ፌስቡክን ዛሬ በሙሉ ልቤ ላመሰግነው ነው። ለካ ይህን ያህል ዋጋ ነበረው! ይህን ያህል የጋራ ሳቅ፣ የጋራ ጨዋታ፣ የጋር ትዝታ፣ የጋራ እምነት፣ የጋራ ሀሳብ ነበረው። ለካ ካወቅንብት የአብዛኞቻችን አስተዳደግ ተመሳሳይ ነበር፤ ወላጆቻችንም ተመሳሳይ ነበሩ። ለካ ፌስቡክ እንዲህ የመመሰጋገኛ፣ የመወዳደሻ፣ የመተዋወቂያ እና የመነፋፈቂያ ቦታ ይሆናል።
ከአንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር ጓደኛዬ ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ እያወራን የነገረኝ ነገር ትክክል መሆኑን አረጋገጥኩ። ‹‹ፌስቡክ የፖለቲካ መተንተኛና የግጭት መቀስቀሻ የሆነው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ነው›› ነበር ያለኝ። የፌስቡክ ዋና ጥቅሙ ማህበራዊ ግንኙነት ነው፤ ለዚህም ነው ‹‹ማህበራዊ ሚዲያ›› የተባለው። ይህ ማህበራዊ ገጽም ማህበራዊ ግንኙነት ይደረግበታል። ሰዎች ይተዋወቁበታል፤ የተጠፋፉ ይገናኙበታል። የጋራ ሀሳብና ትውስታ ይለዋወጡበታል። በነገራችን ላይ ፌስቡክ ገና ወደ አገራችን እንደገባም ይሄው ነበር አገልግሎቱ። ብዙዎች እንደሚሉት ፌስቡክን የፖለቲካ መንደር ያደረገው ደግሞ የዋናዎቹ መገናኛ ብዙኃን መዳከምና የሚፈለገውን ያህል የሀሳብ ነፃነት አለመኖር ነው። እነርሱ የፖለቲካ መተንተኛ ቢሆኑ ማህበራዊ ሚዲያ ደግሞ ለመዝናኛና ለማህበራዊ ግንኙነት ብቻ ይውል ነበር የሚል አምነት አለኝ።
ዛሬ የማወራችሁ ስለ ‹‹90’s ልጆች›› የፌስቡክ ገጽ ነው። ገጹ ከታወቀ ገና አንድ ወር እንኳን አልሞላውም። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችን አፍርቷል። በፌስቡክ ተስፋ ቆርጠው መጠቀም ያቆሙ ሁሉ በዚህ ገጽ ምክንያት ተመልሰዋል። የተመለሱበትን ምክንያት ሲናገሩም ይሄ ‹‹ግሩፕ›› ትዝታቸውን መቀስቀሱና፤ በዋናነት ደግሞ ቅጥ ያጣውን የፌስቡክ የብሄር ብሽሽቅ ስለገላገላቸው ነው።
ይሄን ‹‹ግሩፕ›› ብዙዎች ያመሰገኑበት ምክንያት ከብሄር ብሽሽቅ ነፃ የሆነ እፎይታ በመፍጠሩ ነው። በዚህ ‹‹ግሩፕ›› ውስጥ ማንም ስለዘረኝነት አይጽፍም፣ ማንም ሰውን የሚሳደብና ነውር ነገር ፈጽሞ አይጽፍም፤ የሚጻፈው የልጅነት ትዝታ ብቻ ነው። ገጹን የሚቆጣጠሩት ሰዎች የኤዲቶሪያል ህግ ሳይኖራቸው አይቀርም።
የአብዛኞቻችን አስተዳደግ ተመሳሳይ ነው፤ የቤተሰቦቻችን የኑሮ ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር። በዚህም የአገራችንን ስነ ልቦናዊ አንድነት እንረዳለን። ይሄ ሁሉ ተመሳሳይነት እያለን፤ ይሄ ሁሉ አንድነት እያለን ምን ሆነን ይሆን አሁን ላይ እንዲህ እርስበርስ የምንዘላለፈው? ለምን ይሆን እንዲህ የምንጨካከነው? አንዱ አንዱን ውጣልኝ የሚለው ለምን ይሆን?
የ90ዎቹ ልጆች ገጽ በብዛት የትምህርት ቤት ትዝታ ነው። ምክንያቱ ግልጽ ነው። አብዛኞቻችን ልጅነታችንን የምናሳልፈው በትምህርት ቤት ስለሆነ ትዝታዎች በዚያ በኩል ይበዛሉ። ያም ሆኖ ግን ሌሎች ትዝታዎችም አሉበት። ትዝታዎቹም የሚ ያተኩሩት በ1990ዎቹ በነበሩ ሁነቶች ላይ ነው። ለምሳሌ በ90ዎቹ የነበሩ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጋዜጠኞች፣ በወቅቱ የነበ ረው የሸቀጦች ዋጋ፣ በተለይም ልጆች እንደመሆናችን የሚበሉ ነገሮች ዋጋ፣ በወቅቱ ተወዳጅ የሆኑ ዘፋኞች… እነዚህንና የመሳሰሉት በገጹ ላይ ተደጋግመው የሚጻፉ ናቸው። ይሄ ገጽ ለቀልድና ለመዝናናት ብቻ ሳይሆን ታሪክ በመሰነድም ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው።
በነገራችን ላይ ይሄን ገጽ መከታተል ከጀመርኩ በኋላ ጨዋ ሰው ሆኛለሁ (አክቲቪስት ልሆን ትንሽ ነበር የቀረኝ)። በቃ የልጅነት ባህሪዬ ነው የመጣብኝ። ቢሰድቡኝ እንኳን የምሳደብ አይመስለኝም። በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርቴን ሁሉ እንዳስታውስ አድርጎኛል። እንዲያውም አንድ ዕለት ማታ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ የተማርኩባቸውን ደብተሮች ሳገላብጥ አመሸሁ። የመምህሮቼን ስም ሁሉ እያስታወስኩ በትዝታ ፈረስ ወደኋላ ስጋልብ ነበር።
አንድ ዕለት ደግሞ ‹‹የፕላዝማ መምህሮ ቻችሁን ስም ተናገሩ›› ተብሎ ነበር። የ9ኛ ክፍል የፕላዝማ መምህሮቼ ከነመልካቸው ነበር የመጡብኝ። ጠይም ባለፍሪዝ ፀጉሩ የሒሳብ መምህር መክብብ ሰለሞን ብዙዎች የጠቀሱት ነበር። በቁንጅናዋ ብዙ ተማሪ የሚያስታውሳት ደግሞ የባዮሎጂ መምህሯ ምህረት ትዕግስቱ ነበረች። ተከስተ የሚባለው የኬሚስትሪ መምህር የአነጋገር ድምጸቱ ሁሉ ነበር ትዝ ያለኝ። ‹‹Isomerism reaction›› እያለ የሜቴን፣ ኢቴን፣ ቡቴን፣ ፔንቴን የሚባሉትን የኪሜስትሪ ቀመሮች ሲናገር አስታውሳለሁ። ይህኛው የኬሚስትሪ ክፍል ደግሞ ለብዙዎቻችን ይከብደን ነበር። እነዚህን የፕላዝማ መምህሮች ብዙ ሰው ያስታወሳቸው አገር አቀፍ ሥርጭት ስለሆነ የሁላችንም የጋራ መምህሮች ስለነበሩ ነው። በእርግጥ የፕላዝማ ትምህርት ያልደረሰባቸው አካባቢዎችም ይኖራሉ።
ሌላው የዚህ ‹‹ግሩፕ›› ትውስታ ደግሞ በ90ዎቹ የወጡ ዘፈኖች ናቸው። የነ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ጥበቡ ወርቅዬ፣ ታምራት ደስታ፣ ሃይልየ ታደሰ፣ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ አበባ ደሳለኝ፣ ሃይማኖት ግርማ፣ ትዕግስት ፋንታሁን… የመሳሰሉት የዚያን ዘመን ፈርጦች የልጅነት ትውስታወቻችን ናቸው። እንዲያውም ከዘፈኖቻቸው ውስጥ ራሱ ሲጠቀስ የነበረው ትምህርት ቤትና ልጅነትን የሚያስታውሱ ናቸው። ለምሳሌ የጥበቡ ወርቅዬ ‹‹ሊጋባ›› የትምህርት ቤት ትዝታ ነበረው።
የአበባ ደሳለኝና የትዕግስት ፋንታሁን ‹‹እርጅኝ አብሮ አደጌ›› የልጅነት ፍቅርንና አይናፋርነትን የሚገልጽ ነበር። የታምራት ደስታ ‹‹አንለያይም›› የ8ኛ ክፍል፣ የ10ኛ ክፍል ወይም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ጨርሰን መለያየት የግድ ሲሆን እንባና ሳግ እየተናነቀን የምንገባበዘው ነበር። የትምህርት ቤት ሚኒሚዲያ ውስጥ በዚያን ሰሞን ይደጋገማል። እንዲሁም የሰኔ ወር መጥቶ ትምህርት ሲዘጋ ለመምህሮቻችን ጭምር እንጋብዝ ነበር።
ሌላው የዚህ ‹‹ግሩፕ›› ባህሪ ደግሞ አዝናኝነቱ ነው። እዚህ ላይ የዓመተ ምህረት ገደብ የለውም። ዝም ብሎ የልጅነት ትዝታ ብቻ ነው። የዓመተ ምህረት ገደብ የለውም ስል ግን በአሁኑ ጊዜ አለ ማለቴ ሳይሆን ከ90ዎቹ በፊት ሊኖር ይችላል በሚል ነው። አብዛኛው የልጅነት ትዝታ ግን አሁን ላይ ያለ አይመስልም። ለምሳሌ ተማሪ ሲያጠፋ መምህር መግረፍ የለም፤ መንበርከክ የለም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የመማር ማስተማር ሁኔታውም ተቀይሯል። እስኪ ከዚያው ‹‹ግሩፕ›› ውስጥ ካገኘኋቸው አንዳንዶችን እየጠቃቀስኩ እናንተም ልጅነታችሁን አስታውሱ።
ቲቸር ብሎ ተጣርቶ የክፍል ጓደኛውን ሊያስጠቁር ካለ በኋላ በመናገር እና ባለመናገር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ራሱ ከክላስ ያበረረ ተማሪ ብዙ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም።
በተለይም ከ5ኛ እና 6ኛ ክፍል በታች እያለን ክፉ ደጉን ብዙም ለይተን አናውቅም ነበር። የተጣላነው ጓደኛ ካለ ሰበብ ፈልገን መምህሩ እንዲቆጣው ለማደረግ ያላጠፋውን ጥፋት አጠፋ ብለን እናነገራለን። ያው እንግዲህ ልጅነት ነውና መጨከን ደግሞ ያቅተናል። ይህኔ መምህሩ ‹‹ምን ያወዛግብሃል›› ብሎ ራሱን ያባርረዋል ማለት ነው።
‹‹ነስር የነሰረውን የክፍላችሁን ልጅ አጅቦ ለመውጣት እኔ ይዤው ልውጣ በማለት ክፍሉን በአንድ እግር ያቆማችሁ›› ይቺ ደግሞ የስንፍና ምልክት ናት። በሰበቡ ከክፍል ለመውጣት ነው።
‹‹እቤት የመጣ እንግዳ የሰጠህን ብር ‹ይጠፋብሃል ላስቀምጥልህ› ተብሎ ሿሿ የተሰራ›› ይሄኛው የትምህርት ቤት ሳይሆን ዝም ብሎ የልጅነት ትዝታ ነው። እንግዳ ሲመጣ ለልጅ ብር መስጠት የተለመደ ነው። ታዲያ እናቶች ይጠፋብሃል በማለት ይቀበሉና ያስቀምጡታል፤ ከዚያም ራሳቸው ያጠፉታል። ተጨምሮ ጫማ ይገዛልሃል፣ ልብስ ይገዛልሃል ይባልና ግን በዚያው ይረሳል። ‹‹ሿሿ›› ማለት በአራድኛው የተሰ ረቀ፣ የተጭበረበረ፣ የተታለለ እንደማለት ነው።
እዚህ ጋ ደግሞ ሌላ ቀልድ። ይሄኛው የልጅነት ብቻ አይደለም፤ የ90ዎቹ ብቻም አይደለም። በብዙ የገጠር አካባቢ የሚደረግ ነው።
‹‹ማታ ልንተኛ የቤታችንን በር በጄሪካን፣ በብረት፣ በርሜል፣ ብረት ምጣድና በተለያዩ ድምፅ ያላቸው ዕቃዎች የምናስደግፈው ነገር፤ የድሮ የደህንነት ካሜራ ማለት ነው›› እነዚህ በመንኳኳት ድምጽ የሚፈጥሩ ዕቃዎች የበር ማስደገፊያ የሚሆኑት በሩ ሲከፈት እንዲሰማ ተብሎ ነው።
‹‹እስኪብርቶ እምቢ ሲለው የሰው ጫማ ላይ የሞከረ እጁን ያውጣ!›› ይችኛዋ ደግሞ የትምህርት ቤት ትዝታ ናት። እስኪርቢቶ እምቢ ሲለን ጫማ ላይ ነበር የምንሞክረው። በወቅቱ የምናደርገው ጫማ ፕላስቲክ ነክ ስለሚሆን የዘጋ እስኪርቢቶ ይከፍት ነበር። ያንኑም የፕላስቲኩን ጫማ ያላደረግን ደግሞ የሰው ጫማ ላይ ሞክረን ይሆናል።
‹‹እኛ እኮ ሲም ካርድ በ368 የተገዛልን ትውልዶች ነን፤ ምነው ኢንዶሚዎች በ15 ብር ሲም ካርድ እኩል ካላወራን አላችሁ›› ይችኛዋ ደግሞ እርስበርስ መፎጋገሪያ መሆኗ ነው። ‹‹ኢንዶሚዎች›› የተባሉት የዘመኑ ልጆች መሆናቸው ነው። በነገራችን ላይ ከ90ዎቹ ‹‹ግሩፕ›› በኋላ ብዙ የተፈጠሩ ገጾች አሉ። አንዳንዶቹ እንዲያውም ለቀልድ ብቻ ተብለው ያልተኖረበትን ዘመን የሚገልጹ ናቸው። ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት የሰው ልጅ ይኖርበት የነበረውን ዘመን ታሳቢ በማድረግ የሚጻፉ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ከ2000 ሚሊኒየም ወዲህ ያለውን የሚገልጹ ናቸው።
አንዳንዴ ደግሞ ከቀልድም ያለፈ ጥያቄ ይጠየቃል። ይሄኛው ጥያቄ እንደ ጠቅላላ እውቀትም ጭምር ነው። በ90ዎቹ ውስጥ ከነበሩ ሁነቶች ውስጥ ይጠየቃል። ለምሳሌ የስልክ ቁጥር 10 ዲጂት የሆነው በ90ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ነው። ከዚያ በፊት 6 ዲጂት ነበር። በነሐሴ ወር 1996 ዓ.ም አካባቢ ማስታወቂያው ተነግሮ ከመስከረም 1997 ዓ.ም ጀምሮ 10 ዲጂት ሆኗል። በወቅቱ የነበሩ ማስታወቂያዎችም ይጠየቁ ነበር። ለምሳሌ ‹‹መንደር ሆናለች ዓለማንችን፤ የመረጃ ነው ዘመናችን…›› የሚለው የቴሌኮሙዩኒኬሽን (የያኔው ስሙ) ማስታወቂያ ከነ ዜማው አስታውሰዋለሁ።
እንግዲህ ይሄ ገጽ ሁላችንም አንድ ቤት እና አንድ እናትና አባት ያሳደገን እስከሚመስል ድረስ የጋራ ባህሪዎቻችንን ተጋርተንበታል። የማይተዋወቁትን አስተዋውቋል።
የዚህ ‹‹ግሩፕ›› ፈጣሪዎች በፋና ቴሌቭዥን እንግዳ ተደርገው ነበር። እዚያ ላይ እንደተናገሩት ማንም ሰው ዘረኝነተንና ብሄርን ከብሄር ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ ነገር በፍጹም አይለጠፍም። የገጹ አባላት ሁሉ ለዚህ ተባባሪ ናቸው።
ልጆቹን እናመሰግናለን፤ አስተዳደጋችን ነውና እንዲህ አይነት ጨዋነት ሲኖረን ያምርብናል!
አዲስ ዘመን ኅዳር 20/2012
ዋለልኝ አየለ