አዲስ አበባ፡- የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደም አፍሰው ህይወትን የሚያጠፉ ሳይሆን ደም ለግሰው የወገናቸውን ህይወት መታደግ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው ደም የለገሱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራኖች አስታወቁ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ‹‹social marketing for abetter life›› በሚል መሪ ቃል ከጎንደር ደም ባንክ ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር በተካሄደው የደም ልገሳ ፕሮግራም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የማርኬቲንግ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር አስቻለው አዳነ እንደገለጹት፤ተማሪዎች በጉልበትም በአስተሳሰብም አቅም ስላላቸው ለወገን ቀድመው ደራሽ መሆን አለባቸው፡፡
በተሳሳተ መረጃ የሰውን ደም ከማፍሰስ ይልቅ ደም በመለገስ የሰው ህይወትን መታደግ መቻል አለባቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ከግንዛቤ ማስጨበጥ በዘለለ በየሦስት ወሩ የደም ልገሳ ፕሮግራም በማዘጋጀት የተማሪዎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከርና ለወገን ደራሽነቱን እያረጋገጠ ነው፡፡
በደም እጥረት የሚሞቱ ሰዎችን ሊያድን የሚችል የሰው አቅም ቢኖርም በአመለካከት ችግርና በቸልተኝነት ምክንያት በሀገራችን በደም እጥረት የተነሳ በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን እንደሚያጡ ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ተሰማ እንዳልካቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ደም መለገስ ሰብአዊነት ነው፡፡ ወጣቱ ከጠባብ አስተሳሰብ ተላቆ ደም በመለገስ ኢትዮጵያዊነትን ማጠናከር አለበት፡፡
‹‹የኔ የሚል በበዛበት ወቅት የምለግሰው ደም ከዘሬ፣ ከኃይማኖቴና ከቋንቋዬ ውጭ ላለ ሰው እንደሚሰጥና ህይወት እንደሚታደግ ሳስብ ከፍተኛ የሆነ ደስታ ይሰማኛል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወጣቱም የሀሳብ ልዩነቱን ደም በማፍሰስ ሳይሆን ደም በመለገስ፣ መሰል ማህበራዊ ስራዎችን በመስራት፣ በውይይትና በክርክር በማጥበብ የሀገር አለኝታነቱን ማረጋገጥ አለበት ብሏል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የአካውንቲንግ ተማሪ መኩሪያው አዳነ እንደሚለው፤ የማንግባባቸውን ነገሮች አንድ በሚያደርጉን ስራዎች ማጥበብ እንችላለን፡፡ ተማሪዎች ደም በመለገስ በመላው ኢትዮጵያ የደም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁሉ መድረስ አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ፊት ትልቅ ኃላፊነት ስላለባቸው የማያግባቡ ነገሮችን ከማተኮር ይልቅ የምንግባባቸውን በማጠናከር አንድ መሆን አለብን ብሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2012
ሞገስ ፀጋዬ