ተሽከርካሪው እና ተሳፋሪው እጅግ በርካታ ነው፡፡ የቢሾፍቱ፣ የዱከም፣ የሞጆ፣ አዳማ፣ ዝዋይ፣ ሻሸመኔ፣ ሀዋሳ.ወዘተ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማስተናገጃ እንደመሆኑ ከፍተኛ እና መካከለኛ አውቶብሶች እንዲሁም ሚኒባሶች በአይነት በአይነት ይስተናገዱበታል፡፡
መናኸሪያውን ላለፉት አራት ዓመታት በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ ሁሌም ያው ነው፡፡ ከዓመት ዓመት መሻሻልና ለውጥ አይታይበትም። በክረምት ጭቃው፣ በበጋ አቧራው አይጣል ነው – የቃሊቲ መናኸሪያ፡፡
በዘመናዊ መንገድ እንደሚገነባ ሲገለጽ ዓመታት ቢያልፉም፣ ይህ ግን እውን መሆን አልቻለም፡፡ጽዳትና ውበት ዞር ብሎበት አያውቅም፡፡ ለመንገደኞች የሚሆን ደረጃውን የጠበቀ መጠለያ፣ መጸዳጃ ቤት፣ የካፌ አገልግሎት የለውም፡፡ ሁሉም አገልግሎቶቹ ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሠሩ ጊዜያዊ ቤቶች ነው የሚከናወኑት፡፡ በዚህ የተነሳም በክረምት ቅዝቃዜው በበጋ ሙቀቱ እያድርስ ነው ሲሉ ተሽከርካሪዎች እና የመናኸሪያው ሠራተኞች ይጠቁማሉ።
የኬቢክ ተሽከርካሪዎች ማኅበር አሽከርካሪ አቶ ሓለፎም ታደሰ በሥራቸው ተዘዋውረው ከተመለከቷቸው በርካታ መናኸሪያዎች የቃሊቲው መናኸሪያ አንዱ ነው፡፡ መናኸሪያው ለአዲስ አበባ ከተማ ጨርሶ እንደማይመጥን የሚናገሩት አቶ ሓለፎም፣ በክልል ከሚገኙ መናኸሪያዎች አንጻርም ሲታይ ደረጃውን የወረደ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ከተለያየ አካባቢዎች አገልግሎቱን ፍለጋ የሚመጡ መንገደኞች ከውጪ በማየት ብቻ መናኸሪያ መሆኑን ሲጠራጠሩ ማስተዋላቸውን ይገልፃሉ። የመናኸሪያው ምድረ ግቢ በአዲስ አበባም ሆነ ከክልል ከተሞች ተመሳሳይ አገልግሎት ከሚሰጡ መናኸሪያዎች ጋር ጨርሶ ሊወዳደር እንደማይችል ነው የሚገልጹት፡፡
አቶ ሓለፎም የመናኸሪያው ምድረ ግቢ በአስፋልት ኮንክሪት አለመሠራቱ ለሰዎችም ለተሽከርካሪዎችም እንቅስቅሴ ማስቸገሩን ጠቅሰው፣ አቧራው እና ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ቤት የሌለው መሆኑም የጤና ችግር እንደሚያስከትል ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ደረጃውን የጠበቀ መናኸሪያ መሠራት አለበት ሲሉም ያመለክታሉ።
ሌላው አሽከርካሪ አቶ የሱፍ ሐጂ ሱልጣን የቃሊቲ መናኸሪያ በርካታ መንገደኞችና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የሚስተናገዱበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአሽከርካሪዎች፣ ለሠራተኛውና ለተሳፋሪዎችም ታስቦ ጥገና ሊደረግለት ይገባል ይላሉ። መናኸሪያው የአሽከርካሪዎችን፣ የሠራተኞችንና የተሳፋሪዎችን ምቾት እንደሚነሳ፣ በተለይ በበጋ ወቅት አቧራው በክረምት ወቅት ደግሞ ጭቃው ፈተኝ እንደሆነም ያመለክታሉ፡፡
የመንገደኞችና ተሸከርካሪዎች ብዛትና የከተማው ደረጃ ከግምት ገብቶ ለጊዜውም ቢሆን ግቢው በአስፋልት ኮንክሪት ሊሠራ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡ አንድዬው አሽከርካሪዎችና ተገልጋዮች በጋራ የሚጠቀሙበት መጸዳጃ ቤት ፌስታልና ፕላስቲክ ጠርሙሶች እየተጣሉበት መሆኑንና መፍትሄ ሊፈለግለት እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
የመናኸሪያው መሬት ወጣ ገባነት በተሽከርካሪዎች ላይ ችግር እያመጣ ለጥገና ወጪ መዳረጋቸውንም አቶ የሱፍ ያመለክታሉ፡፡ መናኸሪያው ቢገነባ ከጥገና ወጪ እንደ ሚታደ ጋቸው፣ ሥራቸውንም በምቾት ለመሥራት እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ።
አንዳንድ ተሳፋሪዎችም መናኸሪያው መጠለያ እንደሌለው በአቧራውም ክፉኛ መማረራቸውን በመጥቀስ የአሽከርካሪዎቹን አስተያየት በመጋራት መናኸሪያው ትኩረት ተሰጥቶት ቢሠራ መንግሥት፣ ህዝብና ሠራተኞች እንደሚጠቀሙም ነው የሚናገሩት፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ይግዛው ዳኘው የአሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎችን ቅሬታ ይጋራሉ፡፡ መንግሥት መናኸሪያውን እንደ ሀገር ተምሳሌት ሊሆን በሚችል መልኩ ለማስገንባት መታቀዱን ያስረዳሉ። ለግንባታውም 445 ሚሊዮን ብር መመደቡን፣ ጨረታ ወጥቶ ውል ለመፈፀም ዝግጅት መጠናቀቁንና ዲዛይን መሠራቱንም ያመለክታሉ።
አቶ ይግዛው ለግንባታው ሥራ በያዝነው ዓመት 184 ሚሊዮን ብር በጀት ተፈቅዷል ይላሉ። የመናኸሪያ ህንፃ ግንባታውን በሁለት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱን፣ ግንባታውንም በተያዘው ዓመት በተመደበው በጀት የጨረታ አሸናፊ ከተለየ በኋላ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ