ከክብደቴ ላይ ኪሎ ሥጋ ቀንሼ ከወዲያ ወዲህ ስንቆራጠጥ ያየኝ ሰው ለአዲስ አበባ አረጋውያን ተሽከርካሪዎች ሠቆቃና ብሶት መሆኑን ላይረዳኝ ይችላል። በአሮጌ መኪና የደረሰውን አንድ ዘግናኝ አደጋ ካየሁ በኋላ ግን ፊልም ሳይ፣ በምግብ ሰዓት፣ ሥራ ገበታ ላይ ሆኜ አብሮኝ ቁጭ ያለ ሰው ከእኔ ጀርባ እርቆ ከተቀመጠ ሌላ ሰው ጋር የሚነጋገር ይመስል ጮክ ብዬ ብቻዬን እለፈልፍ ጀምሬያለሁ።
አውቃላሁ ይህ ወቅት ፖለቲካው ናላችንን ያዞረበት ጊዜ ነው። እርሱን ወደ ጎን ትቶ ሌላ ጉዳይ ማንሳት ከጮማ ወደ ሽሮ ፊትን የማዞር ያህል ነው፤ (አባባሉ ጮማ በልተው ለሚያድሩት ነው ታዲያ)። ወጃጆቼ እኔን ግን አዕምሮዬን ተቆጣጥሮት ያለው የጡረታ ጊዜ ያለፈባቸው የመዲናችን ተሽከርካሪዎች ጉዳይ ነው።
አንድ ቀን ለአንድ የሥራ ጉዳይ ወደ አትክልት ተራ አምርቼ ያየኋቸውን ያለ አቅማቸው ጭነት ያበዙ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ማመን አልቻልኩም። በአንዲት ጀንበር የሰውን ነብስና ንብረት ዶግ አመድ ማድረግ እንዴት ቀላል እንደሆነ ተገንዝቤበታለሁ።
በድሮ ስሟ አሁንም አራዳ አራዳ የምትጫወተው መዲናችን ያረጁና ያፈጁ የሥሪት ዘመናቸው መቼ እንደሆነ እንኳን የማይታወቁ ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ የፋራነት መጠኗ ጨምሯል። በዚህ የተነሳም ቀኙ ፤ግራው፤ የእግረኛው መንገድ ብቻ ሁሉም ነገር ድብልቅልቅ ብሎባት የአንዱን ድርሻ ሌላኛው ሲወስደው የምናይበት አጋጣሚ ብዙ ነው።
ለመሆኑ ጭራሮ የምታህል ‹‹ስፖኪዮ›› እንኳን ሳይኖራቸው ከወደ ራስጌያቸው ሰማይ ጠቀስ ለመምሰል ግዙፍ ቁሳቁሶችን ተሸክመው በየአውራጎዳናው የሚሽከረከሩ ጡረተኛ መኪኖችን ስታዩ ምን ትሏቸዋላችሁ? አንዳንዶችማ ትኩረታቸው የሰውን ህይወት ከመታደግና ለከተማዋ ውበት ከመጠንቀቅ ይልቅ እንደ አንዳንድ የአፍሪካ ባለስልጣናት ከሥራዬ ሞት ይንቀለኝ ያሉ ይመስላሉ። ለራስ ወዳድነታቸው የሰጡትን ትኩረት ከእኔ ሌላ ላሳር በማለት አዲስ ወደ መዲናዋ የገቡትን መኪኖችም መግፋት ጀምረዋል። እነዚህ አዛውንት ተሽከርካሪዎች ከከተማዋ ጥርግ ብለው ቢጠፉ ምን ይፈጠራል ትላላችሁ?
እርጅና ተጫጭኗቸው የተወሰነች እርቀት እየተጓዙ ለእድሳት የሚቆሙ፤ መብራታቸው ማታ ማታ የሚዳከምባቸው፤ የጡሩንባ ድምፃቸው የሰለለ፤ በነዳጅ ሳይሆን በወይራ ዘይት የሚሠሩ ይመስል አካባቢውን በጭስ እያጠኑ የሚንቀሳቀሱ ዕድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎች እንደ ደህና ሞዴል መሀል ከተማ ላይ ሲምነሸነሹ ከነሱ የተሻለ ፍጥነት ያለውን እግረኛ ሲፈጁት ማየት እንግዳ አይደለም። እናም እነኚህ አዛውንት ተሽከርካሪዎች ጡረታ መውጣት አለባቸው የሚል ጭምጭምታ ሰማሁ በእርግጥ እውነት ከሆነ መልካም ነው ብዬ አሰብኩ። ነገር ግን ተሽከርካሪውን እንዳይጠቀም የተከለከለ ባለንብረት እራሱን በብስጭት እንደያጠፋም አጥብቄ ሰጋሁ። (ወይ ጣጣ ሌላ መዘዝ) ለካ ከእነዚህ ያረጁ ተሽከርካሪዎች በእጅጉ ተጠቃሚ የሆኑ ‹‹ጋራዦችም›› አሉ።
መኪኖቹ እርጅና ቢጫጫናቸውም አገልግሎት እንዲያቆሙ የፈቀደላቸውም ሆነ ያስገደዳቸው አካል የለም። ምክንያቱም በእነዚህ ዕድሜ ጠገብ መኪኖች የሚገኘው ገቢ ከቆመ የሾፌሩን ቤተሰብ ጨምሮ ትንፋሻቸው አብሮ የሚቆም በርካታ ህዝብ ሊኖር ይችላል። እነዚህ የተወቀጡ የሚመስሉ ተሽከርካሪዎች የስንቱን የተከፈተ ጉሮሮ ደፍነው እንደሚያሳድሩ የሚያውቁት ባለቤቶቹ ብቻ ናቸው።
አሁን ላይ የመኪና ፋሽን እንደ ‹‹ሂውማን ሄር›› በበዛበት ወቅት ያረጁ ተሽከርካሪዎችን ማየት በራሱ እንኳንስ ባለ አራት እግሩን ይቅርና እኔና መሰል መኪና አልባ ሰዎችን ማበሳጨታቸው አልቀረም። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ መኪኖች ውበታቸው ብቻ ሳይሆን ድምፃቸውም ዘግናኝ ነው። ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚለቀቁ የጡሩምባ ድምፆች ‹‹ክላክስ›› ጸጥታን በሲዲ የሚሸጥ አሳታሚን ያስመኛሉ። የሚያንገሸግሽ ጩኸትና ራስ ምታት ከሚለቅ ጭስ ጋር ለመዋሀድ ትገደዳለህ። በዚያው ልክ ካልፈጠንን አንሄድም ብለው አንዳንዴ በለስ ሲቀናቸው የፈረደባትን የሰው ነፍስ ይነጥቃሉ። ካልቀናቸው ደግሞ ከራሳቸው ጋር ‹‹ግልብጥብጦሽ›› ይጫወታሉ። እውነት ግን ካልታገሱ እኮ የአንዳንዱ አሮጌ መኪና ድርጊት ደም ያፈላል።
የመኪና ጡሩምባ ድምፅ መንገደኛን ማስጠንቀቂያና ከፊት ያለን መኪና ማንቂያ የመሆኑ ፋሽን ድሮ ቀረ በሚባል ደረጃ ላይ ነን ስል በምክንያት ነው። አዛውንቶቹ መኪኖች ምንም በሌለበት እየተነሱ የሚያንባርቁብህ ድምፅ ሌላኛው የስህተታቸው አንጓ ነው። ሐፃናትና ተማሪዎች አሉ፣ አቅመ ደካሞች ይደነግጣሉ፣ ሰፈር ውስጥ ነኝ፣ ትምህርት ቤት ሊኖር ይችላል፣ የሕክምና ማዕከል በአቅራቢያዬ አለ፣ እንስሳ ላስደነብር እችላለሁ… ወዘተ ስጋቶች እነዚህ መኪኖች ላይ አይስተዋሉም። የሚያሽከረክሯቸው ሹፌሮች አዕምሮ ላይም ይህ ቁምነገር በስህተት እንኳን አይከሰትም። እንደ አገራችን አንዳንድ ‹‹ፖለቲከኞች›› እነዚህ ተሽከርካሪዎች የጥንካሬያቸውን መገለጫ በጩኸት ማሳየት ይፈልጋሉ። መንገድ ተዘግቶባቸው ተሰልፈው በቆሙና ወዴትም ሊሄዱ እንደማይችሉ በሚታወቅ መኪኖች ላይ የጥሩንባ እሩምታ መልቀቅ ምን ይባላል?
በርግጥ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ቀድመው ከሰለጠኑ አገሮች የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የፍልስፍና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ልማትን ለማፋጠን መገልገላቸው ከበደል የሚቆጠር ሆኖ አይደለም። ዘመናዊነታቸውና ለከተማ ምቹነታቸው የተረጋገጡ እልፍ መኪኖች ያስፈልጉናል። እርግጥ ነው ቁጥሩ በአንድ መቶ ሚሊየን ለሚቆጥር ህዝብ ገና አንድ ሚሊየን መኪና እንኳን በአገሪቷ የለም። ወዳጄ አዲስ መኪና መንዳት የማይፈልግ ማነው? ቀረጡ እኮ ነው ድሪቶ እየደራረበ መኪናን እንደ ብርቅየ እንድናየው ያደረገን። ምንም እንኳን በአንዲት ከተማ ወሳኝ ከሚባሉት ጉዳዮች ተሽከርካሪ አንዱ ቢሆንም አዲስ አበባን በዱሮ ማሊያዊ ላያት ሰው ግን ማዘኑ አይቀሬ ነው። ከሸገር ጋር መለያየት ከሞት የከፋ ሲዖል እስኪሆንባቸው ድረስ ሰውን መግደል አልጠግብ ብለው ዘመናዊነታቸው ተረስቶ እንደ መዥገር ተጣብቀውብናል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ብቻዬን ልጨነቅበት ብዬ አንዱ ጓደኛዬ ጋር ደውዬ ሻይ ቡና እየተገባበዝን ለማውራት ቀጠሮ ያዝን። ከቀጠሯችን አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ብቻ አርፍዶ የመጣው ሰዓት አካባሪው ጓደኛዬ ከመድረሱ በፊት፤ ከዚህ ቀደም የቀለም መደቧ ቢጫ የነበረ በእርጅና ምክንያት አሁን ላይ ወደ እርድ የተለወጠ መልክ ያላት ከባጃጅ ከፍ ያለች የላዳ ታክሲ ታናሽ እህት ብቅ አለች። መንገዱ በአራት እጆች ( በእነ ቴሌ፣ ውሃና ፍሳሽ፣ መብራት ኃይል፣ መንገዶቸ ባለስልጣን) የተቆፋፈረ ነበርና እንኳን ለመኪና መጓጓዣነት ወፎች በዚያ አካባቢ ትንሽ ከፍ ብለው ሲበሩ እንኳን ተንገዳግደው የሚወድቁ ነው የሚመስለው።
እና ይህችው እርድ መልክ ያላት መኪና መቼም ስንትና ስንት ኪሎ ሜትር እንደተጓዘች እግዜር ይወቀው። አዲስ የተቆፋፈረውን መንገድ በማለፍ ታሪክ ብትሠራም፣ መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ዕርዳታ ከሚጠይቅ ሰው ጋር ተላትማ ሹፌሩ ሰውየውን ወደ ህክምና ለማድረስ ሌላ ልመና መጀመሩን ሳይ መዲናዋ ውስጥ ያሉ መሰል መኪኖች በሙሉ ተሰብስበው መወገድ አለባቸው የሚል የአቋም መለኪያ አወጣሁ።
እናም ከዚህ ጊዜ በኋላ የባለ እርድ መልኳን ሁኔታ ለቀጠሮ አክባሪው ጓደኛዬ ስነግረው ፤ ‹‹ግድ የለም በጤናዋ አይደለም ይኼ አብሮ መኖርንና ፍቅርን የማይወድ ክፉ ጋንጩር ተጠናውቷት ነው እንጂ፣ ሆን ብላ ሰውን ለመቅጠፍ በዚህ ዕድሜዋ አትባልግም። ባይሆን እነ ቮልስን ጨምሮ የተከበሩ ሽማግሌ መኪኖችን በሲኖ ትራክ እናስመክራቸዋለን። እንዳስፈላጊነቱም እንገስጻቸዋለን›› አለኝ ፌዝ በተቀላቀለበት የሽሙጥ አነጋገር።
ሞትን በሻንጣችን ሸክፈን የመሄዳችን ቅሉ የገባኝ እነዚህ ዕድሜ ጠገብና ዘመን የማይሽራቸው ተሽከርካሪዎች ዛሬም ከእኛ ሌላ ላሳር እያሉ መጫወቻ ሲያደርጉን ነው። በዘመናቸው አልበቃ ያላቸው ገዳይነት ያለዘመናቸው ስንቱን ለአፈር አበቁ፤ አዛንቶችን አሽንቀንጥረው ጥለው ሕፃናትን ያለ ጧሪ ያስቀሩ ብዙ አነዚህን መሰል መኪኖች አሉ። ይኸው ዛሬ ላይ ‹‹ከአዲስ አበባማ ተለይቼ የብቸኝነትን ተራራ የመግፋት አቅም ለእኔ አልተቸረኝም›› የሚል ብርቱ አቋም ይዘው እየፎከሩብን ይገኛሉ።
እንዴት ያለውን መኪና ባየሁበት አይኔማ እነዚህን ጡረታ እምቢ ያላቸውን መኪኖች አላይም ከማለታችን ከኋላ መጥተው የልማዳቸውን ያደርሱብናል። መቼም ጆሮ ቢኖራቸው ‹‹ይኼ አብሮ መኖርንና ፍቅርን የማይወድ ክፉ ተንኮል ተጠናውቶት ነው እንጂ፣እንዲህማ አይለንም›› ይሉኝ ነበር። ግን እመኑኝ ከእነዚህ መኪኖች ጋር እንኳንስ አብሬ መኖርን ልመኝ ይቅርና አሮጌ መንገዶች እንኳን ‹‹ዓይናችሁን ላፈር›› ማለታቸው አይቀርም።
አንድ ተሽከርካሪ ያገለገለበት ዘመንና የሄደበት ርቀት ታይቶ በሰውና በንብረት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ ከአገልግሎት እንዲወጣ ማድረግ ለምን ተሳነን? ይህንን ለማድረግስ የግዴታ ለመኪኖች የጡረታ ሚኒስቴር ያስፈልገን ይሆን? ደግሞም ለዚህ ብለን የአገር ሽማግሌዎችን አማላጅ አንልክም።
እየሰጡት ካለው ጥቅም ይልቅ እያስከተሉት ያለው ጉዳት ያመዝናል። አንድ የአገልግሎት ዘመኑ ያበቃ ተሽከርካሪ በመንገድ ላይ ሊያመጣ የሚችለው አደጋ ዘግናኝ ከመሆኑም በላይ፣ የመንገድ ደኅንነት ሥጋታችንን እያባባሰው ይሄዳል።
መዘዙ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች ከአዲሶቹ ይልቅ ወደ ከባቢ አየር ከፍተኛ መጠን ያለው የተበከለ ጋዝና ደቃቅ ብናኞች ስለሚለቁ እንደ አስምና ብሮንካይትስ ያሉ የመተንፈሻ አካል በሽታን እንዲቀሰቀስና እንዲባባስ ያደርጋሉ፤ የሕፃናትን የነርቭ እና የአዕምሮ ሥርዓትን ያቃውሳሉ፤ በደም ውስጥ የኦክስጂን ዝውውር በማወክ በተለይ የልብ ሕመም ያለባቸው ሰዎችን ለከፍተኛ ጉዳት ብሎም ለህልፈት ያጋልጣሉ፣ ኦዞን በታችኛው የከባቢ አየር ክፍል እንዲፈጠር ምክንያት በመሆን የዓይን መቆጥቆጥ እና የመተንፈስ ችግር እንዲፈጠር ያደርጋሉ፤ የግሪን ሀውስ ኢፊክት በመፍጠር ለአካባቢ አየር መሞቅ እና ለአየር ንብረት መለወጥ እንዲሁም ለአሲድ ዝናብ መከሰት ምክንያት ይሆናሉ።
የአሮጌ ተሽከርካሪዎችን ድርጊት ከአጥፍቶ ጠፊነት ለይቼ አላየውም። የሚቅጥፉትን ነፍስ ብቻ ሳይሆን የባለመኪናው ቤተሰብም እንዲሁ ፈርሶ አገር ትንኮታኮታለች። ቤተሰብ አገርን የምንገነባበት አንደኛው ምሰሶ ነው። ያለ መልካም ቤተሰብ አገርን ታላቅ አደርጋለሁ ብሎ ማሰብ ደግሞ ዘበት ነው።
መቼም አሮጌውን ተው ማለት አዲስ ተጠቀሙ ማለት ነው። በነገራችን ላይ ሰው አዲስ ነገር የማይገዛው አቅም ስለሌለው ነው ብዬ አምናለሁ። ታክሱም ከፍተኛ በመሆኑ ያገለገሉ መኪናዎችን እንዳይጠቀም ለማድረግ አዲስ መኪና ላይ ታክስን በመቀነስ ገዥን ማበረታታት ይቻላል። ከዚህም ባሻገር አገር ውስጥ የሚሠሩ መኪናዎች ጥራትን ማስጠበቅም ቢቻል መልካም ይመስለኛል። ምክንያቱም የአገር ምርቱ ‹‹ቦዲው›› ካርቶን ነው። ትንሽ ችግርን እንኳን ማስተካከል የማይቻልበት ስለሆነ ጥራትን መከታተል ቢቻል ገዥ ወደ አገር ውስጥ ምርት ይጎርፍ ነበር።
የሚመለከተው አካል ከከባቢ አየር ብክለት፣ ከመንገድ ደህንነት፣ የሀገር ውስጥ አወቶሞቲቭ ኢንዱስትሪን ከመጠበቅ እና ኢንቨስትመንትን ከመሳብ ጋር ተያይዞ ያለውን ነገር ታሳቢ አድርጎ ለጉዳዩ ስልት ሊቀይስ ይገባል። ታዲያ መፍትሔዎች የአሮጌ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ሕይወትንም ያገናዘቡ መሆን አለባቸው ባይ ነኝ። ከዚያም ሕመማችንን አክመን፣ ጥፋታችንን አርመን አዲስ አበባን በሁሉ ነገር እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
አዲሱ ገረመው