14ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ‹‹ህገ መንግሥታዊ ቃልኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መልዕክት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት ይከበራል። በዓሉ ለሃገራዊ አንድነትና መግባባት መፍጠር በሚያስችል መከበር እንዳለበት ይገለጻል።
በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረስላሤ እንደሚገልጹት፤ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ እሴታቸውን፣ ትውፊታቸውን እንዲሁም ወግና ስርዓታቸውን ለመላ ኢትዮጵያዊያን ብሎም ለዓለም ህዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ ነው። በመሆኑም መድረኩ ከወረቀት በዘለለ ብዝሓነት ውበት መሆኑ በተግባር የሚታይበት ቀን ነው።
መድረኩ ህብረተሰቡን ለልማት፣ ለአንድነትና ለሰላም ለማነሳሳት፤ በህገ መንግሥቱና በፌዴራል መንግሥቱ ስርዓት ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ ለአገር ውስጥ ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት መስፋፋትና ዕድገት፤ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ለከተሞች መነቃቃት የራሱን ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በአጠቃላይ በዓሉ በአለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ መከበሩ ለብሄር ብሄረሰቦች ያለው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ በፖሊሲና ልማት ምርምር ማዕከል ተመራማሪ እና እስኩልኦፍ ገቨርናንስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ስተዲ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ፤ በአገሪቱ 86 ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሉ። ነገርግን ከእነዚህ መካከል እንደአገር በዋናነት የሚታወቀው የሦስት ወይም የአራት ብሄረሰቦች ባህል፣ ቋንቋ፣ እሴት እንዲሁም ወግና ስርዓት ነው። ይህም የሆነው የሌሎቹን ብሄሮች ባህልና ወግ የማውቅ እና የማሳወቅ አገራዊ ዕድል ባለመኖሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊነት ሲባል የእነዚህ የሦስት ወይም የአራት ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህል፣ እሴት እና ትውፊት ብቻ ጎልቶ ይታያል የሚሉት ዶክተር የሺጥላ፤ ነገርግን የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ከጀመረ በኋላ ሌሎችም ብሄረሰቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና እሴታቸውን ለመላ ኢትዮጵያዊያን ብሎም ለዓለም ህዝብ እንዲያስተዋውቁ ዕድል ፈጥሯል። ከዚህ ባሻገር በአንድ መድረክ ተገናኝተው ያላቸውን ባህል፣ ቋንቋ እና እሴት አንዱ የሌላውን እንዲያውቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። በአጠቃላይ በዓሉ የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊነት አጉልቶ የሚያሳይ መነጸር መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በዓሉ በአለፉት ዓመታት በአገሪቱ መከበሩ ለህዝቦች አንድነትና ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላበረከተ የሚናገሩት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ናቸው። እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ እራሱን ከሴራ ፖለቲካ አጽድቶ መድረኩን በሐቅ አንዱ ብሄር የሌላውን ብሄር ባህል እና ወግ አውቆ፤ የጋራ ብሄራዊ ማንነት በመገንባት ተቻችሎና ተከባብሮ እንዲኖር አላደረገም። ይልቁንም መድረኩ በየዓመቱ ድራማ የሚታይበት እንዲሁም ስልጣን ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች የፖለቲካ ተቀባይነታቸውን ለመገንባት የሚጠቀሙበት ነው።
በመሆኑም በዓሉ በአለፉት ዓመታት ሲከበር የአገሪቱ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በሐቅ አንድነታቸውን ለመጠበቅ የተቀራረቡበት፣ ለመቀራረብ የቻሉበት፣ ችለውም ደግሞ የተሻለ ሰላምና መረጋገት ያመጡበት ሁኔታ አለመኖሩን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ በዚህ መድረክ ከፖለቲካ ጨዋታ የዘለለ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል መሬት ላይ የሚታይ ሥራ ባለመሠራቱ፤ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተከባብረው የሚኖሩ ህዝቦች አሁን ላይ አንዱ አንዱን እየገፋ ብዙ የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል። እንዲሁም ፖለቲካኞች ቃል የገቡትን የህዝቦች አንድነት ሳያስጠብቁ በፖለቲካ ሽፋን ‹‹ህዝቦች ሳይቀራርቡ ተቀራርበዋል፤ ልዩነታቸውን ሳያጠቡ አጥብበዋል›› በማለት በየዓመቱ ድብብቆሽ በመጫወት አገሪቱ ይበልጥ አደጋ እንደተጋረጠባት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አገሪቱ የገባችበት ቀውስ መሰረታዊ ችግሩ ብሄራዊ ማንነት አለመፈጠሩ ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር የሺጥላ፤ በዓሉ በአለፉት 13 ዓመታት ሲከበር ህብረ ብሄራዊነትን ከማንጸባረቅ ባሻገር አገራዊ አንድነትን ከመገንባት አኳያ ውሃ የሚያነሳ ሥራ አልተሠራም።
ስለዚህ አገራዊ አንድነትን የሚያስጠብቁ የጋራ እሴት ባለመገንባቱ በዓሉ የዕድሜውን ያህል ለአገራዊ አንድነት ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ አላበረከተም። እንዲሁም በዓሉ ይበልጥ ልዩነት ላይ በማተኮሩ ብሄራዊ አንድነትና መግባበት ተሸርሽሯል። በዚህም በአገሪቱ አገራዊ አንድነት ጥያቄ ውስጥ በመግባቱ አገሪቱን አሁን ለገባችበት ቀውስ ዳርጓታል ይላሉ።
ህብረ ብሄራዊነትን ከማንጸባረቅ ባሻገር አንድነትን ይበልጥ አስጠብቆ ከመሄድ አኳያ በቂ ሥራ አለመሠራቱን የሚናገሩት አቶ ገብሩ፤ በዓሉን ተገን በማድረግ በህገ መንግሥቱና በፌዴራል ስርዓቱ ዙሪያ ለዜጎች ግንዛቤ ከመፍጠር፤ የፌዴራል መንግሥቱ ከታችኛው መዋቅር ጋር ተናቦ በዓሉን ከማክበር አኳያ እና በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተጀመሩ አንዳንድ መሰረተ ልማቶችን አጠናክሮ ከማስቀጠል አንጻር በአለፉት ዓመታት የተስተዋሉ ክፍተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከአሁን በፊት በዓሉ ሲከበር የተስተዋሉ ክፍተቶች በጥናት ተደግፎ በማስተካከል በቀጣይ አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር እንዲሁም የሁሉንም ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ መልኩ እንደሚከበር አቶ ገብሩ ጠቁመዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር የሺጥላ በበኩላቸው፤ በዓሉ ለወደፊት ሲከበር ከፖለቲካ ፍጆታና ከጭፈራ በዘለለ በየብሄረሰቡ እንደ ባህል አምባሳደር የሚታዩ ሰዎች እየተገናኙ ሃሳባቸውን የሚለዋወጡበት፣ ልዩነታቸውን እያረቁ ይበልጥ አገራዊ አንድነትን የሚገነቡበት መድረክ ሊሆን ይገባል። እንዲሁም በመድረኩ የሚሳተፉ ሰዎች ማህበረሰቡን የሚወክሉ ተሰሚነት ያላቸው የአገር ሽማግሌዎች የሚሳተፉበት ቢሆን፤ አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።
በተጨማሪም ለወደፊት የሚዘጋጁ መድረኮች የየብሄረሰቡ ምሁራን ተገናኝተው የምርምር ሥራዎቻቸውን የሚለዋወጡበት፤ አዳዲስ ሃሳቦችንና ግኝቶችን የሚካፈሉበት፤ የተደራጀ ምሁራዊ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱበት ሊሆን ይገባል። አንዱ ብሄር ከሌላው የተሳሰረበት ማህበራዊ ገመድ ምንድነው የሚለውን በጥናት ተደግፎ የሚቀርብበት መድረክ መሆንም አለበት። በአጠቃላይ መድረኩ በልዩነት ላይ አንድነት የሚጠናከርበት ሥራ የሚሠራበት መድረክ ሆኖ በዓሉ ለወደፊት ሊከበር እንደሚገባ ረዳት ፕሮፌሰር የሺጥላ መክረዋል።
ፕሮፌሰር መራራ በበኩላቸው፤ መጀመሪያ ፖለቲከኞች በከፋፍለህ ግዛ ሴራ ህዝቡን እርስ በእርስ ከማጋጨት እራሳቸውን መቆጠብ እና በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ፈትተው ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ ይገባቸዋል። ይህ ሳይሆን በየዓመቱ ህዝቡን እየሰበሰቡ ድራማ መሥራቱ ከፖለቲካ ፍጆታ ያለፈ ለአገር አንድነትና ለህዝቦች ሰላም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የለም።
ስለዚህ በዓሉ ለወደፊት ሲከበር አመራሮች ከከፋፍለህ ግዛ ሴራ ወጥተው በተግባር የህዝቦች ግንኙነት በአዲስ መልክ ታድሶ ብሄራዊ መግባባት እንዲኖራቸው በሙሉ ልብ መሥራት እንዳለባቸው ፕሮፌሰር መራራ አሳስበዋል።
ህገ መንግሥቱ የጸደቀበት ቀን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ቃልኪዳን ያሠሩበት ዕለት በመሆኑ በዚህ ዕለት የአገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማክበር ቃልኪዳናቸውን የሚዘክሩበት፣ የሚያድሱበትና የሚፈትሹበት ቀን ሆኖ ተከብሮ እንዲውል የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነው በ1998 ዓ.ም ነው። ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አዘጋጅነት ተከብሯል።
እንደባለሙያዎቹ እምነት በዓሉ ለወደፊት ሲከበር ህብረ ብሄራዊነትን ከማንጸባረቅ ባሻገር ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ መድረክ ተገናኝተው አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት በመጋራት የጋራ አገራዊ መግባበት የሚፈጥሩበት መድረክ ከሆነ፤ በዓሉ በአገሪቱ ብሄራዊ አንድነትና መግባባት ለመፍጠር ይረዳል። ይህም ህዝቦች በውስጣቸው ያለውን ልዩነት እንደ ውበት በማየት ተከባብረውና ተቻችለው ለመኖር ያስችላቸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 29/2012
ሶሎሞን በየነ