ትምህርት ቤቶች ከቀለም መቅሰሚያነት ባለፈ የመልካም ዜጋ መፍለቂያ መሆን እንደሚገባቸው ይታመናል። ይሁን እንጂ አሁን አሁን ትምህርት ቤቶች የሚያፈሯቸው ተማሪዎች የብቃትና የሥነምግባር ችግሮች እንደሚስተዋሉባቸው በተደጋጋሚ ይሰማል። የችግሮቹ ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ በሚፈጠሩ፣ በሚስፋፉና የመማር ማስተማሩን ጤናማ ሂደት በሚያውኩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገናል። ለመሆኑ አዋኪ ተግባራት የሚባሉት ምን ምን ናቸው? መማር ማስተማሩን ሊያውኩ የሚችሉት በምን ሁኔታ ነው? በዘላቂነትስ ምን መደረግ ይኖርበታል? ለችግሮቹ መቀረፍ ከማን ምን ይጠበቃል? ስንል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል።
‹‹የትምህርት ቤቶችን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በማወክ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልምና ሥነምግባር ላይ አሉታዊ ሚና የሚያሳድሩ በርካታ ተግባራት አሉ። በዋናነትም በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የአደንዛዥ እጽ መሸጫዎች መበራከት፤ በአካባቢው የመጥፎ ሽታ መኖር፣ ለከፍተኛ ጫጫታና የድምፅ ብክለት መጋለጥ እና ሌሎቹም ሊጠቀሱ ይችላሉ›› ያሉት የዳግማዊ ሚኒሊክ አጸደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ዝማም ደስታ ናቸው።
ርዕሠ መምህሯ እንደሚሉት፤ የችግሮቹ ዓይነት፣ የሚፈጥሩት ተጽዕኖ መጠንና ስፋት ከትምህርት ቤት ትምህርት ቤት፣ከቦታ ቦታ እና ከማህበረሰብ ማህበረሰብ ይለያያል።
‹‹በትምህርት ቤታችን ተጨባጭ ሁኔታ የተማሪዎች የጽሕፈት መሳሪያ አሟልቶ መማር አለመቻል፣ ምግብ በተገቢው አለማግኘት(ተመግቦ አለመምጣት) እና በትምህርት ቤቱ መግቢያ በር በኩል ከሚገኙ መኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ሽታ ያላቸው ፍሳሾች በመማር ማስተማሩ ላይ ተጽዕኖ ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚህ ባለፈ በአዋኪነት ከሚነሱ የከፉ ችግሮች ትምህርት ቤቱ የጸዳ ነው›› ይላሉ።
ርዕሰ መምህርት ዝማም እንደሚሉት ለተማሪዎች ሥነምግባር እየተበላሸ መምጣት በትምህርት ቤት ዙሪያ ከሚፈጠሩ አዋኪ ተግባራት ባሻገር ወላጆችም የራሳቸው አስተዋፅኦ አላቸው።
‹‹ከትምህርት ቤቶች ፍሬ ሁሉም ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንደመሆኑ መጠን ለውጤታ ማነታቸውም ሁሉም ጠንካራ ሥራ መሥራት ይገባ ነበር፤ ነገር ግን ቸልተኝነትና ምን አገባኝ ማለት በማህበረሰቡ ዘንድ በሰፊው ይስተዋላል። ሕፃናት የማህበረሰቡ ልጆች ተደርገው መወሰድ አለባቸው። ድሮ ድሮ ማህበረሰቡ ተማሪዎችንም ሆነ የትኛውም አካባቢ የሚገኙ ልጆች መጥፎ ሲሠሩ ገስጾና መክሮ ጥሩ ሲሠሩ አበረታትቶና ሸልሞ ያሳድግ ነበር። አሁን ላይ ምን አገባኝ የሚል ማህበረሰብ ተፈጥሯል። በዚህ የተነሳ የተማሪዎች ስነምግባር ልቅ ሆነ። ለትምህረት ቤቱ ማህበረሰብ ብቻ የልጆቻቸውን አደራ ሰጥተው ወላጆች ተዘናግተዋል›› ሲሉ ይወቅሳሉ።
‹‹በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የሚከናወኑ አዋኪ ተግባራት ለመማር ማስተማሩ እና ለተማሪዎች ሥነምግባር መበላሸት ዋና ጠንቅ ናቸው›› የሚሉት መሐመድ አደም፣ ቄራ የሚገኘውና ከ700 በላይ ተማሪዎች የሚስተናገዱበት ኮርዶሻ አካዳሚ (የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ) ርዕሰ መምህር ናቸው።
‹‹በተለምዶ አልማዝዬ ሜዳ ተብሎ የሚጠራው ስቴዲየም ግቢ ከስፖርት ማዘውተሪያነት ሙሉ በሙሉ ወደ ጫት መቃሚያነት፣ሽሻ ማጨሻነት፣ትምባሆ ማጨሻነት ተቀይሯል፤ ለቁጥር የሚያታክቱ ሕገ ወጥ ተግባራት መፈጸሚያነት እየዋለ ነው›› የሚሉት ርዕሰ መምህር መሐመድ፤በተጨማሪም በልማት ምክንያት የተቆፈረው ዋና መንገድ ባለበት ከቆመ ከዓመት በላይ ሆኖታል። በዚህ ምክንያት ወደ ትምህርት ቤት መተላለፊያው ከመዘጋቱም በላይ በገደሉ ውስጥ የተጠራቀመው የጎርፍ ውሃ በኃላፊነት ለተቀበልናቸው ተማሪዎች ደህንነት ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮብናል›› ብለዋል።
የቄራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቶፊቅ ተማም እንደሚሉት፤ ‹‹የግልም ሆኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሀገር የሚጠቅምና በሥነምግባር የተስተካከለ ትውልድ ዜጋን የማፍራት ታላቅ አደራ የተጣለባቸው ናቸው። ስለዚህ የልጆቻችንን ጤንነትና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥትም፣ የወላጆችም፣ የትምህርት ቤቶችም የጋራ ሥራ መሆን አለበት። የሚሠሩ መሰረተ ልማቶችን ሁላችንም የመደገፍ ኃላፊነት አለብን፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ሕጋዊ አሠራሩን ተከትሎ የጀመረውን መንገድ በወቅቱ መቋጨት አለበት። በአካባቢው ያሉት መንገዶችም ሆኑ ሜዳዎች ለማህበረሰቡ እንዲጠቅሙ ታስበው የተሠሩ ቢሆንም ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገላቸው ባለመሆኑ አሁን ላይ ለማህበረሰቡና ለተማሪ ልጆቻችን ጠንቅ ሆነዋል፤ በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊፈልግላቸው ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል።
‹‹የትምህርት ቤቶችን ተግባር የሚያውኩ ነገሮች ከውስጥና ከውጪ በትምህርት ተቋማት ዙሪያ ሊፈጠሩ ይችላሉ›› የሚሉት ርዕሰ መምህር ደሳለኝ ግርማ ፤ ‹‹ዕድገት በሥራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በልማት ምክንያት በፈረሰው ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የሚገኝ ሲሆን አካባቢው ከመፍረስ ባለፈ መልክ የያዘ ባለመሆኑ ለሕገወጥ ተግባራት መፈጸሚያነት ተቀይሯል›› ይላሉ።
‹‹ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ጥራት በያዘው ቁርጠኛ አቋም ምክንያት የትምህርት ቤቶች ከመታደሳቸው የተነሳ ምቹና ማራኪ የመማሪያ አካባቢ እየሆኑ ነው። የተማሪዎቻችንም የምግብና የመማሪያ ግብዓት ችግሮች መቃለል ችለዋል። የትምህርት ቤት የውስጥ ችግሮቻችን ብዙዎቹ በመቃለል ላይ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች በርካታ እና ዘርፈ ብዙ ናቸው። አካባቢው ከየት እንደመጡ ለማይታወቁ የጎዳና ተዳዳሪ አካላት መጠለያ ሆኗል። በዚህ የተነሳም ከወረዳው ትምህርት ጽሕፈት ቤት እና ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት ጋር በቅንጅት እየሠራን ቢሆንም የችግሮቹ ስፋት አቅም የሚጠይቁ ከመሆናቸውም ባለፈ ጊዜ የሚወስዱ በመሆናቸው መቅረፍ አልተቻለም። ስለዚህ የመማር ማስተማሩን ሂደት በማወክና በተማሪዎች ስነምግባር ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥሩ በመሆናቸው የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊያበጅላቸው ይገባል›› ሲሉ ርዕሰ መምህር ደሳለኝ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ማረጋገጥ ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስማማው እስተዚያው በበኩላቸው፤ ‹‹ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በዝግጅት ምዕራፍ ከተማ አስተዳደሩ ያከናወናቸው ተግባራት የትምህርት ተቋማትን የጥራት ደረጃ የሚያሻሽሉ ናቸው። በመንግሥትም ሆነ በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ዜጎች የሀገር ሀብት በመሆናቸው እኩል ምቹ የመማሪያ አካባቢ እንዲኖራቸው መሥራት ግዴታችን ነው። በመሆኑም ችግሮቹ መኖራቸው ልክ እንደዚህ በመረጃ ሲደርሰን መደበኛ የኢንስፔክሽን ጊዜውን ሳንጠብቅ ችግሮች ባሉባቸው አካባቢዎች ተገኝተን በማረጋገጥ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት ዕርምጃ ወስደን የምናስተካከል ይሆናል›› ሲሉ ተናግረዋል።
በተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋሉት የስነምግባር ክፍተቶችና የብቃት ችግሮች ለአንድ አካል የሚወረወሩ አይደሉም። በአንድ አካል ብቻ የሚስተካከሉም አይሆኑም። ስለዚህ ትውልድን የመሥራት ሂደት ጊዜ ብቻ የሚወስድ ሳይሆን በወላጆች(በአሳዳጊዎች) ፣ በአስተማሪዎች፣በማህበረሰቡ እና በመንግሥት መካከል ጥብቅ የሆነ አዎንታዊ ቅንጅትን ይሻል። በሁለንተናዊ ቁመናው የታነፀ ትውልድ በቅሎ ማደግ የሚችለው በጋራ አስተዋጽኦና በጋራ ጥረት ነው። በመሆኑም የመልካም ትውልድ መብቀያ የሆኑት ትምህርት ቤቶችና አካባቢያቸው ምቹና ከአዋኪ ድርጊቶች የፀዱ እንዲሆኑ እያንዳንዳችን የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ ህዳር 26/2012
ሙሐመድ ሁሴን