አዲስ አበባ፡- በጎንደር ከተማ ፋሲል ግንብ (የነገሥታት ግቢ) እየተባለ የሚታወቀው ታሪካዊ ቅርስ በኃላፊዎች ክልከላ በአገር ውስጥና በውጪ አገር ጎብኚዎች እንዳይታይና መጉላላት እንዲፈጠር እየተደረገ መሆኑን የአስጎብኚዎች ማህበር አስታወቀ።
የጎንደር አስጎብኝዎች ማህበር አባል ወጣት ኑር ሁሴን አጋዥ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፀው፤ በቱሪስት መስህብነቱ በቀዳሚነት የሚታወቀው የፋሲል ግንብ በተለያዩ ምክንያቶች በቅርብ አመራሮች ትዕዛዝ እንዳይጎበኝ እየተደረገ ነው። በርካታ ጎብኚዎች ገንዘብ ከፍለውና ጊዜያቸውን አባክነው በቦታው ቢገኙም ሰዓት ደርሷል በሚል እንዲወጡ ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት እንዲመላለሱና ላልተገባ ወጪም እንዲዳረጉ ሆነዋል። ይህም ሁኔታ ቱሪስቶች እንዲቆዩና ተመልሰው እንዲመጡ ከማድረግ አኳያ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርሱ ከፍተኛ ገቢ የማስገኘት ዕድል ቢኖረውም ምንም አይነት ጥገና እየተደረገለት ባለመሆኑና በእኔነት ስሜት የሚቆጣጠረው አካል ባለመኖሩ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እየተገኘ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
‹‹ለእድሳት በሚል በቅርሱ ላይ የተረበረበው እንጨት ለእይታ ማራኪ እንዳይሆን ከማድረጉም በላይ ውሀ ወደ ውስጥ በማስረግ ቅርሱ እንዲጎዳ አድርጎታል። ›› የሚለው ወጣት ኑርሁሴን፤ ከዚህ በፊት በዙሪያው ምንም አይነት ተሽከርካሪ እንዳይሄድ የሚል መመሪያ ቢተላለፍም ተግባራዊ ባለመሆኑ በፋሲል ግቢ የሚገኙ በርካታ ግንቦች እየተሰነጣጠቁ መሆኑን ተናግሯል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳይታወቅ በቤተ መንግሥት ውስጥና ውጭ የሚገኙ ዘመን የተሻገሩ ‹‹ክብ ቤቶች›› በሚል መጠሪያ የሚታወቁት መኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ የሚል ትዕዛዝ ተላልፏል ብሏል።
የጎንደር አስጎብኝዎች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ማስረሻ ፈንታው በበኩሉ እንደገለፀው፤ ቅርሱ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው። ብዙ ጊዜ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ባገኙትና በተመቻቸው ሰዓት መጎብኘት ይፈልጋሉ። ቢሆንም ግን በፈለጉት ጊዜ ለመጎብኘት አመቺ ባለመሆኑ ብዙ ገቢ ከመቅረቱም በላይ በርካታ ሰዎች ይጉላላሉ ሲል ተናግሯል።
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የማይንቀሳቀስ ቅርስ ልማት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፀሐይ እሸቴ የቀረበውን ቅሬታ አስመልክተው በሰጡት ምላሽ፤ ቅርሱን በተመለከተ በርካታ ችግሮች እንዳሉ አምነዋል።የቀረበውም ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልጸው ነገር ግን በግቢው ውስጥ የሚፈርሱ ቤቶች የሉም። ሆኖም በሚፈለገው መንገድ ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። በተለይ ደግሞ የጎብኝዎች መጉላላት ከዚህ ቀደም የነበረ ቢሆንም በወቅታዊ የፀጥታ ችግር የተነሳ አሁን ላይ ማባባሱን አስታውቀዋል።
“ግንቡን ለማደስ የበረንዳ መቀየሪያ የሚሆን እንጨት በመጥፋቱ እስካሁን ሳይታደስ ቀርቷል። በፋሲል ግቢ ዙሪያ ያሉ መንገዶች ለቅርሱ ደህንነት ሲባል በተለዋጭ መንገድ እንዲተኩ ቢባልም ቅንጅት ባለመኖሩ ተግባራዊ መሆን አልተቻለም። ይህም በቅርሱ ላይ ከፍተኛ ችግር እያደረሰ ነው” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 5/2012
ሞገስ ፀጋዬ