አዲስ አበባ፡- ሃያ ሁለት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከግብር በፊት 18 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ማትረፋቸውን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ወንዳፍራሽ አሰፋ፤ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2012 ሩብ ዓመት ድርጅቶች 84 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅደው 75 ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ሰብስበዋል።
በሩብ ዓመቱ ከሚሰበስቡት ገቢ 18 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት አቅደው ከግብር በፊት 18 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር አግኝተዋል። አፈጻጸማቸውም ከእቅዳቸው በገቢ 90 በመቶ እንዲሁም በትርፍ 96 በመቶውን መሆኑን ተናግረዋል። የዘንድሮው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በገቢ የ16 በመቶ በትርፍ የ38 በመቶ ብልጫ አለው።
ከተገኘው ትርፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 6 ነጥብ1 ቢሊዮን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 5 ነጥብ3 ቢሊዮን፣ ኢትዮ- ቴሊኮም 5 ቢሊዮን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት 650 ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 251 ሚሊዮን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 214 ሚሊዮን ብር አትርፈዋል።
የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽንን ጨምሮ 13ቱ ድርጅቶች ደግሞ 585 ሚሊየን ብር ያተረፉ ሲሆን ቀሪዎቹ ሦስት ድርጅቶች ኪሳራ ውስጥ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ወንዳፍራሽ ማብራሪያ ፤ከሃያ ሁለቱ የልማት ድርጅቶች መካከል ዘጠኙ የልማት ድርጅቶች በውጭ ምንዛሬ ጭምር ሽያጭ የሚያካሂዱ ናቸው። ከሚያካሄዱት ሽያጭም 3 ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 3 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ይህም የዕቅዳቸውን 86 በመቶ ነው ።
ከልማት ድርጅቶቹ መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እቅዳቸውን ከመቶ በመቶ በላይ አሳክተዋል። ባለፈው ዓመት ኪሳራ ውስጥ የነበሩት የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ከኪሰራ ወጥተው ትርፋማ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።
ከልማት ድርጅቶቹ መካከል በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩት ድርጅቶች በኪሳራ ውስጥ መሆናቸው የሩብ ዓመቱን ዕቅድ ላለማሳካት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ የፐልፕና የወረቀት ፋብሪካ ባጋጠመው የውጭ ምንዛሬ ችግርና በሌሎች ምክንያቶች ኪሳራ ውስጥ መሆኑ ሌላው ለአፈጻጸሙ ጉድለት ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል። እቅዱ እንዳይሳካ ሌላው ምክንያት ትርፋማ የሆኑትም በእቅዳቸው ልክ ገቢና ትርፍ አለማግኘታቸውን ዳይሬክተሩ በምክንያትነት አስቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ