ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ‹‹ምጡን እርሽው ልጁን አንሺው›› የሚለው የአበው ብሂል የተዘነጋ ይመስላል። ለዚህም አሁን አሁን በርካታ ነፍሰጡር እናቶች አምጠው ከመውለድ ይልቅ በቀዶ ጥገና መውለድን መምረጣቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል።
በሌላ በኩል የመንግሥት የጤና ተቋማት የነፍሰጡር ክትትልና የወሊድ አገልግሎት በነፃ እየሰጡ ቢሆንም የነፍሰጡሮች ቀዳሚ ምርጫዎች ሲሆኑ ግን አይስተዋልም። ከእነዚህ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ምክንያታቸው ምንድን ነው? የሚያስከትሏቸው ችግሮችስ፣መፍትሔዎቻቸውስ ምን ይሆን? ስንል የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።
‹‹በግል የጤና ተቋማት ከፍተኛ ወጪ እየከፈሉ የሕክምና ክትትል አድርገው የሚወልዱ እናቶች ብዙዎቹ ገንዘብ ኖሯቸው አይደለም። በወሊድ ጊዜ ለሚከፍሉት ገንዘብ ጭንቀት የሚይዛቸው አሉ። በዚህ የተነሳ የቤታቸውን ወጪ በተገቢው ባለማሟላት ቤተሰቦቻቸውን እና ልጆቻቸውን እስከ መበደል የሚደርሱ እንዳሉ አውቃለሁ›› ሲሉ ሐሳባቸውን የገለፁት በመሿለኪያ ጤና ጣቢያ ክትትል የሚያደርጉትና ሦስተኛ ልጃቸውን ለመውለድ የቀናት እድሜ የቀራቸው ወረግቡዋ ነፍሰጡር ወይዘሮ መለሰች ደሱ ናቸው።
በነፃና በጥሩ እንክብካቤ መውለድ የሚቻልበት ዕድል በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ በመንግሥት በኩል ተመቻችቶ እያለ በሌላቸው የኢኮኖሚ አቅም እየተጨናነቁ፣ ተበድረው ጭምር ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉ ነፍሰጡሮች በመኖራቸው ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሮ መለሰች፤ በቂ የገንዘብ አቅም ያለው ሰው በግል የሕክምና መስጫዎች አገልግሎቱን ማግኘቱ ክፋት የለውም፤ መንግሥትንም የማገዝ ያህል ነው ይላሉ።
‹‹እኔ ከታዘብኳቸው ሰዎች ሁለት ምክንያቶችን አስተውያለሁ›› የሚሉት ነፍሰጡሯ፤ የመጀመሪያው ከሚሰሙት ወሬ ተነስተው ወይም ደግሞ ከዓመታት በፊት ከገጠማቸው ክስተት ተነስተው በአንድ በኩል የመንግሥት የጤና ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሹ አድርጎ የመደምደም ሁኔታ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጉል መኮፈስ ነው ይላሉ። በማይጠቅም ይሉኝታ ታጥረው በቅርበት ከሚያውቋቸው ሰዎች፣ከጎረቤቶቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጭምር ለየት ላለማለት ሲሉ ገንዘብ ያለው የሚያደርገውን ለማድረግ ሲንጠራሩና ለአላስፈላጊ ወጪ የሚዳረጉ እናቶች በርካታ እንደሆኑም ተናግረዋል።
‹‹በግል የጤና ተቋማት ጥሩና የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል የሚል አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ውስጥ በሰፊው ይታያል። እኔም የዚህ አይነት እሳቤ ካላቸው እናቶች መካከል በመሆኔ ሦስቱንም ልጆቼን የወለድኩት በግል ሆስፒታል ነው›› ያሉት ወይዘሮ ሐያት አሊ፤ “ወጪው በተለይ አሁን ካላው የኑሮ ውድነት አኳያ ከባድ ነው። አራስ ይዘው ሲወጡ ዘመድ የሚያስቸግሩ ሞልተዋል” ይላሉ ትዝብታቸውን ሲገልፁ።
ከአጠቃላይ የጤንነት ሁኔታ ጋር አያይዘው የመውለዱን ሁኔታ በምጥ ይሻላል ወይስ በቀዶ ጥገና የሚለውን ከገንዘብ ሳይሆን ከሙያዊ አይን ብቻ ሀኪሞች መወሰን ቢችሉ የተሻለ እንደሚሆን የሚናገሩት ወይዘሮ ሐያት፤ አሁን ላይ “ከዘመናዊነት ጋር በሚያያዙ ምክንያቶች ለዘጠኝ ወራት በሆድ መሸከምን እንጂ አምጦ መውለድን ከነአካቴው የማያውቁ ብዙ ወላዶች አሉ” ይላሉ። በዚህ መንገድ ነው መውለድ የምፈልገው ብለው ቀዶ ጥገና እንደሚመርጡ ይገልፃሉ።
ሁሉንም ልጆቻቸውን የወለዱት በምጥ ሲሆን ‹‹ፈጣሪ ያስቀመጣቸው ነፍስን የመተካት ሂደቶች እያንዳንዳቸው በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ ነው›› የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸውም ወይዘሮ ሐያት ተናግረዋል።
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አዋላጅ ሐኪም የሆኑት ወይዘሮ ኑሪት አህመድ እንዳሉት፤ ነፍሰጡሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል በመንግሥት ጤና ተቋማት ላይ ያለው አመኔታ እምብዛም ነው። እንደውም እዚህ የሚወልዱትም ሆነ የሚታከሙት ገንዘብ የሌላቸው ደሀዎች እንደሆኑ አድርጎ የማየት ሁኔታዎች እንደሚገጥሙ ያነሳሉ። አገልግሎት ፈላጊዎቹም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ሆነውና ወስነው ስለሚመጡ አይረኩም። በመሆኑም በማህበረሰቡ አመለካከት ላይ በሰፊው ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በድንበሯ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ማዕከል በማሕፀንና ፅንስ ሕክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ደነቃቸው አሰግደው እንደሚሉት፤ መንግሥት በዘርፉ የሚከተለው መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ በመሆኑ በጤና ኤክስቴንሽን አማካኝነት የጤና ትምህርት ቤት ለቤት ይሠጣል። በመሆኑም በጤና ተቋማት ክትትል የሚያደርጉና የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። መንግሥትም ለነፍሰጡር እናቶች በነፃ አገልግሎት መስጠቱ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የመንግሥት የጤና ተቋማት በነፃ አገልግሎት እየሰጡ ለምን ከግል የጤና ተቋማት እየሄዱ ከፍለው ይወልዳሉ ለሚለው በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት በመንግሥት የጤና ተቋማት ላይ የሥራ ጫናን ፈጥሯል። በመሆኑም የአገልግሎት ፈላጊውና አገልግሎት ሰጪው አለመመጣጠን ይስተዋላል፤ የጤና ባለሙያ፣የአልጋ፣ የመድሃኒት ወዘተ.. አጥረት ስለሚፈጥር ተገልጋዩ ማግኘት የሚፈልገውን አገልግሎት በሚፈልገው ጊዜና መጠን እንዳያገኝ ያደርገዋል። በዚህ የተነሳ ሌላ አማራጭን መፈለጉ ግድ ስለሚሆን ወደ ግል የጤና ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ዶክተሩ ገልፀዋል።
ዶክተር ደነቃቸው እንዳብራሩት፤ ጤና ጣቢያዎች ምንም አይነት የጤና ችግር የሌለባቸው ነፍሰጡሮች የእርግዝና ክትትል አድርገው የሚወልዱበት የጤና ተቋም ነው። አሁን ላይ አንዳንዶቹ ድንገተኛ የቀዶ ህክምና በማድረግ ማዋለድም ጀምረዋል። ነገር ግን እነኝህን የጤና ተቋማት መጠቀም የሚገባቸው ነፍሰጡሮች ሁሉ በየሆስፒታሉ በመሄድ የወሊድ አገልግሎት እያገኙ ስለሆነ በሆስፒታሎች ላይ የሥራ ጫና መፍጠራቸውን አንስተዋል።
‹‹በምጥ መውለድ የሚችሉ እናቶች በፍፁም ቀዶ ጥገናን መምረጥ የለባቸውም›› ያሉት ዶክተር ደነቃቸው፤ በቀዶ ጥገና የሚወልዱ ነፍሰጡሮች ሌሎች አላስፈላጊ ችግሮችን ይጋፈጣሉ። ማደንዘዣም የራሱ የሆነ ችግር አለው። በአጋጣሚ በሂደቱ የደም መፍሰስ ካጋጠመ ደግሞ ማህፀን እስከመውጣት የሚደርስ ችግር ሊያስከትል ይችላል። ቁስሉም ቢሆን ሊያመረቅዝ ይችላል። ስለዚህ በቀዶ ጥገና መውለድ ግዴታ ካልሆነ በስተቀር አስፈላጊ አይደለም። በዚህ መንገድ መውለድም ዘመናዊነት ሳይሆን አላዋቂነት እንደሆነ አስረድተዋል።
ነፍሰጡር እናቶች የሥነልቦና ክትትልም ሊደረግላቸው ይገባል። በተለይም የትዳር አጋር ባሎች የሚስቶቻቸውን ስብዕና በመንከባከብ ሊጠብቁላቸው ያስፈልጋል የሚሉት የሥነልቦና ባለሙያ የሆኑት አቶ ሻረው አለማየሁ፤ የሀገራችን እናቶች ካለባቸው ጫና የተነሳ በምቾት አርግዘው ላይወልዱ ይችላሉ። ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር መጋጨት አለያም መለያየት ሊከሰት ይችላል፤ በዚህ ወቅት ነፍሰጡር እናቶች ይጨነቃሉ። ይከፋቸዋል፤ ባይተዋርነት ይሰማቸዋል፤ ይሄ ተጽዕኖ በልጆቻቸው ላይ ጫና ማሳረፉ አይቀርም ይላሉ።
አቶ ሻረው እንደሚሉት፤ አምጠው የሚወልዱ እናቶች ለልጆቻቸው ያላቸው ፍቅር ከፍተኛ ነው።እስከ ሕይወታቸው ፍፃሚ መስዕዋትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። በቀዶ ጥገና የወለዱ እናቶች በዚህ መንገድ መውለዳቸው በራሱ የሚፈጥርባቸው ጫና አለ። ከዚያ አለፍ ሲል አምጠው አለመውለዳቸው የእናትነታቸውን ሚዛን የቀነሰው ያክል የሚሰማቸውም አይጠፉም፤ ማህበረሰባዊ እይታውም የሚወደድ ባለመሆኑ ተጽዕኖው ቀላል አይደለም። በመሆኑም አምጦ መውለድ በሥነልቦና ላይ የሚፈጥረው የእናትነት ጣዕም በእጅጉ የላቀ እንደሆነ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ሙሐመድ ሁሴን