በዚህ አምድ ሥር ለወደፊቱ በተከታታይ የሚቀርቡ ጽሑፎች በፍልስፍና ዓይን የሚቃኙ ናቸው:: እነዚህ በፍልስፍና ዓይን የምንቃኛቸው ጉዳዮች ባብዛኛው ሀገር-ተኮር መሆናቸውን አንባቢዎች ከወዲሁ እንዲያውቁት ምርጫችን ነው:: ለጽሑፎቹ መሠረት ከመፍጠር አንጻር በመጀመሪያ ፍልስፍና ራሱ ምን እንደሆነ ማብራራት ያስፈልጋል። ስለ ምንነቱ፣ ባሕርይው፣ ጠቀሜታውና የትኩረት መስኩ ላይ የተወሰነ ግንዛቤ ማግኘት ለአንባቢ ብርሃን ይፈጥራል። ዛሬ የምናተኩረው በዚሁ ጉዳይ ላይ ነው:: ለመንደርደሪያ ሁለት ቀላል ጥያቄዎችን እናንሳ:: ፍልስፍና ለሰው ምንድነው? ሰውስ ለፍልስፍና ምኑ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ቅጽበታዊ መልስ መስጠት አስቸጋሪ ነው:: ቢሞከር የማይቻል ባይሆንም ለማስረዳትም ሆነ ለመረዳት ግን ቀላል አይሆንም። ከሁሉም በላይ ጥያቄዎቹ ቅጽበታዊ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ሳይሆኑ በዚህ ዝግጅት ውስጥ በተከታታይ ለሚነሱ ጉዳዮች መሪ ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው::
«ፍልስፍና» ለሚለው ቃል ቀላል ትርጉም ማግኘት ያስቸግራል። ብዙ ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ትርጉም ሰጥተውታል። እነዚህን በዝርዝር ማቅረብ አስቸጋሪ ቢሆንም ለምናነሳቸው በርካታ ጉዳዮች አንድ አንኳር ትርጉም መርጦ ማንሳት ግን ተገቢ ነው:: «Philosophy» የሚለው የእንግሊዘኛው ቃል የተገኘው ፍሎ (philo) እና ሶፊያ (Sophia) ከሚሉ ሁለት የግሪክ ቃላት ነው:: ሁለቱ ባንድ ላይ ሲዋሃዱ ፊሎሶፊያ (philosophia) የሚል ቃል ይሰጡናል። ትርጉሙ የዕውቀት ወይም የጥበብ ፍቅር ማለት ነው:: በታሪክ ሂደት ውስጥ ፊሎሶፊያ (philosophia) የሚለው ቃል ፍልስፍና Philosophy) ወደሚል ቃል ተለወጠ። ስለዚህ ፍልስፍና በጥሬ ትርጉሙ የሰው ልጅ ለዕውቀት ወይም ለጥበብ ያለውን ፍቅር (love) የሚገልጽ ነው:: ይህ ጥሬ ትርጉም የፍልስፍናን ዓይነተኛ ምንነት ግን አይገልጽም።
በጥናት፣ በምርምርና ዕውቀት ምስክርነቱ በርካታ ሰዎች ለፍልስፍና የተለያዩ ትርጉሞች ሰጥተዋል። ሁሉም ትርጉሞች በሦስት ነገሮች ላይ የሚገናኙ ናቸው:: አንደኛው ፍልስፍና ጠያቂ፣ ምክንያታዊና ሂሳዊ መሆኑ፤ ሁለተኛው የሚያተኩረው በተናጠል ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ባጠቃላይ ጉዳዮች ላይ መሆኑና ሦስተኛው የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ስለዓለም፣ ስለ ሰውና ስለ ሰው ልጅ አስተሳሰብ አጠቃላይ ጉዳዮች መሆኑ ነው:: ከዚህ አንጻር ሚለር እንደጻፈው ፍልስፍና ማለት እጅግ ጠቃሚ ስለሆኑ ጥያቄዎችና ጉዳዮች ምክንያታዊና ሂሳዊ በሆነ መንገድ የሚያስብና የሚመራመር የጥናት መስክ ነው:: የፍልስፍና አንድ ልዩ ባሕርይ ሰዎች ያለ በቂ ማስረጃና ያለ አንዳች ጥርጣሬ የተቀበሉትን ሐሳቦችና እምነቶች እንዳለ የሚቀበል አለመሆኑ ነው:: የሐሳቦችና እምነቶች ምክንያታዊ መሠረት ምን እንደሆነ መረዳት ይፈልጋል። በቂና ተገቢ ትኩረት ያልተሰጠው የጥናት፤ የምርምርና የዕውቀት ዘርፍ ቢሆንም ፍልስፍና እስካሁን ለገነባቸው ዕውቀቶች ሁሉ ፈር-ቀዳጅና መሠረት ጣይ ሆኖ አገልግሏል። ለዚህ ነው የዕውቀቶች «እናት፤ ንግሥት» ወይም «የሳይንሶች ሁሉ ሳይንስ» በመባል የሚታወቀው:: የሰው ልጅ ፍልስፍናን ለምን ይፈልጋል? ማንን ወይም ምንን ይጠቅማል? ምናልባት ፍልስፍና ብቻ የሚመልሳቸውና ሌሎች የዕውቀት ዘርፎች የማይመልሷቸው ጥያቄዎች ይኖሩ ይሆን? በዘመናችን ለፍልስፍና ትምህርትና ጥናት በቂ ትኩረት የማይሰጠው ለምን ይሆን? ፈላስፎች የሚያነሱአቸው ጥያቄዎችና የሚመልሱአቸው መልሶች በሰው ልጅ ሕይወትና ዕድገት ውስጥ የማይተገበሩና ጭብጥነት የሌላቸው ሆነው ይሆን? አንዳንድ ሰዎች ስለማይታይና ስለማይጨበጥ ረቂቅ ነገር የሚደረግ ሰበካ አድርገው ያስቡታል። አንዳንዶች ደግሞ በሥራ የማይጠመዱ ወይም ቁጭ ብለው ለማሰብ የሚያስችላቸው ጊዜ ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉት መራቀቅ ነው ይላሉ።
ሰዎች የማሰብ ችሎታና የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ፍጡራን ናቸው:: ችሎታና ፍላጎት ባይኖራቸው ኖሮ ማሰብና ሐሳብ የሚባሉ ነገሮች ባልተፈጠሩ ነበር። አርስቶትል እንደሚለው «ሁሉም ሰው በተፈጥሮ የማወቅ ፍላጎት አለው»:: ሰው ስለሚኖርባትም ሆነ ስለማይኖርባት ዓለም ማወቅ ይፈልጋል፣ ስለራሱም ሆነ ስለሌላው በቂ ግንዛቤ ማግኘት ይሻል፣ የሚያውቀውን ነገር እንዴትና በምን ያህል ጥልቀት እንደሚያውቅና፤ የማያውቀውን ደግሞ ለምንና እንዴት ማወቅ እንዳልቻለ መረዳት ይፈልጋል:: ይህን ፍላጎት ለማሟላት ስለ በርካታ ነገሮች ብዙ ጥያቄዎችን አንስቷል፣ ለጥያቄዎቹ መልሶች ይሆናሉ ብሎ የገመታቸውን ሰጥቷል። ስለዚህ ሰው የሚያስብና የሚመራመር፤ የሚፈጥርና የሚያፈልቅ ፍጡር ነው ያስባለ ማለት በአእምሮው ብዙ ነገሮችን ይሠራል ማለት ነው – ይጠራጠራል፣ ይጠይቃል፣ ይመራመራል፣ ይገመግማል፣ ይገነዘባል፣ ያገናዝባል፣ ይመዝናል፣ ያመዛዝናል፣ ይተነትናል፣ ይከራከራል፣ ያምናል፣ ብይን ይሠጣል፣ ይዘግባል፣ ይፈትሻል፣ ይፈጥራል፣ ወዘተ. እነዚህ የሰው ልጅ አእምሮው ከሚሠራቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶች ናቸው:: የሁሉም ዋና ዓላማ አስተማማኝ ዕውቀትን ማመንጨትና ምክንያታዊ ግንዛቤን ማስጨበጥ ነው:: ፍልስፍና የሚያጠናው ሶስት ትላልቅ ነገሮችን ነው – ዓለምን፣ ሰውንና የሰው አስተሳሰብን። በተናጠል ነገሮች ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችና ችግሮች በተፈጥሮና በማሕበራዊ ሳይንሶች የሚጠና ሲሆን እነዚህ ሳይንሶች ስለዓለም፧ ስለሰውና ስለ ሰው አስተሳሰብ ሊያጠኑአቸውና ሊመልሱአቸው የማይችሉአቸው አጠቃላይ ጥያቄዎችና ችግሮች ለፍልስፍና የሚተው ናቸው::
በሰው ልጅ የታሪክ ሂደት ውስጥ በመጀመሪያ ሰው ላነሳቸው ጥያቄዎች ምክንያታዊ የሆኑ መልሶችን መስጠት የሞከረው ፍልስፍና ነው:: ሳይንሶች የራሳቸውን ጥናት ፈጥረው ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ ከመጀመራቸው በፊት ፍልስፍና እንደ ሳይንስም እንደ ፍልስፍናም ሆኖ ለሰዎች ጥያቄ መልስ ይሰጥ ነበር። ለዚህ ነው በዕድገት ታሪኩ ውስጥ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ፍልስፍና ነው የሚባለው:: በተለያዩ ነገሮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ሌሎች የዕውቀት ዘርፎች በታሪክ ሂደት ውስጥ ከፍልስፍና እየወጡ የራሳቸውን ነጻ አውድ ሲፈጥሩ እነርሱ የማይደርሱባቸው ጉዳዮች ለፍልስፍና ብቻ የሚተው ሆነ::
ዛሬ ሰው ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑት በተግባራዊ ሳይንሶች የተመለሱና የሚመለሱ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ ሳይንሶች መጠየቅና መመለስ የማይችሉአቸው ሌሎች መሠረታዊ ጥያቄዎች አሉ። ይሁን እንጂ የሰው አዕምሮ ለጥያቄዎች መልስ ካላገኘ እረፍት ማግኘት የማይችል መሆኑ የፍልስፍናን አስፈላጊነትና ዕድገት የግድ አደረገው:: ለዚህ ነው ዛሬ ፍልስፍና ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ከሳይንስ ተደራሽነት ውጪ ያሉ ጥያቄዎች የሆኑት::
ፍልስፍናም ሆነ ሳይንስ ምክንያታዊና ሂሳዊ በመሆናቸው በተወሰነ ደረጃ አንዱ ሌላውን መሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ፍልስፍና የሚያነሳቸውና የሚመልሳቸው አንዳንድ ጥያቄዎች በሚታዩና በሚዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ከሚያተኩሩ ሳይንሶች ውጪ ናቸው:: ሰው በማያውቃቸው ወይም የሚያውቃቸው ነገር ግን በሚገባ ባልተረዳቸው ነገሮች ላይ ያተኩራል። በዚህ ምክንያት በአንዳንዶች ዘንድ ፍልስፍና ፍሬ የማይሰጥ ዛፍ መስሎ ሊታይ ይችላል። በእርግጥ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ከሰው ልጅ ተግባራዊ ሕይወትና እውነታ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት የሌላቸው ናቸው:: ለምሳሌ «ዓለም እንዴትና መቼ ተፈጠረች? በዓለም ላይ የመጀመሪያና የመጨረሻ የሌለው ነገር ምንድነው?» እነዚህና እነ ዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች ከተጨባጭ ሕይወት እጅግ ርቀው ስለሚገኙ ነገሮች የሚነሱ ናቸው:: ይሁን እንጂ ጥያቄዎቹ በሰው ውስጥ የተፈጠሩና የሚኖሩ በመሆናቸው በሕይወት ላይ የራሳቸው ተፅዕኖ አላቸው::
ፍልስፍና ጥያቄ በማንሳት ብቻ የሚቆም አይደለም፤ መልስም ይሰጣል። ይህ መልስ ምክንያታዊ ወይም ኢ-ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ የተወሰነ እምነት የሚፈጠረው በዚህ ላይ ተመስርቶ ነው። አንዳንድ ጥያቄዎች እጅግ ረቂቅ ስለሆነና ከሰው ርቀው ይኖራሉ ተብለው ስለሚታሰቡ ነገሮች ቢሆኑም፤ ሰው ለጥያቄዎቹ የሚሰጣቸው መልሶች፤ የዚህን ሰው አቅም በማጎልበት ዕድገቱንና ሕይወቱን የሚያበረታቱ ወይም አሉታዊ ጫና በመፍጠር የሚያደናቅፉ ሊሆኑ ይችላሉ:: የፍልስፍና ዕውቀት ወይም ግንዛቤ ሂሳዊነትና ምክንያታዊነት በሰው ውስጥ መተማመንን (አማኔታን ) (confidence) ይፈጥራል። ከዚህ አንጻር በሰው ሕይወትና ዕድገት ላይ በጎ የሆነ ተፅዕኖ የማያሳርፍ አስተሳሰብ በፍልስፍና ውስጥ የለም።
ከላይ በዝርዝር ለማብራራት እንደተሞከረው ፍልስፍናን መስራት ወይም መፈላሰፍ ከሰው ልጅ የማይነጠል ነው:: በሌላ አገላለጽ መፈላሰፍ ለሰው ልጅ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የሕይወት ጥሪ ነው:: የሰውን ልጅ ምክንያታዊ ኑባሬ የሚያደርገውም ይህ ነው። የማይታወቁትንና በትንሹ የሚታወቁትን ነገሮች በሚገባ የማወቅና ምክንያታዊና ሂሳዊ በሆነ መንገድ የማሰብ ፍላጎት በሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ አለ። ፍላጎቱ የቁሳዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የኢ-ቁሳዊ ነገሮች ማለትም (ምሁራዊ፤ ፍልስፍናዊ፤ ሃማኖታዊና መንፈሳዊ) አዕምሮአዊም ነው:: ሥነ-ፍጥረታዊ ፍላጎቶቹን ለማርካት ቁሳዊ ነገሮች ያሉትን ያህል አዕምሮአዊ ፍላጎቶቹን ለማርካት ምሁራዊና መንፈሳዊ ነገሮች ያስፈልጉታል። አንድ ፀሐፊ እንዳለው «ፍልስፍና ተፈጥሮአዊ ነው፤ ሊታፈን የማይችል የሰብአዊ ሕላዌ አካል ነው::» ሰው ፍልስፍናን ከራሱ ቆርጦ ሊጥለው ወይም ሊተወው አይችልም። ስለዚህ ይህ ሰው ፍልስፍናዊ ኑባሬም ነው።
በእርግጥ አንዳንድ ተመራማሪዎች ፍልስፍና ለፈላስፎች ብቻ መተው ያለበት ነው ይላሉ:: ወደድንም ጠላንም፤ አወቅንም አላወቅንም ግን የሰው ልጅ ያለ ፍልስፍና አይኖርም። ፍልስፍና የሰው ልጅ መሠረታዊ ምንነት እንጂ ስንፈልግ የምናነሳው ሳንፈልግ የምንጥለው አይደለም። መፈላሰፍ ሰው መሆን ነው:: ብንፈላሰፍም፤ ባንፈላሰፍም እንፈላሰፋለን። ፍልስፍና መታየት የሚኖርበት የምሁራን እንቅስቃሴ ብቻ ሆኖ ሳይሆን ሰብአዊና ሰዋዊ ጉዳይ ሆኖም ነው:: አርስቶትል እንዳለው «አወቀው አላወቀው ሁሉም ሰው ፍልስፍና አለው» ፤ እናም ሁሉም ሰው በተወሰነ ደረጃ ፈላስፋ ነው:: ይወቁትም አይውቁት፤ ግርድፍ ይሁን የረቀቀ ያለ ፍልስፍና የሚኖር ሰብአዊ ግለሰብም ሆነ ሕብረተሰብ የለም። ባጭሩ ሰዎች የሚኖሩትና ሕይወታቸውን የሚመሩት ባላቸው ፍልስፍና ነው::
የተለያዩ ሳይንሶች የተለያዩ የጥናት መስኮችና ተገብሮዎች አሉአቸው:: የሚያነሱአቸው ጥያቄዎችና የሚመልሱአቸው መልሶች ስለ ተናጠል ነገሮች ነው:: ይሁን እንጂ የሰው ልጆች የሚያነሱአቸው ጥያቄዎች በተናጠል ስለሚኖሩና ስለምናውቃቸው ነገሮች ብቻ አይደለም፤ ስለ ነገሮች ግንኙነትና አጠቃላይ ባሕርይም ጭምር እንጂ። የተናጠል ነገሮች ዕውቀት ብቻውን ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤን (wisdom) ሊሰጠን አይችልም።በዓለም ላይ ብቻውን የሚቆም ምንም ነገር የለም። ስለዚህ ሰው ማወቅ የሚፈልገው እያንዳንዱን ነገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ እንዴት አድርገው መስተጋብራዊ ሥርዓት እንደፈጠሩም ጭምር ነው::
የፍልስፍና ሥራ ትንተናዊና ቅንብራዊ፣ ገንቢና አፍራሽ መልኮች አሉት። በትንተና አንድን ጥቅል ሐሳብ በትኖ ጠቃሚ የሆነውንና ያልሆነውን ለይቶ ለማሳየት ይሞክራል። በቅንብራዊ ተግባሩ ጠቃሚ፣ ተፈላጊ፣ እውነትና ውበት የሆኑትን ነገሮች ማሳየት የሚችለው አመክንዮያዊ በሆነ መንገድ ነው:: በዚህ ተግባሩ የነበረውን አፍርሶ ያልነበረውን ይገነባል። ካተን የተባለው ፀሐፊ «በፍልስፍና ውስጥ ገንቢና አፍራሽ ገጾች አሉ» ይላል። የሚገነባው ጠቃሚ፣ አስፈላጊ፣ ምክንያታዊ፣ እውነትና ማረጋገጫ ያለውን ነው:: የሚያፈርሰው ደግሞ የማይጠቅም፣ የማይፈለግ፤ ውሽት፣ ኢምክንያታዊ፤ ማስረጃ የሌለውና ኢአመክንዮያዊ የሆነውን ነው:: ምክንያታዊና እውነት የሆኑትን ኢምክንያታዊና ውሸት ከሆኑት ለይቶ ማወቅና ማሳወቅ በሚያደርገው ጥረት ገንቢ ነው:: ኢምክንያታዊንና ውሸትን ከምክንያታዊና እውነት ለይቶ የሚያስወግድ በመሆኑ ደግሞ አፍራሽ ነው::
ሰዎች ከአእምሮአቸው ውስጥ በሚነሳው ችግር ምክንያት ይሰቃያሉ:: ነገር ግን የዚህ ችግር መንስኤ የት እንደሆነ ለማወቅ ይቸገራሉ:: የችግራቸው መንስኤ ከውስጣቸው ሆኖ እያለ ከውጪ ይፈልጋሉ። ብዙ ጊዜ ለውስጣዊ ችግራቸው ውጫዊ ምክንያት ያቀርባሉ ፤ ያማርራሉ። ከውስጣቸው የሚነሳ ችግር ብዙ ጊዜ አይታሰባቸውም። ስለዚህ ለማወቅ የሚጥሩት ባብዛኛው ከራሳቸው ውጪ ስለሆነ ምክንያት እንጂ በውስጣቸው ስለላው ነገር አይደለም። የፍልስፍና ፍተሻ የሚያተኩረው በውጫዊ ነገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ውስጣዊ ማንነትም ላይ ነው:: ዋናው የፍልስፍና ቤተ-ሙከራ አስተሳሰብ ወይም ሐሳብ ነው:: የሰው አስተሳሰብ አንዳንዴ የቅርቡን ሩቅ የሩቁን ቅርብ፣ ቀላሉን ከባድ ፣ ከባዱን ቀላል፣ ያለን የሌለ የሌለን ያለ፣ የሚቻልን የማይቻል፣ የማይቻልን የሚቻል፣ ውሸትን እውነት እውነትን ውሸት አድርጎ ያቀርባል። ስለዚህ አስተሳሰቦች እንዳለ ከመወሰዳቸው በፊት መፈተሽ አለባቸው:: እውነታን በትክክል የሚገልጹ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት።
ከዚህ አንጻር ሲታይ የፍልስፍና ዋና ጉዳይ የሰውን ልጅ አዕምሮ ማልማት ነው:: አዕምሮው የለማ ሕብረተሰብ አብሮ ለመኖር፣ አብሮ ለመሥራትና አብሮ ለማደግ አይቸገርም። ያልለማ አዕምሮ ግን አመክንዮያዊ አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የእኩይ አስተሳሰቦች ምንጭና መሠረት የመሆን ዕድል ሰፊ ነው:: የለማ አዕምሮ በርካታና ውስብስብ የሆኑ ችግሮችንና ጥያቄዎችን ምክንያታዊ በሆኑ መንገዶች የመፍታትና የመመለስ አቅም አለው:: ፍልስፍና በባሕርይው ነባር ሐሳቦችን፣ እምነቶችን፣ ሥርዓቶችን፣ እሴቶችን፣ ግንኙነቶችን እንዳሉ አይቀበልም:: አስተሳሰቦች ይፈጠራሉ፤ ያድጋሉ፤ ያረጃሉ። ሐሳቦች አረጁ ማለት ሰውን የሚጎዱ እንጂ የሚጠቅሙ መሆናቸው አብቅቷል ማለት ነው:: ካተን እንደሚለው «ያረጁ የአስተሳሰብ ሥርዓቶች ሰውን የማገልገል አቅም የላቸውም» ያለ ፍልስፍናዊ ትንተና ሃሳቦች ሰውን የማገልገል አቅም ያላቸውና የሌላቸው መሆናቸውን መረዳት ያስቸግራል። ያረጀውን መጣል ወይም እርሱን የሚተካ አዲስ ሐሳብ ማመንጨትና ማቀንቀን የግድ ይላል::
የዳበረ የፍልስፍና ባሕል በሌላቸው ሕብረተሰቦች ውስጥ የተሳሳቱ ግንዛቤዎች፣ የተለያዩ የሀሰት አምልኮቶች፣ እውነትነታቸው ያልተረጋገጠ አመለካከቶች፣ አለመተማመንና አለመፈቃቀድ፣ ትዕቢትና ጥላቻ፣ የበላይነትና የበታችነት ስሜት፣ ሐሜትና ውሸት፣ ምቀኝነትና አስመሳይነት ባጠቃላይ ምክንያታዊ ያልሆነ አስተሳሰቦች ማሕበራዊ እውነሰታንና ግለሰባዊ ሕይወትን የሚቆጣጠሩ ናቸው:: እነዚህ የአንድን ማሕበረሰብ፣ ሕዝብ ወይም ሀገር ፖለቲካ ፣ ባሕል፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት መሠረት በማሳጣት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው። በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሳለች በምትባለው ዓለማችን ውስጥ ዛሬ ሕዝቦች ምክንያት በጎደላቸው አስተሳሰቦች የተነሳ የጥላቻና የጦርነት፣ የክፋትና ጥፋት ፣የዘረኝነትን የአግላይነት መከራ ይገፋሉ::
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከአንጋፋዎቹ ሀገሮች አንዷ ብትሆንም ባለመታደል የዳበረ የፍልስፍና ባሕል የላትም። በማሕበረሰባችን ውስጥ የበላይነት ያለው አስተሳሰብ ምክንያታዊና ሂሳዊ አቅም ያለው አይደለም:: ባብዛኛው ሰፍኖ ያለው የመካከለኛ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ነው:: በመካከለኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የ21ኛውን ምዕተ-ዓመት ሕይወትና ሀገር መምራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ለበርካታ ምዕተ-ዓመታት በሀገራችን ውስጥ የነበረው አስተሳሰብ ችግርን የመፍጠር እንጂ የመፍታት፣ ጥያቄን የማንሳት እንጂ የመመለስ፣ የማጣላት እንጂ የማስታረቅ፣ የማራራቅ እንጂ የማቀራረብ፣ የመግፋት እንጂ የማቀፍ አቅም አልነበረውም። ዛሬም ያለው ገዢ አስተሳሰብ ይኸው ነው:: ስላለንበት ማሕበረሰብ ለትንሽ ጊዜ እናስብ፤ ራሳችንንና ያለንን ቤተሰብ እናስተውል:: ብዙዎቻችን ከላይ በተጠቃቀሱ እኩይ ነገሮች የተቸገርን ወይም በእነዚህ ነገሮች ያስቸገርን እንደምንሆን ይገመታል። ከእነዚህ ነፃ የሆኑ ሰዎች የሉም ማለት ባይቻልም ቁጥራቸው በእጅጉ ዝቅተኛ ነው:: የብዙ ሰው አዕምሮ ባብዛኛው ማሰብ የማይኖርበትን የሚያስብ ወይም ማሰብ የሚኖርበትን የማያስብ በመሆኑ ሕይወትና ዕድገት በኢትዮጵያ ክፋትና ጥፋት፣ ፍርሃትና ሥጋት፣ መግፋትና መገፋት ተለይቶት አያውቅም::
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ጠና ደዎ /ፒ ኤች ዲ/