የአዛውንቷ የአዲስ አበባችን ዕድሜ በአንድ ምዕተ ዓመት ላይ 33 ዓመታትን ደምራ ከአንቺነት ወደ እርሶነት ተሸጋግራለች። ለስሟ ዳቦ ቆርሰው ያወጡላት እመት ጣይቱ ብጡል አይሆንም እንጂ ቢሆንማ ኖሮ ከዘላለማዊ እንቅልፋቸው ተቀስቅሰው በስም ያሽሞነሞኗትን ከተማ ዛሬ ማየት ቢችሉ ምን ሊሉ እንደሚችሉ ለመገመት ይከብዳል። እንደሚመስለኝ ግን ማራኪውን ስሟን በተመለከተ “ስምን መልአክ ያወጣል” ቢባልም ታሪክ በአክብሮት የመዘገበላቸውን ስያሜ ለቅዱሳን መላእክት አሳልፈው የሚሰጡ አይመስለኝም።
ከጣይቱ በፊት ተሽቀዳድመው ስሟን መላእክት ቢያወጡት ኖሮ እንደ ስሟ ባበበች ነበር በማለት ቁጭት ብጤ ሽው ይልብናል። ስም ያወጡላት ጣይቱም ቢሆኑ “አፈር መስኮት የለውም እንጂ” አዲስ አበባቸውን ቀና ብሎው ቢያስተውሏት ልክ እንደኛ ባይፀፀቱም መተከዛቸው ግን የሚቀር አይመስለንም።
“ወሸባ፣ ወሸቦ፣ ወሸቦ፣ ወሸቦ፣
ሀሜት ስም ሲያወጣ መች ይቆርሳል ዳቦ”
ተብሎ እንዳይዘፈንብን ሰጋን እንጂ አዲስ አበባችን ስሟና ግብሯ ከተቃርኖ ሊፋታ ያለመቻሉ ሁሌም እንዳስቆዘመን አለ።
“አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ እንዳርጋታለን!” በሚለው የወደፊታዊ ምኞት ጣይቱ ራሳቸው ደስተኛ የሚሆኑ አይመስለንም። በዕምቡጥነቷ ቀጭጫ ከምዕተ ዓመት በላይ በመኖሯ ንዴት እያበገናቸው ከባለቤታቸው ከምኒልክ ሞት በኋላ የነገሡትን አባ ጤና እያሱን፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱን፣ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን እዚያው በሰማይ ቤት ሰብስበው “ምነው ልጆቼ ከተማዬን ዘንግታችሁ ኖራችሁ!” በማለት ሐዘናቸውን ሳይገስጹአቸው የሚቀሩ አይመስለኝም። ደርግና ኢህአዴግም የፈጸሙት ኩነኔና በከተማዋ ላይ የሠሩት ጭቡ ጠንክሮባቸው ፍርዳቸው እንዲከብድ ለሚያምኗት “ወላዲተ አምላክ” መማጠናቸው የሚቀር አይመስለንም። አይመስለንም መሆኑ ይሰመርልን።
የብልፅግናውን ፓርቲ አዋላጅ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) እና የልጃቸው ልጅ የሚሆነውን ጎልማሳ የከተማችን ከንቲባን በተመለከተ ግን አዲስ አበባን ለማስዋብና ለማቆንጀት ለሚያደርጉት የቀን ተሌት ጥረት እንቱፍቱፍ እያሉ በእናት ቋንቋ ሳይባርኳቸው የሚቀሩ አይመስለንም። በተለየ ሁኔታ ግን ጠቅላዩ ቤተ መንግሥታቸውን አድሰው ስላሳመሩላቸውና ወደ ጥንቱ ሞገስ ለመመለስ ስለከፈሉት ዋጋ ከባለቤታቸው ከምኒልክ ጭምር ምርቃት ሳያዥጎደጉዱላቸው እንደማይቀር ውስጣችን ይመሰክርልናል።
ከእንጦጦ ጀምሮ ቁልቁል የተቀየሰውና ሥራው እየተፋጠነ ስላለው መንገድና መዝናኛ ሲሰሙማ በደስታ ፈንጥዘው ምን ብለው እንደሚመርቋቸው ለመገመት ይከብድ ይመስለናል። ምናልባትም “አንተ ቁምነገራም ልጄ ሺህ ዓመት ንገሥ” ብለው በዘመናቸው ምርቃት ወንበራቸውን ለልጅ ልጅ ሳይባርኩ የሚቀሩ አይመስለንም። ይህን ምርቃት የሚሰሙ ተስፈኛ የሀገራችን ፖለቲከኞች አኩርፈው ከሀገር እንዳይወጡ “የለም የተለመደ ምርቃት ስለሆነ እንጂ በዓለም ላይ ሺህ ዓመት የነገሠ የለም” እያልን እናረጋጋቸዋልን።
የእንጦጦን ጎዳና በተመለከተ አንድ ታሪካዊ ሁኔታ እግረ መንገድ አስታውሰን እንለፍ። ከባለቤታቸው ሞት በኋላ በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ሰበብ የምኒልክ ሹማምንት እቴጌይቱን ከቁም እስረኝነት ባልተናነሰ ሁኔታ ከመንግሥቱ ሥራ ገለል አድርገው እንጦጦ ከሚገኘው ቤተ መንግሥት እልፍኝ ውስጥ አግተዋቸው እንደነበር ከታሪክ ንባባችን ተረድተናል። እናም እሜቴ ጣይቱ ከደንገጡራቸው ጋር በመሆን በታገቱበት ግቢ ውስጥ ነፋስ ለመቀበል ወዲያ ወዲህ እየተንቀሳቀሱ በነበረበት አጋጣሚ ድንገት ለዓመታት ተከብረው የኖሩበትና ጊዜ ሲከዳቸው ጥለው የወጡት ታላቁ ቤተ መንግሥት ትዝ ሲላቸው በርቀት ተመልክተው ናፍቆታቸውን ለመወጣት ዓይናቸውን ወርወር ሲያደርጉ ከእንጦጦ ዳገት ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት የተዘረጋው መንገድ ወለል ብሎ ይታያቸዋል።
ይሄን ጊዜ ደንገጡራቸውን በቁልምጫ ስም በመጥራት “እቴ ይሄ መንገድ ወዴት የሚወስድ ነው?” ብለው ይጠይቋታል። ተጠያቂዋም በጥያቄያቸው ግር እንዳላት በሚያስታውቅ ቃና ፈጠን ብላ “እመቤቴ ሆይ ይህንን መንገድ እኮ ቆመው ያሰሩት እርስዎ ራስዎ ነዎት። የተዘረጋውም ከእንጦጦ እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት ነው።” ብላ ስትመልስላቸው ዓይናቸው እንባ አቆርዝዞ በትዝታ እንደተዋጡ እንዲህ መለሱላት ይባላል፤ “አዬ ልጄ ለካንስ ነበር እንዲህ ቅርብ ኖሯል!” ግሩም ተጠቃሽ አባባል – እሜት ጣይቱ ነፍስ ይማር።
እኛስ የ133 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ከተማችን የኖረችባቸውን የኋልዮሽ ጊዜያት እያብሰለሰልን ብሶታችንን ሁሉ ባንዘረግፍም ትዝብታችንን ለመግለጽ ያህል ብቻ “ነበር ለካንስ እንዲህ ቅርብ ነው” ብለን የ30 ዓመት ብሶታችንን ብንተርክ የእቴጌዋን አነጋገር ኮረጃችሁ ያሰኝብን ይሆን። ቢባልስ ምን አለበት? ምንጭ እስከጠቀስን ድረስ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ብንለማመድ የሚወቅሰን ማነው! በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በጠቅላዩ ጥረት የተከናወነውን አዲስ አበባን የማስዋብ ዘመቻን ጅምር እያደነቅንና ከትናንትናና ከትናንት ወዲያ ጋር እያነጻጸርን ብንዘምርስ ማን ከልካይ አለብን።
የጡብ ድርድር ሕንጻዎቻችን “አያዎ”
“አያዎ” (አይ+አዎ) የሚለው ቃል አሉታዊና አዎንታዊ ትርጉሞችን አንድ ላይ አጣምሮ የያዘ የሁለት ቃላት ጥምረት ውጤት ነው። የጥምረቱ ቃል ፈጣሪ የምናከብረውና የምንወደው መምህራችን የነበረው ደበበ ሰይፉ እንደሆነ በቃል ምስክርነት ሲመሰገን ሰምተናል። እርግጥ ነው ስለዚህ ምስክርነት ጸሐፊው ዳግላስ የጽሑፍ ማረጋገጫ ዋቢ አላገኝም። ደበበ ሳይሆን እኔ ነኝ የሚል የቃሉ ባለሀብት ለሙግት ከመጣ ንስሃ ገብተን ለመታረምና “የአእምሯዊ መብቱን” ለባለቤቱ ለማስረከብ ወደ ኋላ አንልም።
ሕንጻ በማብቀል ፍጥነት አዲስ አበባ ከተማን የሚወዳደራት ሌላ የአህጉራችን ከተማ ስለመኖሩ እንጠራጠራለን። አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ሌሊት በቅለው የሚያድሩ ሕንጻዎች ብዛት ያለ ምንም ማጋነን ከክረምት እንጉዳይ አበቃቀል ጋር ቢነጻጸር ግነት አይሆንም።
ትናንት የሠፈር ውሪዎች በልጅነት እድሜያቸው የሚቦረቁባቸው፣ ታዳጊዎች በጨርቅ ኳስ የሚፋለሙባቸው፣ ወጣቶች የሚሰባሰቡባቸው የሠፈር ውስጥ ሜዳዎች በአንድ ሌሊት ሰማይ ጠቀስ ወይንም እንደነገሩ የተውገረገሩ ሕንጻዎች ሲቆሙባቸው ሃይ ብሎ የሚቆጣ የከተማችን ሹም አጥተን ኖረናል። ዛሬስ ብናማ “ጌቶች ይቆጡን ይሆን!”
ለአረንጓዴ መናፈሻነት የተከለሉ የማህበረሰብ ቦታዎች “በእነ ሰው ጤፉ” በወረራም ሆነ በዘረፋ ወደ ግለሰብ ሃብትነት ሲዘዋወሩ እያየን ፈርተን ዝም ብለናል። “እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” እያልንም ሃሞታችንን አቅጥነን 27 ዓመታት አባክነናል። ለነገሩ ዛሬም እየባከነብን አይደል። ስለ ተግባራዊነቱ እንጃልን እንጂ በቀደም ዕለት ከንቲባችን የአረንጓዴ ቦታዎችን ለማስመለስ ቆርጠዋል ፣ ጉብኝትም አድርገዋል በማለት ሚዲያዎች ሹክ ብለውን ተስፋችን ማንሰራራት ጀምሯል። እንዳሉት ከሆነማ ስለት እናገባለን።
ሌላው አንገብጋቢ ጩኸታችን በስመ ሪል ስቴት (እኔ አንጡራ ሀብት ብዬዋለሁ) የሚሰራው ግፍ አንገሽግሾን ኡኡታችን መበርከቱ ነው። የሪል ስቴት ስም የደረቡ ጥቂት ቡድኖች የአፓርታማ እንቁልልጮሽ እያሳዩ ሕዝቡን የደም እንባ ሲያስለቅሱ ሃይ የሚላቸው መጥፋቱ ሌላ ሀዘን ጨምሮብናል። በአንድ ዓመት ቤቱን ሰርተን እናስረክባለን የሚል ተስፋ እየመገቡ የምስኪን ተስፈኞችን ገንዘብ ካጋበሱ በኋላ የቀጠሮው ጊዜ ሲደርስ የጡብ ድርድራቸው አግጥጦ እንደተገሸረ ከሀገር በመውጣት ባዕድ ምድር የሚሸሸጉ “አልሚ ተብዬ” እና ሕግን የጨፈለቁ ማንግዱዎች በከተማችን ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አይደለም። ጠቁሙ የሚል ቃል ከመሪ ጌቶቻችን አፍ ይውጣ እንጂ እንባችንን በመሃረባችን እያበስን ፒያሳ የሚገኘውን ቢሯቸውን በብሶተኞች ጎርፍ እናጥለቀልቀዋለን።
ከአሁኑ በፊት ለማንሳት እንደሞከርኩት ከጥቂቶች በስተቀር በርካቶቹ “የሪል ስቴት አልሚ ተብዬዎች” በሕዝብ አንጡራ ሀብት ላይ ለሚፈጽሙት ግፍ የከተማችን አስተዳዳሪዎች ለምን ጆሮ ዳባ ልበስ እንዳሉ ግራ ገብቶናል። የሪል ስቴቶችን ጉዳይ በተመለከተ “የመንግሥት ያለህ!” እየተባለ የሚጮኸው ጩኸት በማናውቀው ምክንያት ሰልሎብናል። መሬቱን ገምሶ የሰጠው ክፍል ለምን ለቁጥጥር እንደቦዘነም አልገባንም፡ በአጭሩ ገንዘቡና ቀብድ ቀድሞ የተበላባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የወፍ ጎጆ የአፓርትመንት ጅምር የጡብ ድርድሮች እዚያም እዚህም እንደፈራረሰ ከተማ ተፈረካክሰው መመልከት ለአዲስ አበቤ የተለመደ ሆኗል። በበርካታ ሳይቶች ላይ ጅምራቸው አርጅቶ መፈራረስ የጀመሩ ምስለ ሕንጻዎችን ማየትም እንግዳ አይደለም። ሚሊዮን ብሮች ከግለሰቦች ላይ እንደ አባይ ወንዝ ሲዘረፍ ሰሚ ጠፍቷል።
የከተማችን ከንቲባ እንደለመዱት ቆሞ ቀሮቹንና ደንበኞቻቸውን የሚያስለቅሱ “ሪል ስቴቶችን” በድንገቴ ጉብኝት ቅኝት አደረጉ የሚል ዜና የሰማን ዕለት እንደየእምነታችን ለፈጣሪ ስዕለት ማስገባታችን አይቀርም። ጥቁምታው ከረዳቸው “ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ” ያለው ድምጻዊ የአዲስ አበባን የትኛውን ክፍል ለማመልከት አስቦ ይሆን ብሎ መጠየቁ አይከፋም። እንደ ጸሐፊው እምነት “የሪል ስቴቶችን” እያሞካሹ የሚለፍፉ የሚዲያ ማስታወቂያዎች ልክ እንደ መጠጥ ማስታወቂያዎች በሕግ ቢታገዱ ደስታውን አንችለውም። ብዙዎቹ የሪል ስቴት አልሚዎች ውሸታሞች ብቻ ሳይሆኑ ጨካኞችም ጭምር ስለሆኑ፤ ማስታወቂያቸው በተግባራቸው ልክ እየተመዘነ ቢተላለፍ ክፋት የለውም። ሰሚ ከተገኘ።
የአዲስ አበባ የጡብ ድርድር ጫካዎች ጉዳይ ብዙ ያነጋግራል። ነገራችንን ወደ ሌላ ጉዳይ ለጠጥ አድርገን እንመልከት። የአዲስ አበባ ከተማ “አይ” እና “አዎ” ተቃርኖ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች መካከል የኮንዶሚኒዬም የጡብ ድርድሮች ጉዳይም በቀዳሚነት ይጠቀሳል። በድሃ ከተማ ቢሊዮን ብሮች ሆጨጭ እየተደረጉ የተገነቡት የኮንዶሚኒዬም ሕንጻዎች “ኡኡታ ያሰኛል!” የሚባልለት አንዱ የከተማችን ርዕሰ ነገር ከሆነ ውሎ አድሯል። የጥራቱ ጉዳይ እንኳ ተከድኖ ይብሰልና ነጋ ጠባ ተስፋ በማድረግ ለሚባንኑ ባለእድለኞች ለምን በወጣላቸው ዕጣ መሠረት እንዳልተከፋፈለ ዕንቆቅልሹ ዛሬም ድረስ ፍቺም ፈቺም አላገኘም።
ለድሆች መጠለያነት ታስቦ መሠራቱ “ይበል! አዎ!” ቢያሰኝም ተስፋው እውን ባለመሆኑና ሳይኖርባቸው የሚያረጁትን ስንመለከት ደግሞ “አይ!” ብለን ማዘናችን አይቀርም። እንደዚያም ቢሆን እንኳ “ዕጣ ደርሷችኋል” ተብለው ለፈጣሪያቸው ስዕለት ያስገቡ በሺህ የሚቆጠሩ ተስፈኞች በማግሥቱ ምላሹ ሲቃረንባቸውና ተስፋቸው ሲመክን እያስተዋሉ በየቤተ እምነታቸው ደጃፍ ላይ ተሰልፈው በስዕለት የሰጡት ንብረታቸው እንዲመለስላቸው በፈጣሪ ፊት እየቃተቱና መሪዎቻቸውን እያሳቀሉ እንባቸውን ማንባት የዘወትር ቀለብ አድርገውታል።
ሌላም ጉዳይ እናንሳ። የራሱ የመስተዳድሩ ክፍለ ከተማና የወረዳ ጽ/ቤት የጡብ ድርድር ሕንጻዎችን ጥራትና አያያዝ በተመለከተ ከመናገር ዝምታ መምረጡ ይሻላል። ጥራት ተነፍጓቸው በተገነቡ ሕንጻዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች በምን የሞራል ብቃት ስለ ሕንጻ ግንባታ ጥራት መናገር እንደሚደፍሩ ግራ ያጋባል። ቢሯቸው ተዝረክርኮ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚመስል ኃላፊዎች ሕዝብ እየሰበሰቡ ስለ አካባቢና ስለ ቢሮ ጽዳት ሲያወሩ መስማት ማሳፈር ብቻ ሳይሆን ያሸማቅቃል።
“በአንዱ ስትጠቁም ከጣቶችህ መሃል፣
ሦስቱ ግን ራስህን ይመለከቱሃል።”
የሚለው የጥላሁን ገሠሠ የዘፈን ግጥም ለሞራል መገንቢያ እንዲሆናቸው ጋብዘናቸዋል።
ስለ አዲስ አበባ ከተማ የጡብ ድርድር ደኖች ጉዳይ የቱን አንስቶ የቱን መተው ይቻላል። የዛሬ አስር ዓመት ገደማ አንድ የውጭ ሀገር እንግዳ የከተማችን በርካታ ሕንጻዎች የተሸፈኑባቸውን የቻይና ርካሽ መስታወቶች አስመልክቶ የሰጠውን ሙያዊ ትንተና ባሰብነው ቁጥር ያሳስበናል። እንዲህ ነበር ያለው፤ “ከዛሬ ሃያ ዓመት በኋላ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከመስታወቶቹ በሚወጣው ነፀብራቅ እየተጠቃ የዓይን ህመምተኛ መሆኑ አይቀርም። ነዋሪዎች ብቻም ሳይሆኑ በከተማው ውስጥ የተተከሉት ዕፅዋቶች ጭምር በነፀብራቁ እየተጠቁ ሳይደርቁ አይቀሩም።”
ይህ የባዕድ ሀገር ባለሙያ የተናገረው እውነት ስለሆነ “ሀሰተኛ ነብይ” ተብሎ ሊወገዝ በፍጹም አይገባም። ለማንኛውም ከግምቱ ላይ አሥር ዓመት ተቀንሶ የቀረው አንድ አሥር ዓመት ብቻ ስለሆነ እኛ ነዋሪዎች ብቻ ሳንሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ የተተከሉት ዕፅዋትም ሳይቀሩ ሁላችንም ስጋት ላይ ስለወደቅን በፍጥነት ሊታሰብበት ይገባል።
ስለ ከተማችን የጡብ ድርድር ደኖች ጉዳይ መራር እውነታ እያመነዠክሁ እያለ አንድ ሃሳብ አእምሮዬ ውስጥ ስንቅር ብሎ ፈገግ አሰኘኝ። አዲስ አበቤ ሆይ ልብ ብላችሁ እንድታስተውሉ ወደ ብሔራዊ ቴያትር ጀርባ በሃሳብ ላጓጉዛችሁ። አካባቢው የፋይናንስ ተቋማት ሴክተር ተብሎ ከተለየ በኋላ ለበርካታ ባንኮች ዋና መ/ቤት የሚሆኑ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች እየተንጣለሉበት ነው። ያውም የዘመኑን ጥራትና ብቃት ባሟላ ደረጃ። ለከተማችን ውበት ስለሆኑ በጸሐፊ ብዕር እንመርቃቸው። ሕብረት ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ዘመን ባንክ ወዘተ. ለዘነጋኋችሁ ይቅር በሉኝና በእውነት ንብረታችሁን ያደርጅላችሁ፤ በገቢም ያበልጽጋችሁ።
ከእነዚህ ታላላቅ ሕንጻዎች ፊት ለፊት የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (የቀድሞው ኮሜርስ) ጥንታዊ ሕንጻ ለምቦጩን ጥሎ ወደ ላይ አንጋጦ ዘመናዊዎቹን ሕንጻ በተስፋ መቁረጥ ሲያስተውላቸው ትመለከታላችሁ። የበርካቶቹን የየባንኮቹን ሲኒየር ሹማምንትና ሰራተኞች አሰልጥኖ ያበቃው ያ ድንክዬ ሕንጻ ረዣዥምና መለሎ ፎቆችን ሲመለከት በሰውኛ አገላለጽ ምን ስሜት ይሰማው ይሆን። በእኔ ትሁት ግምት “ሸክላ ሰሪ በሰባራ ገል ትበላለች” ተብሎ ቢተረት ይገጥም ይመስለኛል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሹማምንት ሆይ በስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ ችምችም ተደርገው እንዲበቅሉበት ከተወሰነው የሕንጻ በጀት ውስጥ በስልጡን ሕንጻዎች ፊት ለፊት ቆሞ ለሚተክዘው አሰልጣኝ ኮሌጃችን እጃችሁን ዘርጉለትና ደረጃውን የሚመጥን ግንባታ አቅዱለት። ያለበለዚያ የቀድሞ የኮሌጁ ተማሪዎች በተንጣለሉት የፎቅ ብራንዶች ውስጥ ሲንፈላሰሱ አሮጌው ሕንጻ ግን እያንጎላጀጀ እንዳያሳጣችሁ አስቡበት። የቀለም ቅባት እንኳን አጥቶ የወየበው የሕንጻው ግድግዳ በምድርም በሰማይም እንዳያስኮንናችሁም ፍሩ።
እንደ መጫኛ የሳብኩትን ርዕስ ላጠቃልል፤
አዲስ አበባ ሆይ! ጆሮሽን ከፍተሽ ከሰማሽን ደግ። ዓይናችንን ለሚያጥበረብሩ የቻይና ርካሽ የሕንጻ ላይ መስታዎቶች መፍትሔ እንድትፈልጊልን በዓይን አምላክ እንማጠናለን። በሪል ስቴት ስም የሚፈጸመውን ዘረፋና ውንብድና ለማስቆምም መላውን ፈልገሽ እንባችንን አብሽልን። የራስሽን ቢሮዎች ጉዳይ አስቢበት። በኮንዶሚኒዬም ጉዳይ ስዕለታቸው ደርሶ ለተሳቀቁ ልጆችሽ እዘኚላቸውና ታደጊያቸው። በየሕንጻዎቹ ሥር ለመኪና መቆሚያ የተሰሩትንና ለሌላ ጉዳይ የዋሉትን ሥፍራዎችንም አጣርተሸ መፍትሔ ስጭልን። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሆይ አንተም ለኮሜርስ ት/ቤታችን ዝመና ዓይንህ ይገለጥ። ላንጨርስ በለኳኮፍናቸው ጉዳዮች ዙሪያ እኔና ብዕሬ ዳግም መመለሳችን አይቀርምና እስከዚያው ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012