ባለፉት 27 ዓመታት በ36 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገሮች እንዲሸሽ መደረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ አይነቱ ሀብት ማሸሽ እንዳይቀጥል ለማድረግ የመንግሥትና የሥራ ኃላፊዎች ንጽህና ወሳኝ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ዘላለም እጅጉ እንደሚሉት፤ ከአስር ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ከአገር የሚወጣበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል። ይኸው ችግር በማስረጃ ተጠናቅሮ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ወደ ውጭ ሀገሮች እንዲሸሽ የተደረገው ሀብት ሀብት በማስረጃ ተጠናክሮ መቅረቡ ቀጣዩ የመንግሥትና የሹማምንቱ አካሄድ ምን መልክ መያዝ አለበት የሚለውን ያመላከተ ነው።
ዶክተር ዘላለም ይህ ምዝበራና ሀብት ማሸሽ እንዴት ሊከሰት ቻለ? በምን አይነት መንገድስ ወደ ውጭ እንዲወጣ ተደረገ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጦች አንድ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡ በዚህም ከገበያ ዋጋ ውጪ በተጋነነ የዋጋ ዝርዝር እቃዎችን ከውጭ አገር መግዛትና የሚገኘውንም ትርፍ በዚያው በውጭ አገር እንዲቀር ማድረግ ከማሸሻዎቹ መንገዶች መካከል መሆናቸውን ጥናቶችን በመጥቀስ ይጠቁማሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር አጥላው አለሙ በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት አለመደረጉን ይገልጻሉ፣ ችግሩ በአገር ላይ ሊደርስ የሚችልባቸው መንገዶች እጅግ ከፍተኛ መሆናቸውን ፣ የሚፈጸመውም በመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች መሆኑን ያመለክታሉ ።
ለምዝበራ ምቹ ከሆኑ መንገዶች መካከል ደግሞ የንግድ ልውውጥ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ የዶክተር ዘላለምን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ በንግድ ልውውጡ ሰዎች በሌላ አገር የራሳቸውን ኩባንያ በማቋቋም አልያም ከውጭ ተቋማት ጋር ሽርክና በመመስረትና ምስጢራዊ ግንኙነትን በማድረግ ሀብት እንደሚያሸሹ ይጠቁማሉ፡፡
በዚህም ከአገር ውስጥ ወደ ተቀባይ አገር የሚልኩትን በዝቅተኛ ዋጋ እንደሚሸጡ ፣አንዳንድ ጊዜም በኪሳራም ይቅር ሊሉ እንደሚችሉ ያብራራሉ፡፡ይህ ሲሆን በውጭ ያላቸው ተቀባይ አትርፎ እንደሚሸጥና እነርሱም የሚፈልጉትን ገንዘብ እንደሚያገኙ ዶክተር አጥላው ያብራራሉ፡፡ ይህ አይነቱ ግብይት አገሪቱ ግብርም ታክስም እንዳታገኝ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝቷ እንዲዳከም እንደሚያደርግም ያብራራሉ።
ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚጠራ፣ ውጭ ሀገር የሚገኙት ደንበኞቻቸው ባላቸው ሽርክና ለእቃዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንደተከፈለባቸው እንዲገልጹ እንደሚደረግም ዶክተር አጥላው ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ገንዘብ በትክከል እቃውን ለመግዣ ሳይሆን ለሌላ ተግባር የዋለ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ይህን መሰል ሁኔታዎች ደግሞ ለምዝበራ የተመቻቹ መንገዶች በመሆናቸው ኢትዮጵያም በዚህ መሰሉ ሁኔታ በርካታ ሀብቷን ያጣች አገር ሆናለች ይላሉ ።
ዶክተር ዘላለም በአገር ውስጥ የሚፈጸም ሙስና ደግሞ ሌላው ወሳኝ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ መንገድ የተገኘው ገንዘብ ወደ ዶላር እየተቀየረ ወደ ውጭ በመላክ በውጭ ባንኮች ማስቀመጥም እየተስተዋለ ላለው የገንዘብ ሽሽት ሌላው ምክንያት አድርጎ መውሰድ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡
እነዚህ ችግሮች በላላ አሰራርና የቁጥጥር ማነስ እንደሚፈጠሩም ይገልጻሉ፡፡ በአገሪቱ ላይ ያለው የፋይናንስ ደረጃ ያልተጠናከረ መሆኑን ለአብነት በመጥቀስ፣ አብዛኛው ግብይትም በጥሬ ገንዘብ እንደሚፈጸም ያመለክታሉ፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚከብድ ይህም ለምዝበራ በር መክፈቱን ያብራራሉ።
ዶክተር ዘላለም ለዚህ ችግር እንደ መፍትሔ ያስቀመጡት ደግሞ በኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አስተዳደር ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል፣ ተቋማትን ማጠናከር፣ ህጎችን መከለስና ተፈጻሚነታቸውን መከታተል፤ የህግ አስፈጻሚ ተቋማትን አቅም ማጠናከር ፣ በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ቅጣት መውሰድ የሚሉትን ነው ።
እስከ አሁን መንግሥት በእንደዚህ አይነት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ አለመሥራቱን ባለሙያው ተናግረው፣ ገንዘብ በማሾለኩ ሥራ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እጅ ሊኖርበት እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
ዶክተር አጥላው ያለፈው ማለፉን በመጥቀስ በቀጣይ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን በሚገባ ሊሠራ እንዲሁም የሚሾሙት ኃላፊዎችም በትክክል ሊረዱትና በተግባር ሊተረጉሙት እንደሚገባም ይናገራሉ።
በተለያዩ መንገዶች ወደ ውጭ በሚሸሽ እንዲሁም በአገር ውስጥ እየተከማቸ በሚባክን ገንዘብ ላይ ጥብቅ ክትትል ማድረግ በጣም እንደሚያስፈልግ ተናግረው፣ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ መወጣት ከተቻለ ችግሩን ማስቀረት ባይቻል እንኳ መከላከል የሚቻልበት እድል ሰፊ ነው ይላሉ።
ለዚህ ምዝበራ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት ህገ ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) መሆኑ ግልጽ ነው የሚሉት ዶክተር አጥላው፣ ይህም በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ድጋፍ ሲደረግለት እንደቆየም በመጥቀስ የዶክተር ዘላለምን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ ችግሩ በዚሁ መንገድ ከቀጠለ አሁንም አደጋው ከፍተኛ እንደሆነም ይጠቁማሉ፡፡ ይህንን መቆጣጠር የሚችል የመንግሥት አሰራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ያስገነዝባሉ።
ወቅቱ በብድር የተገኘን የአገር ገንዘብ በቀጥታ በሻንጣ ይዘው የሚሄዱ ሰዎች የተፈጠሩበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ቢሆን የመንግሥትን ሥልጣን በመንተራስ የሚደረግ እንጂ ማንም ተራ ሰው ሊያደርገው የሚችል እንዳልሆነም ነው የሚገልጹት፡፡ ችግሩን ለመፍታት አሁንም እጁ ንጹህ መንግሥትና የመንግሥት የሥራ ኃላፊ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ።
እስከ አሁን የተከሰተውን አይነት ምዝበራ እንዳይፈጸም በቅድሚያ መንግሥት ራሱን ንጹህ ሊያደርግ፣ ከዚያም ሹማምንቱን ሊያጸዳ እንደሚገባ ይጠቁማሉ ፡፡ በቀጣይም የችግሩ ፈጻሚዎችን ለህግ የማቅረቡ ሥራ በከፍተኛ ትኩረት መሥራት ይኖርበታል ይላሉ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ሀብት ወደ ውጪ ከሚሸሽባቸው ሀገሮች አንዷ በመሆን ትታወቃለች፡፡ ባለፉት 27ዓመታት ውስጥም 36 ቢሊዮን ዶላር ወይም አንድ ትሪሊዮን 80 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ገንዘብ ከሀገሪቱ ወደ ውጭ እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡ ይህ የገንዘብ አቅም በ80 ቢሊዮን ብር ሂሳብ 13 የህዳሴ ግድቦችን ለመገንባት ያስችል ነበር፡፡
ከሀገሪቱ እንዲሸሽ እየተደረገ ላለው ገንዘብ አንዱ ምክንያት የወጪና ገቢ ንግዱ መሆኑ እየተገለጸ ነው፤ ከዚህ የወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም እየተዳከመ መምጣቱ ይታወቃል፡፡ ችግሩን ለመፍታት አንዱ መንገድም የወጪና ገቢ ንግዱን በሚገባ መፈተሸ ነው፡፡
ሀገሪቱ የወጪ ምርቶችን ወደ የት ሀገር እንደምትልክ ብቻ ሳይሆን ለእነማን እንደምትልክ መጣራት ይኖርበታል፡፡ ላኪና ተቀባይ ላይ እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን እንደ ንግዱ ማህበረሰብም ሆነ እንደ ተቋም ግብይታቸው በምን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ በመለየት ትክክለኛውን የንግድ መስመር እንዲከተል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የሀገሪቱ ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ የሚደረግበት ሌላው መንገድ ደግሞ የባለሥልጣናት እጅ ነው፡፡ እንዲሸሽ እየተደረገ ያለው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከፍተኛ ባለሥልጣናት በማሳተፍ የሚፈጸም ነው፡፡ የሀገሪቱን ሀብት ለመታደግ፣ የመንግሥት ኃላፊዎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ባለሥልጣናት የእጃቸውን ንጽህና ጠብቀው እንዲሠሩ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
እፀገነት አክሊሉ