ለብዙ ሰዎች “ዓላማ” ከቃልነቱ ያለፈ በሕይወት ጉዞአቸው ትርጉም የለውም፡፡ የአንዳንዶቻችን የሕይወት ታሪክ ሸለቆ ደርሶ መቆም እንደተገደደ ከተራራ አናት ላይ እንደተፈነቀለ አለት ከዕለት ወደ ዕለት ከማናልፈው ሞት እስከምንደርስ ድረስ እንደመንከባለል ያለ ሂደት ነው፡፡
ሌሎቻችን ደግሞ ሕይወታችን በዓላማ የምንመራው እንኖርበታለን ያልነውን ዓላማ የሚገዳደሩ ሁኔታዎች እስካልገጠሙንና ኑሮ “አልጋ በአልጋ” እስካልሆነ ድረስ ነው፡፡ ዓላማቸው እና ግባቸው አድሮ መገኘት ከሆነው በየምዕራፉ ተግዳሮት ሲገጥማቸው ጎመን በጤና እያሉ መንገድ ከሚቀያይሩት ለየት ያለ ለዓላማቸው የጨከነ ማንነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች ግን አይጠፉም፡፡
ከእነዚህ መካከል የዛሬ እንግዳችን አንዱ ናቸው፤ ለዓላማቸው የጠነከረ አቋም ካላቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ ለረዥም ዓመታት በውትድርና ዓለም ውስጥ ቆይተዋል፡፡ የፖለቲካውን ስራ ሲሰሩ ነበር፤ በጤና እክል ከወታደር ቤት በጡረታ ከተገለሉ በኋላ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አሃዱ ብለው በመማር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡ በአገኙትም የቀለም ትምህርት ጋዜጠኛ በመሆን “ጦማር” በተባለ የግል ጋዜጣ ላይ ለ6 ተከታታይ ዓመታት ከጀማሪ ሪፖርተር እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት በመሆን ሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በጅግጅጋ ክልል ትምህርት ቤት በመክፈት ትውልድን የመቅረጽ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ፤ የዛሬ የ“ሕይወት እንዲህ ናት” እንግዳችን መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ወልደ ትንሳይ ናቸው። ከእሳቸው ጋር ያደረግንውን ቆይታ እነሆ አልን፤ መልካም ንባብ!
ልጅነት
የተወለዱት በአዲስ አበባ በተለምዶ ቅድስት ማሪያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ለውትድርና ልዩ ፍቅር እንዳላቸው የሚናገሩት መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ከወላጅ አባታቸው ከአቶ ወልደትንሳይ መንገሻ እና ከእናታቸው ወይዘሮ አጸደ መንገሻ ነሃሴ 13 ቀን 1961 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ውልደታቸውንና ኑሮአቸውን በጀመሩበት በአዲስ አበባ ከተማ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ከቀለም ትምህርት ጋር ትውውቅ አድርገዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው አፄ ካሌብ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡
የአንደኛ ክፍል ገና ከመጀመራቸው ወላጅ እናታቸው በስራ ምክንያት ወደ ጫንጮ ያመራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ክፍለገብርኤልም ወላጅ እናታቸውን በመከተል ለስራ ወደ ተመደቡበት ጫንጮ ከተማ በማምራት በዚሁ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተከታትለዋል፡፡ እናታቸው በጫንጮ ከተማ ያላቸውን ስራ በመጨረሳቸው ምክንያት ኑሮአቸውን ወደ ተወለዱባት አዲስ አበባ ከተማ አደረጉ፡፡
የያኔው ታዳጊ ክፍለገብርኤል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ይመደባሉ፡፡ ለውትድርና ትልቅ ፍቅር ያላቸው መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ይህንን ተቋም ለመቀላቀል የትምህርት ማስረጃቸውን በማስገባት መጠባበቅ ይጀምራሉ፤ በወቅቱ ከአመለከቱ ሰልጣኞች መካከል ባላቸው ውጤት ተመርጠው በዛን ወቅት ሀረር ሚሊታሪ አካዳሚ ይባል የነበረው ማሰልጠኛ በመግባት ለሶስት አመት “የካዴት” ስልጠና በመውሰድ በምክትል መቶ አለቃነት እና በፖለቲካ ሰራተኝነት ተመረቁ፡፡
የስራ ጅማሮ
ከሀረር “የሚሊተሪ”አካዳሚ ከተመረቁ በኋላ በምድር ጦር ሰራዊት የጥይት እና እደላ ፖለቲካ ሃላፊ ሆነው ነበር የመጀመሪያ ስራቸውን አሀዱ ያሉት፡፡ ሃላፊነትን መሸከም የጀመሩት በ19 ዓመታቸው ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነበር፡፡
በተመደቡበት ክፍል ስራቸውን በትጋት እየሰሩ የነበሩት መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል፤ አለቆቻቸውም የመቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ያላቸውን ትጋት እና ታታሪነት በማየት እየተዘዋወሩ እንዲሰሩ መረጧቸው፤ ታዲያ በዚህም ምክንያት በሃያ አምስተኛ ክፍለ ጦር ጎንደር፣ በሃያ ስድተኛው ክፍለ ጦር በባህር ዳር ከዚያ በአንድ መቶ ሰላሳ ስድስተኛ ብርጌድ በሚባለው የአንድ ሺህ አለቃ የፖለቲካ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል፡፡
በዚያን ወቅት በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በመሆን አገርን የማዳን ስራ ሲሰሩ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን በሰሜኑ ክፍል በነበረው ጦርነት እሳቸውም የኢትዮጵያን ጦር ወክለው ተሰላፊ ነበሩ። በወቅቱ በነበረውም እልህ አስጨራሽ አውደ ውጊያ በሰሜን ጎንደር ከአምባ ጊዮርጊስ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ገደብዬ በተባለች ቦታ ተመትተው ቆሰሉ፡፡ ጉዳታቸውም ከፍ ያለ በመሆኑ ለተሻለ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተላኩ፡፡
በአዲስ አበባ ህክምናቸውን ቢከታተሉም ጉዳታቸው ከፍተኛ ነበርና ጨርሰው መዳን አልቻሉም። ስለዚህ በጡረታ ተገለሉ። በዚህ ምክንያት የውትድርና ህይወታቸው ተቋጨ፡፡ ከዚህ በኋላ ህይወት ሌላ መልክ ያዘች፡፡ በነበራቸው ውጤት ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመግባት “ጂኦግራፊ” ትምህርትን በማጥናት ዲፕሎማቸውን በ1988 ዓ.ም ያዙ፡፡ በወቅትም የግል ሆና በተቋቋመችው “ጦማር” ጋዜጣ ላይ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት በመመደብ የጋዜጠኝነት ስራ ሰርተዋል፡፡
ትምህርታቸውን በመቀጠል በ“ጂኦግራፊ” የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ2000 ዓ.ም ያገኙ ሲሆን በትምህርት አስተዳደር ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በ2003 ዓ.ም አግኝተዋል፡፡
ሶስት ጉልቻ
ቤተሰብ የህብረተሰቡ ዋና ምሰሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜው ድረስ በሕግና እና ስርዓት መመራት ይኖርበታል፡፡ የቤተሰብ መመስረቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ ባወጣው ሕግ መሠረት መመሥረት ይኖርበታል፡፡
እናም መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል የመሰረቱት ትዳር አስተማሪ መሰረቱ በህግም በፍቅር የጸና ነው፤ የክፍለገብርኤል የትዳር ጅምሮ እንዲህ ነው፤ መቶ አለቃ ከቆሰሉ በኋላ አዲስ አበባ አምስት ኪሎ አካባቢ መጥተው መኖር ጀመሩ፤ በጡረታ ስለተገለሉ ከሚያገኟት የጡረታ ክፍያ በስተቀር ምንም የላቸው፤ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ጉዳቱም ከፍ ያለ በመሆኑም የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በክራንች (በመደገፊያ) ነበር፤ ታዲያ የሰፈሬ ልጅ የሚሏት የአሁኗ ባለቤታቸው ምንም ሳታይ በፍቅር ለፍቅር ልትኖር ወደ መቶ አለቃው ህይወት እንደመጣች ይናገራሉ፡፡ በ1994 ዓ.ም የተመሰረተው ትዳር በፍቅር እና በትጋት ከነበረበት ከብዙ የዝቅታ ህይወት ተሰቶ አሁን ወደደረሰበት የሀብት ማማ ላይ ወጣ፡፡ አገኘዋለሁ ብለው ያልተመኙትን ህይወት በጥራታቸው ደግሞም በጥንካሬያቸው አገኙት።
ባለቤታቸውን “ጀግናዋ” በማለት የሚያደንቁት መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ‹‹ከዚያ መጥፎ የጨለማ ዘመን ወጥቼ ብርሃን እንዳይ ያደረገችኝ የብዙ ስኬቶቼ፣ የመነሳቴ ሚስጥርም ናት›› በማለት ነበር የትዳር አጋራቸው በሚገርም የተከሸኑ ቃላት የሚገልጿት፡፡ መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል በሚያስደንቅ የፍቅር ቃል ከሚገልፅዋቸው ባለቤታቸው ወይዘሮ ኤልሳቤት ሙሉጌታ አንድ ወንድ አግኝተዋል፡፡ የመቶ አለቃ እና የወይዘሮ ኤልሳቤት በጋብቻ አስራ ሰባት ዓመት በጓደኝነት አስራ ሁለት ዓመት በአጠቃላይ ሃያ ዘጠኝ ዓመት የቆየ ግንኙነት አላቸው፡፡
መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ከትዳር ህይወታቸው ተሞክሮ እንዲህ ይላሉ፤ “የእኔ የጓደኝነት ግንኙነትም ሆነ የትዳር ህይወት እንዲጸና የረዱኝ ነገሮች እምነት እና ፍቅር ናቸው፡፡ ወጣቱ ትዳሩ እንዲጸናለት ከፈለገ ሲያገባ በምክንያት እና ሚስት ልትሆነው የምትችለውን ሴት በመምረጥ መሆን አለበት፤ ማንኛውም ወጣት ትዳር ሲመሰርት ቀጣይ ለሚመራው ህይወት ሃላፊነት መሸከም እችላለው ወይ የሚለውን ጥያቄ ለራሱ በመጠይቅ በስነልቦናም ዝግጅት በማድረግ ወደተከበረው ትልቁ ተቋም መግባት ይኖርበታል፡፡” ብለዋል። የትዳርን ኩቡርነትን ሲገልጹ። ትዳር ጸንቶ እንዲቆይም መተሳሰብ፣ ፍቅር፣ መቻቻል ዋነኛ መሰረቶች መሆናቸው ይናገራሉ። ስህተቶች ሲኖሩ መተራረሙ፣ ጥፋት ሲፈጸም ይቅርታው፣ ለነገ አርቆ ማሰቡ፣ በዕቅድ መመራቱ፣ ለነገ የተሻለ ህይወት ነውና ለትዳር እነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው።
ሌላኛው የስራ ህይወት
ይመሻል ይነጋል፤ ይነጋል ይመሻልም፡፡ ይህን ሂደት ማን ሊገታ ይቻለዋል? በዚህ ሂደት ውስጥ የአንድን ስጋ ለባሽ ሕይወት የሚያስጨንቅ ከተራራ ናዳ በላይ ጨፍላቂ ሸክም ምን አለ? ከቀንበር በላይስ ምን አንገት የሚያስደፋ ይገኛል? ፈጣሪ እና ዕድል ከጎኑ ከቆሙለትና የተጋረጡበትን ፈተናዎች እንደ አለፈ ክረምት የሚያስቆጥር ጸጋ ከተሰጠው ያ ሰው በስተቀር! መቶ አለቃ ክፍለገብርኤልም “የሆነባቸውና የሆነላቸው” ይኼንኑ ይመስላል፡፡
መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል በአሁኑ ወቅት በጅግጅጋ ከተማ በትምህርት ኢንቨስትመንት መስክ ተሰማርተው ይገኛሉ፤ ከተጋቡ ከአንድ ዓመት በኋላ ትምህርት ቤት ለመክፈት ሲያስቡ የነበራቸውን ጥሪት በመያዝ ከመሃል ከተማ መውጣት እንዳለባቸው ወሰኑ። የት ብንሄድና ብንሰራ ራሳችንን፣ ወገንና ሀገራችንን እንጠቅማለን የሚለውን አወጡ አወሩዱ፤ ከባለቤታቸውም ጋር መከሩ። አቅማቸውንም አገናዘቡ። እናም አንድ ውሰኔ ላይ ደረሱ። ቀድሞም አገርንና ህዝብ ማስቀደም ተግባራቸው የሆነው መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል በወቅቱ ትምህርት ወዳልደረሰበት የጅጅጋ ከተማ አመሩ፡፡
በአጠራቀሟት እና በተበደሯት በአጠቃላይ 16ሺ ብር አሃዱ ብለው የቅደመ መደበኛ ትምህር ቤት (ኬጂ) በመክፈት ስራ ጀመሩ። “በእርግጥ” ይላሉ መቶ አለቃ “ስራውን ስንጀምር ገንዘቡም ሆነ ሁኔታው በቂ ሆኖ ሳይሆን እንሰራለን፤ ህብረተሰቡን እንጠቅማለን እኛም እንጠቀማለን በማለት ነበር፡፡”ታዲያ ይህ የሁለቱ ባለዕራዮች ትጋት እና ነገን ማየት ተጨምሮበት ከአንድ ሺ ሶስት መቶ በላይ ተማሪዎችን በመያዝ “ ዘ ስፓርክ አካዳሚ” በሚል የንግድ መጠሪያ ስም ትምህርት ቤት ከፈቱ። ይሄ ጅምር ዛሬ አድጎ ከቅድመ መደበኛ እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡
ዓለም በፈጣን ለውጥ ላይ ነው፡፡ በዚህ የለውጥ ሂደት ለመሳተፍና ለመጠቀም፣ ዜጎች ጊዜውን የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት ሊኖራቸው ይገባል። ዘመኑ የፈጠራ ነው፡፡ ከምንም በላይ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ያለ ዕውቀትና ክህሎት ይጠይቃል። አገራችን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስር የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅማ ወደ ተሻለ የልማት ደረጃ ለመድረስ፣ ሰብዓዊ ሀብቷን ማዳበር ይኖርባታል። ለዚህ ደግሞ የተማረ ዜጋ ያስፈልጋል፡፡ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ፣ የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ በጣም ሰፊና ውስብስብ ነው፡፡
ይህን ችግር ለመፍታት ደግሞ የመንግስት ጥረት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የግል ባለሀብቶች እና የማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ በመተባበር እንደ ተራራ የገዘፈውን ችግር መናድ መጀመር ይኖርባቸዋል። መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ከነዚህ አጋዥ አካላት ውስጥ አንዱ በመሆን የሚመደቡ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው፡፡ የግል ጥቅምን ሊያረኩ ከሚችሉ የንግድ እንቅስቃሴዎች በላይ አዕምሮን ማልማትና ትውልድ መቅረፅ ላይ መሰማራት ትልቀ ሀላፊነትን የሚጠይቅ ነው። ትውልድን በዕውቀት በስነምግባር መቅረጽ ሌሎች ሸቀጦችን ሸጦ እንደማትረፍ ቀላል አይደለም። ትልቅ ክትትልን ይጠይቃል። ልፋት አለው ግን ደግሞ ውጤቱን በተማሪዎች ላይ ማየት ሲቻል የሚያስደስት ዘርፍ ነው። በዚህም ልፋትና ጥረታቸው ስኬት እያስመዘገቡ ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ።
በአስራ ስድስት ሺህ ብር የተከፈተው ትምህርት ቤት አሁን በውስጡ ለስልሳ ሰባት ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ወደ 450 ሺ ብርም ለሰራተኞች ደሞዝ እንደሚከፍሉ መቶ አለቃው ክፈለገብርኤል ይናገራሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ፤ ለመንግስት ግብር በወር ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያደርጉም ጠቅሰዋል፡፡
“እኔ የምመራው ትምህርት ቤት በአብዛኛው በውጤትም በስነ ምግባርም የተመሰከረለት ነው፤ ለዚህ ትልቁ ምክንያት እኔ ወታደር ነበርኩ። ወታደር ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ለህብረተሰቡ ሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና ነው፤ ስለዚህም ይህ መርህ በልቤ ስላለ ሌብነትን በመከላከል፣ ሁሉም ተማሪ በራሱ የበቃ ሆኖ እንዲወጣ እየሰራን ነው ” አሁን ይናገራሉ መቶ አለቃው በትንሹ ሲሰርቁ ዝም ያልናቸው ልጆች ናቸው በአገር ደረጃ በመሾም የአገሪቱ ዕድገት ላይ ትልቅ ጠባሳ እየጣሉ ያሉት፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ስርቆትን ተጠይፈው ማደግ አለባቸው። በስነምግባር የተኮተኮቱ፣ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ሆነው መቀረጽ አለባቸው። እኔም ይሄንን እያሰብኩ ነው ተማሪዎቼ እንዲበቁና ሙሉ እንዲሆኑ የምሰራው።
የትምህርት ዘርፉ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መምራት አለመቻሉን የሚያመላክቱ ጥናቶች በተደጋጋሚ ሲወጡ ተመልክተናል፡፡ የመማሪያ መፅሐፉ ይዘት የተደጋገመ መሆን፣ አቀራረቡ ከዓላማው ጋር መቃረኑ እና የትምህርቱ መርሀ ግብር የሚመራበት በቂ አደረጃጀትና አሰራር አለመኖርን የዘርፉ ቁልፍ ችግር እንደሆነም ይገለፃል። በተለይ ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በአመራር ድክመት የሚጠበቅውን ውጤት አላስገኘም የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል።
የተማሪዎችን ስነ ምግባር ለመከታተል የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት እስካሁን አለመዘርጋቱንም ጠቋሚ ጥናቶቹ በተለያየ ጊዜ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የስነ ምግባር ትምህርትን ጉዳይ የመምህራን ኃላፊነት ብቻ አድርጎ መቁጠር፣ በመምህራን፣ በተማሪዎችና ወላጆች መካከል ያለው ግንኙነት የላላ መሆኑም ከሚነሱት የዘርፉ ተግዳሮቶች ውስጥ ናቸው። ታዲያ መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ይህ አገራዊ ችግር ነው ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ከዚህ የሚከተለውን ሃሳብ በማንሳት ትውልድን ማረቅ ብሎም በጥሩ ስነ ምግባር እና እውቀት ማነፅ የሁሉም ድርሻ ነው የሚል ጠንካራ ሃሳብ ያነሳሉ።
ባለታሪኩ ስለ ግል ጥረታቸው ሲናገሩ ‹‹ የትምህርት ስራ የጋራ ስራ ነው›› ይላሉ። ኩረጃን፣ ብቁ ያልሆኑ ተማሪዎችን ወደ ቀጣይ ክፍል ማሳለፍ፣ በስነ ምግባር ብልሹ የሆኑ ትውልዶችን እንዳይወጡ አጥብቀው እንደሚሰሩም ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሃሳብም ሆነ በድርጊት ልህቀት ላይ ደርሰው የሚገኙ ተማሪዎችም በክልሉም በአገርም ደረጃ ማፍራት እንደተቻለ ያስረዳሉ፡፡ ሁሉም ይህን መሰል አገራዊ ሀላፊነት መውሰድ እንደሚኖርበት ይናገራሉ። የዚህ ሁሉ ድምር ደግሞ በስነ ምግባሩ የሚያስመሰግን፣ የተሻለ ትውልድ እና አገሩን ከስልጣኔ ጫፍ ላይ እንድትደርስ የራሱን ጉልህ ሚና የሚጫወት እንዲሆን ያስችለዋል የሚለው ጠንካራ እምነታቸው ነው።
ችግር እና ስኬት
“ማንኛውም ህይወት አልጋ በአልጋ አይሆንም፤ እኔም የገጠመኝ ከህይወት መንገዶች ብዙዎችን ከሚገጥሙ እክሎች አንዱ ነው፤”ፈተና ሲመጣ ሊያጠፋኝ ነው ብሎ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ህይወትንም በተለየ መንገድ የምናይበት አንዱ አቅጣጫ ማስቀየሪያ ነገር ሊሆን እንደሚችል አድርጎ ማሰብ ያስፈልጋል። ከችግሩ በሻገር ያለው ስኬት ጋር ለመድረስ እና ያንን ለማማተር ያነሳሳል፡፡ ከማንኛውም ሰው ወይም ድርጊት ጀርባ በሕይወት ሂደት የተቋጠረ እውነት፣ እምነት፣ አመለካከት… አለ፡፡
መቶ አለቃ ክፍለገብርኤልም እንደሚሉት በወታደር ቤት አገኘሁት ያሉት ትምህርት “የስልጠናው ጥንካሬ ውጊያውን ያቀለዋል” ወይም ይላሉ “ላብ ደምን ያድናል” ይህ መርህ ከብዙ ልፋት እና ድካም በኋላ ያለውን የሰውን ልጅ ስኬት የሚያሳይ አባባል ነው፤ እሳቸውም ይህንን መርህ ተጠቅመውበት ለውጤት እንደበቁ ገልጸዋል፡፡ መቶ አለቃም በትምህርት ኢንቨስትመንት ላይ ከተሰማሩ በኋላ ያጋጠማቸው ችግር ሲናገሩ “ያልሰራበትን ለመቀበል የሚሮጥ ተማሪ፣ የትምህርት ባለሙያ፣ አንዳንድ በከተማዋ ያሉ የስራ ሃላፊዎች…በብርቱም ፈትነውኛል፤ ብዙ ችግር አድርሰውብኛል፡፡”ይላሉ።
ወታደር መሆናቸው እንደጠቀማቸው የሚናገሩት መቶ አለቃ በትዕግስት፣ በብልሃት እንዲሁም አንዳንድ ጦር ቤት እያሉ የተማሩትን የትግል ስልት በመጠቀም ችግሮችን አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል፡፡ እንዲሁ ጥቅል በአደርገው ይሻላል የሚሉት መቶ አለቃ አንድ ነገር ላይ ግን አትኩሮት መስጠት እንደሚፈልጉ ነገሩን። ይህም ሙስናን የሚጠላ ተማሪ፣ ሰራተኛ እንዲሁ የመንግስት ሃላፊ እንዲፈጠር፤ እንዲሾም መልካም ምኞታቸው መሆኑን አጫወቱን፡፡ ሆኖም ዓላማ አላቸው እና ችግሩን ተቋቁመውታል። መፍትሄ ላሉትም መፍትሄ እየሰጡ ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ደርሰዋል። ነገ ደግሞ ደምቆ የሚታይ ብርሀን ከፊት ለፊት አለ። ብርሀኑ ላይ ለመድረስ አሁንም ሳይታክቱ ይሰራሉ። የሰራ ያሸንፋል። ይሄንን በራሳቸው አስመስክረዋል።
እንግዳችን በወታደርነት ከደረሱበት ስኬት በአሻገር በዋነኛነት ያገኙት ስኬት በትምህርት ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ያመጧቸውን ለውጦች እና የሰሯቸው ስራዎች ናቸው፡፡ “የመምህርነት ስራ ከምንም ጋር ያልተነካካ ድንቅ የሆነ ትውልድ የማፍራት ስራ ነው፤ ስራው በራሱ እርካታን የሚፈጥር ሲሆን አስተምረሃቸው ደግሞ በክልሉ በተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ሆነው አገርንም ክልሉን ሲጠቅሙ ሲታይ፣ በተለይ ደግሞ በጤናው ዘርፍ ላይ የህክምና ባለሙያ በመሆን ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ከሞት ሲታደጉ ማየት ከዚህ በላይ ምንም ዓይነት ስኬት የለም፡፡ ”በተለይ ይላሉ መቶ አለቃ” በከተማው ብሎም በክልሉ የትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነት እና ተሳትፎ እንዲመጣ የሰራናቸው ስራዎች እጅግ ደስ የሚለኝ ደግሞም ለውጥም ውጤትም ያመጣንበት ነበር፤ ይህም እንደ አንዱ ስኬቴ እቆጥረዋለው፡፡”
ሌላኛው “ከእኔ” ከሚል ወጥቼ ከስልሳ ሰባት በላይ ለሆኑ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጥሬ ሌላው ስኬቴ ነው ያሉ ሲሆን በክልሉ ሆነ በከተማ ትምህርት ቤታቸው ለአበረከተው አስተዋፅዎ የተለያዩ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውም ተጨማሪ የስኬታቸው መገለጫ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ምክር
ይህንን እድል ከአገኘሁ የሚያስጨንቀኝና እንቅልፍ የሚነሳኝ ጉዳይ አለ። በተለይ አሁን አገሬ ያላችበት ሁኔታ ያሳስበኛል፤ እዚህ ላይ አስተያየት ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ብለውናል መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል። እኛም ይሄው ዕድሉ ብለን መድረኩን ከፍተናል። ቀጠሉ እሳቸውም “እናንተ ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአገር አንድነት፣ ለሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እመክራለሁ” አሉ።
እውነት ነው ከምንም ነገር በፊት መቅደም ያለበት የሀገር ሰላም ነው። አረጋውያኑ ተጡረው፤ ቢታመሙ አስታማሚ አግኝተው መኖር የሚችሉት እና ሲሞቱም በክብር የሚቀበሩት የሀገር ሰላም ሲኖር ነው። ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተምረው ለቁም ነገር የሚበቁት ሀገር ሲኖር ነው፤ ሀገርም ሀገር የምንለው ሰላም ሲሆን ነው።
ሰላም ለመፍጠር እና ውጤታማ ከማድረግ አንፃርም የሀገር ሽማሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ሚናቸውን በተሻለ ቢወጡ፤ አገራችን ያጋጠማትን ችግር ሁላችንም የድርሻችንን በመውሰድ በመላው ሀገራችን ሰላም እንዲጎለብት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡ የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ትስስር ማጠናከር ይገባናል፤ ተሳስበንና ተደጋግፈን መኖር አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “እንደ ሀገር ከመሬት አንድነት በላይ የህዝብ አንድነት ነው የሚያስፈልገን”ብለዋል። ይሄንን ደግሞ ወጣቱ መገንዘብ አለበት። አርቆ አስተዋይ መሆን ይጠበቅበታል።
ችግሮቻችንን ተመካክረንና ተነጋግረን በመፍታት የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በተለይ እኔ አሁን ስራ በምሰራበት ከተማ እንዲሁም በሀገሪቱ አካባቢ ሰላም ማስፈን ለሀገሪቱ ሰላምና ልማት ወሳኝ ነው፤ ስለሆነም በቅንነት መንቀሳቀስና ችግሮችን መፍታት ይገባናል ብለዋል
መቶ አለቃ ክፍለገብርኤል እንዳሉት ይህንን ችግር ፈተን በመላው ሀገራችን ሰላም እንዲጎለብት የበኩላችንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በመነጋገር መፍታት ይገባናል። ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል ሳይሆን ለአገር አንድነት የተፈጠሩ ችግሮችን በመፍታት የህዝቦች አንድነትና አብሮነት ትስስር ማጠናከር ያስፈልጋል፤ ተሳስበንና ተደጋግፈን መኖር አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ማጠቃለያ
የመቶ አለቃ ክፍለገብርኤል ሕይወት በአንድ በኩል ግልጽ የሚታይ የሚጨበጥ ነው፤ በሌላ በኩል ረቂቅ የህይወት ቀለማት ውሕድ ነው፤ ለሁሉም እንደ ዓይነ ልቡናው አቅም መጠን የሚገለጥ የሚሰወርም ነው፤ የታመቀም፣ የተዘረዘረም ነው፡፡ ስለሆነም ልክ እንደ ቀስተዳመና “የማሪያም መቀነት”ያለ ምንም ጥያቄ ጠቅልለው መርጠው ሊላበሱት የሚወዱት የመኖራቸውን ያህል አከራካሪ ውህዱ እየፈተናቸው በሩቁ ቆመው ብቻ እንዲታዘቡት ያደረጋቸው አይጠፉም፡፡ ነገር ግን ጠጋ ብለው ሲመረምሩት የመቶ አለቃ ክፍለገብርኤል የሕይወት ጉዞ ዘርፈ ብዙ ቀለማት ያሉት ቢሆንም ህብሩ አንድ ወጥ ነው፡፡ እምነት፣ መስጠት ፣ቀጥተኛነት ነው። ልባምነት፣ ምልስነት፣ ባለ አዕምሮአዊነትም ነው። የዓላማ ቁርጠኝነት፣ የጥንቁቅነትና ርኅራኄ ነው፡፡ የመቶ አለቃ ህይወት ጉዞ እንደ ብዙነቱ የተበታተነ አይደለም።
የግል የህይወት ፍልስፍና የአኗኗር ስርዓት በጥንቃቄ የተደረጀ ነው፡፡ ስለሆነም መዝገቡን ከፍቶ ቅጠሎቹን ሳይሆን አንጓዎችን መርጦ ማገጣጠም ከመቶ አለቃው የህይወት ጉዞ ያስተምረናል።
እኛም ለመቶ አለቃ ክፍለገብርኤል በቀሪው ህይወታቸው መልካም የስራ እና የስኬት ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኘን፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2012
አብርሃም ተወልደ