ለሚ ከተማን በጨረፍታ
ከአዲስ አበባ በ125 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለሚ ከተማ ላይ ተገኝቻለሁ። በቅርብ ርቀት ያለው ቆላማ መልክዓምድር ሙቀቱን እየቆጠበ ወደ ደጋማው ሥፍራ ይልካል። የተራራውን ጫፍ ይዛ ከአናቱ ላይ ጉብ ብላ የተሠመረተችው ለሚ ከተማ በተራዋ ቀዝቃዛ አየሯን ወደቆላማው ሥፍራ እየላከች ‹‹እኔ እብስ፣ አንቺ ትብስ›› እንደሚባባሉ ጥንዶች ተሳስበው ይኖራሉ። ቆላው ማሽላ፣ ዘንጋዳ፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ አገዳ፣ ማኛ ጤፍ፣ በቆሎ የመሳሰሉት ለደጋው ማህረሰብ ያቀርባል። ደገኛው በተራው ጥቁር ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽምብራ፣ ባቄላ፣ ምስር፣ አተርና የተለያዩ አዝዕርቶችን አዘጋጅተው ለቆላው እያቀረቡ አንዱ ከሌላኛው እየተመጋገቡ ሕይወታቸውን ይመራሉ። አብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ በሚበዛባት በዚህች ከተማ ኦሮምኛም በስፋት ይነገራል። የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎችም በዚህች ከአገሬው ጋር በፍቅር ይኖራሉ።
በደቡብ ብሄር፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጋሞ ጎፋ አካባቢ ተወልደው ኑሯቸውን በለሚ ከተማ ያደረጉት አቶ ዳልጋ ዳታ ለዚህ አካባቢ ማህበረሰብ አብሮነትና ፍቅር አንዱ ማሳያ ናቸው። በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ‹‹ሃይ መሌ›› አልኳቸው። እርሳቸውም ‹‹ሎ! ጦሳ ጋላታ›› ግርድፍ ትርጉሙም ‹‹ሠላም ጤና ይስጥልኝ ስላቸው›› የእርሳቸው ምላሽ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ይመስገን›› እንደ ማለት ነው። ወደ ወጋችን ገባን።
በ1950 ዓ.ም በጋሞ ጎፋ ከአርባ ምንጭ በቅርበት ከምትገኘው ‹‹ሲቀላ›› የምትባል ቦታ ተወለዱ። በዘመነ ደርግ 1969 ዓ.ም በሚያዝያ ወር 300ሺ ሚኒሻ ወደ ውትድርና በተቀላቀለበት ወቅት እርሳቸውም አንዱ ነበሩ። በ1983 ዓ.ም ወታደሩ እስከተበተነበት ዕለት ድረስ ‹‹50 ከርቤል የሚባል መትረየስ መሣሪያ›› ተኳሽ ነበርኩ ይላሉ- አቶ ዳልጋ ዳታ። በወቅቱም ደመወዛቸው 90 ብር ነበር። ሁኔታውን ሲያስታውሱት ከገንዘቡ በላይ ግን ለአገር ማገልግሉ የሚሰጠው ክብር እጅግ የላቀ ነው።
እኚህ ሰው የእናት አገር ጥሪ ከውትድርና ሳይቀላቅላቸው ፍቅራቸውና የኑሯቸው መሰረት ከጋሞ ጎፋ ተራራ ሥር ከመነጩ ምንጮች፤ ከተራራው አናት ላይ መዓዛቸው የሚያውዱ እጽዋትና በልምላሜ ከታደለው ምድር ውጭ አንድም ነገር በልባቸው አልነበረም። ታዲያ ሕይወት መዘውሯ አይታወቅምና እርሳቸውም ወደማያውቁት መንደር ሊወስዳቸው ግድ ሆነ። ከትውልድ መንደራቸው ራቁ። እትብታቸው ከደቡብ አፈር ተቀብሮ ኑሯቸው ከሰሜን አፈር ሆነ። በመልካም ቤተሰብ ውስጥ ተንፈላሰው አድገው፤ ውሏቸው ከጦር ሜዳ ሆኖ በጦር ጎራዴ መፈተን ሆነ። በጦርነቱም የጠላትን ቀጣና እየደረመሱ በጥይት አረር ዶግ አመድ አደረጉት። ልባቸው ውስጥ ኢትዮጵያ የሚል ደም ተቀላቀለ አልረታ ባይም ሆኑ።
አቶ ዳልጋ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቀጣናዎች ተንቀሳቅሰው የአገራቸውን ዳር ድንበር አስከበሩ። በዚህ ሂደት ውስጥ በ1982 ዓ.ም ለሚ በሚባል አካባቢ በዝውውር ሄደው ነበር። በወቅቱም ከዛሬዋ የትዳር አጋራቸው ጋር ተዋወቁ። እንደገና በ1982 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ወደ ሆለታ አመሩ።
ከውትድርና ስንብት
በ1983 ዓ.ም ሠራዊቱ ሲበተን እርሳቸውም ፊታቸውን ወደ አንዱ አቅጣጫ አዞሩ። ታዲያ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ከሆለታ ወደ ትውልድ መንደራቸው አርባ ምንጭ ድረስ መሄዱን አልቻሉም። በመጨረሻም ወደ ትዳር አገራቸው መንደር ለሚ ከተማ ተመለሱ። በዚህች ከተማ ሰዎችም እንዲሁ እንደ መልክዓ ምድሩ ተከባብረው ተዋደው ይኖሩባታል። ብሄር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው በዓይን ጥቅሻ ይግባባሉ።
አቶ ዳልጋ በጦር ሜዳ ውሏቸው ጀብድ አስመዝግበዋል። ግን በመጨረሻው ሰዓት የደርግ ሥርዓተ መንግስት ሲያበቃ የእርሳቸው የውትድርና ጊዜም አበቃ። በወቅቱ በአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ ከምትገኘው ሆለታ ነበሩ። በወቅቱ ፀረ ደርግ ዘመቻው ተፋፍሞ ሁሉም ወታደር በየአቅጣጫ ተበተነ። እርሳቸውም ወደ ጋሞ ጎፋ መሄድን ትተው ለሚ ከተማ ከተሙ። ከዚያም ከትዳር አጋራቸው ጋር ሆነው ህይወትን አንድ ብለው ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ የውትድርና ጥቅማቸው፣ ደመወዛቸው፣ ክብራቸውና ሁሉ ነገራቸው ቀረ። ለአገራቸው እንዳላገለገሉ ‹‹የደርግ ወታደር›› በሚል ታፔላ አንገታቸውን ደፍተው ጡረታ ሳይጠይቁ ሁሉ ነገር በመና ቀረ። ላባቸውን ጠብ ያደረጉላት አገራቸው ውለታቸውን ረስታ ከአንድ መንደር ጉያ አስቀመጠቻቸው።
ሥራ ፍለጋ
ዕድሜ ዘመናቸውን ሥራ ሲፈልጉ ባዝነዋል። ሌላው ቀርቶ በጥበቃ ሥራ ለመሠማራት ብዙ ሞክረው አልተሳካላቸውም። ወታደራዊ ስልጠናቸውን እንኳን ተገን አድርጎ የሚቀጥራቸው ሰው አላገኙም። አሁንም ቢሆን ልባቸው አልሞተም። ሥራ መስራት እፈልጋለሁ፤ አገሬንም እራሴንም መጥቀም እችላለሁ የሚል እሳቤ አላቸው። የውትድርና ወኔ እየጎበኛቸው፤ የሥራ ፍቅር እያነሆለላቸው፤ የቤተሰብ ናፍቆት ጠዋትና ማታ እያንገላታቸው ዓመታትን አስቆጠሩ። ግን ለዓመታት ሥራ ፍለጋ ላይ ቢጠመዱም አልተሳካለቸውም። ግን ጥሩንባ መንፋትን ደግሞ አክብረው ሥራዬ ብለው ከውኑታል። ጥሩንባቸውንም እንደ ዓይን ብሌናቸው እየተመለከቱ ሌላ ሥራ ደግሞ ለማየት ይማትራሉ። ጥሩንባቸውን ከምንም አብልጠው ይወዳሉ። የዛሬ 10 ዓመት ገደማ በ300 ብር ተገዝቶ የተሰጣቸውን ጥሩንባ ዛሬም በሥርዓት ይዘውታል። ህፃናት በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጠው፤ ሰው ሲሞት ብቻ ያነሱታል። እንጀራዬን የማበስለው በዚህ ጥሩንባ ስለሆነ እሳሳለታለሁ ይላሉ።
በእርግጥ እርሳቸው ሥራ ፈላጊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሙያ መስኮች ዩኒቨርሲቲ እና ቴክኒክና ሙያ ተመርቀው በየሰፈሩ ድንጋይ ኮልኩለው የሚቀመጡ ወጣቶችን ሲመለከቱ ይተክዛሉ። መንግስት አንድ ይበላቸው እንጂ፤ ሥራ አጥ የሆነ ወጣት እኮ የሚያስበው አይታወቅም፤ ይከፋዋል፣ሆደ ባሻ ይሆናሉ፤ አልባሌ ቦታም ይውላሉ ሲሉም ግለሰባዊ ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ። እግረ መንገዳቸውንም ወጣቶቹ ስራ ሳይንቁ ያገኙትን ሰርተው እንዲያድሩ ይመክራሉ።
ሰው ምን ነካው?
አቶ ዳልጋ ለአሁኑ ትውልድ አንድ ጥያቄ ይጠይቃሉ፤ ለዚያውም የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ። ሰው ምን ነካው ይላሉ። እርሳቸው ጋሞ ጎፋ ተወልደው የእንጀራ አሊያም ደግሞ አጋጣሚ ነገር ሆኖ ከአማራ ክልል መርሐቤቴ አካባቢ ከተወለደችው ጉብል አግብተው አራት ልጆችን ወልደዋል። ከተወለዱበት ሰፈር ርቀው በባህልም በመልክዓ ምድሩም ለየት ካለ አካባቢ በሠላም እየኖሩ ነው። ከደቡብ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወልደው ከሰሜኗ እንስት ጋር ተጋብተዋል። ግን አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ ይደናገጣሉ። ብሄርህ ከዚህ ነው፤ የእኔ ደግሞ ከወዲህ ነው ብለው ሰው ብቻ ሳይቀር መሬቱ ጭምር ብሄር ያለው ይመስል አትምጣብኝ ሲባባሉ እንደ ኢትዮጵያዊ ጭንቅ ይላቸዋል። ለመሆኑ የእኔ ልጆችስ ብሄራቸው ምንድን ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። ኢትዮጵያዊ ስሜትና ፍቅራችንን ማንን ወሰደው ሲሉ በትካዜ ይጠይቃሉ። ለመሆኑ ሰው ምን ነካው ሲሉ ሲጠይቁ፤ እኔም፣ ሰው ምን ነካው ብዬ ለመጠየቅ እገደዳለሁ። አብሮነታችን፣ ፍቅራችን፣ መተሳሰባችን፣ ሠላማችን ማን ወሰደው? ለመሆኑ ሰው ምን ነካው?
ሠርግና ለቅሶ በስልክ እደርሳለሁ
ማህበራዊ ሕይወት የማይቀር ነውና አቶ ዳልጋ ከአካባቢው ሰዎች ጋር ጋብቻ ፈፅመዋል። በሁሉም ነገር ተዋህደዋል። ግን አገር ቤት ደስታም ይሁን መከራ ሲኖር ይሰማሉ። ታዲያ ‹‹ለቅሶም ይሁን ሠርግ የምደርሰው በስልክ›› ነው ይላሉ። ሰዎች ሲከፉ ደውዬ አፅናናለሁ፤ ደስታም ሲኖር እንዲሁ ስልክ ደውዬ እንኳን ደስ አላችሁ ብዬ ጣጣዬን እጨርሳለሁ እንጂ ለመሄድስ አቅሙ የለኝም ይላሉ። በለሚ ለ32 ዓመታት ቢኖሩም የእርሻ ቦታ እንኳን አለማግኘታቸው ያሳዝናቸዋል። ግን ደግሞ የቀበሌ ቤት ማግኘታቸው ትንሽ ተስፋዬን አለምልሞታል ይላሉ።
ናፍቆት
አቶ ዳልጋ ከቤተሰባቸው ከራቁ ዓመታት ተቆጠሩ። እናት እና አባታቸው በሕይወት አሉ። አንድ እህትና ሁለት ወንድሞች አሏቸው። እርሳቸው ለቤተሰባቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። እናም አንድ ቀን ናፍቆታቸውን ሊወጡ ይመኛሉ። ግን እንዴት ተደርጎ፣ መቼ፣ በማን አጋዥነት፣ በምን አቅም፣ መቼ እንዴትስ ሊሣካ ይችላል የሚለው ግን ዘወትር አዕምሯቸውን የሚፈትን ጥያቄ ነው። ልብ አያርፍምና ዛሬም ይናፍቃሉ፣ ወደ ጋሞ ጎፋ ሄደው ዘመድ አዝማድ ሊጎበኙ ይሻሉ።
በልጅነታቸው ጫካ ለጫካ ሮጠው ያደጉበት መንደር በጣም ይናፍቃቸዋል። ከፍራፍሬና አትክልት ያልቀመሱት፣ ከአካባቢው ጭፈራ ወዝወዝ ያላሉበት ከሰዎችም ያልተግባቡት አንዳችም ነገር የለም። አሁን ላይ ሆነው ይህን ሁሉ ሲያስቡት ይናፍቃቸዋል፤ ዓይናቸው እንባ እያቀረረ በናፍቆት ይወሰውሳቸዋል። በልጅነት ዘመናቸው ያደጉበትን ባህል እየናፈቁ፤ ከሌላ ባህልና ማህበረሰብ ተቀላቅለው ይኖራሉ ግን ‹‹ሲቀላ›› የተባለችው መንደራቸውን ዛሬም ይናፍቃሉ። ከ1969 ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም በውትድርና ቆይተው ምንም ጡረታ አለማግኘታቸው ያበሳጫቸዋል። ናፍቆት ያዝ ለቀቅ እያደረጋቸው ዛሬም እንደ ደራሽ ጎርፍ ወስዶ ይመልሳቸዋል። አንዳንዴ ውስጣቸው በተለያየ ስሜት ድፍርስርስ እያለ ያስቸግራቸዋል።
አዛውንቱ ዳልጋ ወደ ጋሞ ጎፋ የሄዱት በ1983 መጨረሻ ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን አልሞከሩትም፤ አቅም አጡ። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ፈቅም ደመቅም ማለት አልቻለም። ጥሩንባ እየነፉ ልጆቻቸውን አሳደጉ፤ ዓመታት ነገዱ። የወጣትነት ውበታቸው ሸሽቶ ፊታቸው ገርጥቶ ከዛሬ ላይ ደርሰዋል። እንደ ጫካ ሳር ጥቅጥቅ ያለ ጥቁር ፀጉራቸው፤ እንደ ጋቢ ንጥት ብሎ እርጅና ጋር ትግል ገጥመዋል። ከተራራ ተራራ፣ ከቋጥኝ ቋጥኝ ሲዘሉ የነበሩ እግሮቻቸው ተረቱ፤ ወገባቸው ጎብጦ ከዘራ አስያዛቸው። እንደፈለጋቸው መሮጥ ቀርቶ በፍጥነት መራመዱ የዳገት ያክል ከበዳቸው። እናም ከዘራ እየተመረኮዙ፣ ባለፈው ነገር እየተደሰቱ ደግሞም እየተከዙ 62 ዓመት ደፈናቸው።
የጥሩንባ ነፊው ፀሎት?
አቶ ዳልጋ የዕለት እንጀራዬን ስጠኝ ብለው ከቤት ሲወጡ ይፀልያሉ። ይህ ፀሎታቸው ዘላለም አብሯቸው የኖረና በቀሪ ዘመናቸውም አብሯቸው የሚቀጥል ነው። የዕለት ገቢያቸው ዋንኛ ምንጭ ሰዎች በሞቱ ቁጥር ጥሩንባ ሲነፉ የሚያገኙት 40 ብር ነው። ብዙ ሰው በሞተ ቁጥር ብዙ ብር ያገኛሉ። ጥቂት ሰው ሲሞትም ደመወዙ እንደዛው ነው። ወዲህ ግን አቶ ዳልጋ ፀሎታቸው አንድ እና አንድ ነው። ‹‹ኢትዮጵያን ሠላም ያድርጋት። ዙሪያዋ እሳት መሃሏን ገነት አድርጋት›› ብለው ይፀልያሉ። የሰዎችን ሠላምና ፍቅር አጥብቀው ይሻሉ። በዚህም የሰዎችን ሞት ማየት አይፈልጉም። ግን ስለ ገቢያቸው ይጨነቃሉ፤ ጉሯሯቸውን መድፈን ዋንኛ ዓላማቸው ነው። ሁሌም በሰው ሞት ገቢ እንደሌለ ያምናሉ። ግን ደግሞ ‹‹አቅም የለኝም፤ ያገኘሁትን ለበረከት ያድርግልኝ ብር ቢያስፈልገኝም የሰው መሞትን አልፍልግም››ይላሉ።
ፈገግታ ከፊታቸው የማይጠፋውና በሁሉም ነገር ፈጣሪን የሚያመሰግኑት ጥሩንባ ነፊው አቶ ዳልጋ ዳታ የስንት ሰው ሞት ለፍፈው ስንቶችን ቀብረው ይሆን ለሚለው ጥያቄ ግን መልሳቸው ‹‹አላስታውሰውም›› ነው።
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር