳቸውን ያስረዳሉ፡፡
ፕላስቲክ ከረጢቶች ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውለው በቆሻሻነት የመወገዳቸው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ የሚናገሩት አቶ ግርማ፤ በእያንዳንዱ ቤት ከሚመነጨው ቆሻሻ ውስጥ ከ9 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው ለአንድ ጊዜ ጥቅም ብቻ የሚውል ፕላስቲክ ከረጢት ነው፡፡ እንደ አገር ደግሞ ከ200 እስከ 250 ሺህ ቶን የሚሆነው ቆሻሻ የፕላስቲክ ምርት መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።
የፕላስቲክ ከረጢት በአካባቢ ላይ እያስከተለ ያለውን ብክለት ለመከላከል ጠንካራ ህግ ማውጣት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ግርማ፤ 75 በመቶ የሚሆነው ለአንድ ጊዜ አገልግሎት ብቻ የሚውልና በአንድ ቀን ውስጥ የሚወጣ የፕላስቲክ ቆሻሻ መሆኑ እንደ አገር አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ አሳሳቢነቱን በማየትም ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ረቂቅ ህግ አውጥቶ ለምክር ቤት ማቅረቡን ገልጸው ከመንግስት በኩል አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።ምላሹ ካልፈጠነና ከአዋጁ ውጪ የሚሰሩ አምራቾች ካልታገዱ አገር በተለያዩ የጤና ችግሮች ውስጥ መውደቋ አይቀሬ መሆኑን አሳስበዋል፡፡
በዓለም ላይ እስከ አራት በመቶ የሚሆነው የነዳጅ ድፍድፍ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን ለማምረቻ በጥሬ እቃነት ጥቅም ላይ ይውላል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው