አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያውያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ትግል ሁሉም እኩል የሆኑባት ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሆነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። በዓሉ ለዘመናት ሳይተዋወቁ የኖሩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲተዋወቁ እና ሁለገብ ትስስራቸው እንዲጠናከር መልካም ዕድል መፍጠሩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ትናንት 14ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ በተካሄደ ሲምፖዚየም ላይ በአደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የኢትዮጵያውያን ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ትግል ሁሉም እኩል የሆኑባት ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሆነ መግለፃቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግ ቧል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው የመሰረቱት ህገመንግሥት እንደሚያረጋግጠው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የታገሉት ኢትዮጵያ ውስጥ በእኩልነት ለመኖር ነው። አንዱ የሚበላበት ሌላው የበይ ተመልካች የሚሆንባት አገርን ለመፍጠር ሳይሆን፤ ሁሉም ለፍቶ ጥሮ ግሮ የሚኖርባት አገር እንድትሆን ነው። ይህም እኩልነት እውን የሚሆነው እያንዳንዱ ዜጋ ሁለተኛ ዜጋ ሳይሆን እንደ አንደኛ ዜጋ በየትኛውም ደረጃ በብቃቱ ተወዳድሮ የመሥራት እና የመምራት ዕድል ማግኘት መንቀሳቀስ ሲችል መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም እኩል የሆኑባት አገር እንዳትሆን ሲደረግ የነበረው ጥረት ኢትዮጵያን ወደኋላ ያስቀረ እና አደገኛ ልምምድ መሆኑን በመገንዘብ ያንን ተግባር ለማስቀረትና በጋራ አገሪቱን ለማበልጸግ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሲሰባሰቡ ሊታዩ እና ሊነጋገሩ፤ አንዱ ከሌላው ሊማራቸው የሚገባ ትወፊቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ስነምግባሮች ስላሉ ሲገናኙ ችግር እና ሮሮ ብቻ ማውራት ሳይሆን መልካም ልምዶችን መካፈል እንዱ ከሌላው የሚማርበት እና አብሮ መሆን ፀጋ መሆኑ ሊታስብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዴሞክራሲን ማስፈን ቀላል ተግባር አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ የጅማሬው ሥራ የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆን፣ ጉዞን ወደዚያ ማድረግ ለፍሬ የሚያበቃ ነው ብለዋል። ወደ ብልጽግና የሚደረገው ጉዞ በመከባበር፣ መቻቻል እና የትዕግስት መልህቅ ከጠነከረ እነዚህኑ ፍሬዎች ማጨድ ይቻላል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ህገመንግሥቱ የፀደቀበትን የብር እዮበልዩ በዓልን እና ለ14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል እንኳን አደረሰን ሲሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ህገመንግሥታዊ ዋስትና የተረጋገጠበት ቀን የሚዘከርበት መሆኑን አውስተው፤ በዓሉ ለዘመናት ሳይተዋወቁ የኖሩ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲተዋወቁ እና ሁለገብ ትስስራቸው እንዲጠናከር መልካም ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
በቀጣይም ፋይዳና ጥቅሙን በመጠበቅ የሚነሱ ክፍተቶችን በመፍታት በዓሉ በየዓመቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በበዓሉ ባለቤቶች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል። መድረኩ ህዝቦች ከሚለያዩዋቸው ጥቂት ነገሮች ይልቅ የሚያስተሳስራቸው በርካታ ታሪክና ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግና የተገነባውን ህገመንግሥታዊ ቃልኪዳንን ዳግም ለማደስ ምቹ አጋጣሚ እንደሚሆን ይታመናል ብለዋል።
የበዓሉ አስተናጋጅ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ሁለም ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተገናኝተው ራሳቸውን የሚያሳዩበት እና ስለ ጋራ ቤታችን እንደቤተሰብ የምናወራበትን በዓል እንድናዘጋጅ ስለተመረጥን እናመሰግናለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች በህገመንግሥቱ የተቀመጡ ትን እኩልነት፣ ነፃነትና ወንድማማችነት ተተግብሮ በሁሉም መስክ ያሉ ችግሮች ፤ የፌዴራል ስርዓቱ እንዲጠናከር እና ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ህፀፆች እና ችግሮች አሁን ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ እንዲፈቱ ሁሉም እራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን በጋራ ደግሞ እንደ አገር አንድ ቤትን በጋራ የማስተዳደር ተግባር በሙሉ ኃላፊነት በመወጣት ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ እኩልነትና ነፃነት እንዲረጋገጥባት ለማድረግ የለውጥ ሂደቱን በህገመንግሥታዊ ማእቀፉ አጠናክሮ ማስቀጥል ላይ እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012
ምህረት ሞገስ