‹‹እሸትና ቆንጆ አይታለፍም›› እንዲሉ አበው ብዙዎች በተለይም ገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የማን ማሳ ነው ሳይሉ የደረሰን እሸት ቀጥፈው ይቀምሳሉ። የሚቆጣም አይኖርም። በእርግጥ አሁን አሁን ነገሮች እየተቀየሩ ከልካይ በዝቷል። ግን ብዙዎች ባህላቸውን የረሱ አይደሉምና ከመቅጠፍና ከመመገብ አልፈው በጋራ ተሰብስበን እሸት አይታለፍን እናሳይ በማለት በዓል አድርገው ያከብሩታል። ፍሬ መጣ ሲሉም በጋራ አምላክን አመስግነው በህብረት እሸት ይቀምሳሉ።
በዓሉ እንደክልሉና አካባቢው የተለያየ ነው። ስለዚህም “እህልን በጥቅምት ልጅን በጡት” የሚባልለትን፤ አዝርዕትና አትክልት ሐዲሳን ፍጥረታት ሆነው የሚነሱበት የሚበቅሉበት፣ የሚለመልሙበት ብሎም የሚሰበስቡበት ወር ነው ህዳር። ስለዚህም ስንዴ ከሆነ ወጥለው (አንኩተው)፤ ባቄላ፣ አተር እና ሽንብራ ከሆነ ፈልፍለው፣ በቆሎን ቀቅለው ወይም ጠብሰው ብሉልኝ የሚባባሉበትን የእሸት በዓል በደቡብና በሰሜን እናስቃኛለን። ከደቡብ የጎፋ፣ የቤንችና የሸኮን እንይ፤ ከሰሜን ደግሞ የወሎን ትውፊታዊ ባህልን ከተለያዩ ሰነዶች ያገኘነውን መረጃ እናቋድሳችኋለን።
ባዲገዝ
የእሸት በዓሉ የሚከበረው በብዛት ደቡብ ወሎ ውስጥ ሲሆን፤ ባዲገዝ ተብሎ ይጠራል። ትርጓሜውም “ባዕድ ይገዝ (ያግዝ)፤ ዘመድ ያልሆነም ይርዳ” ማለት ነው። ምክንያቱም በዕለቱ በዓሉ የማይታገዝ ሰው የለም። እገዛው ደግሞ በዓሉን ከማዘጋጀት ይጀምራል። “ለዚህ የእሸት ወቅት ያደረስከን ተመስገን! አዝመራውን ለጎተራ አብቃልን! ከርሞም ከዚህ የተሻለ አዝመራ ስጠን!” ተብሎ ፈጣሪም ይመረቃል በባዲገዝ ሥነሥርዓት። አዛውንቶች ስለአካባቢውና ስለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለባህልና መረዳዳት፣ ፖለቲካና የሕዝብ አስተዳደር በእሸት በዓላቸው ላይ ያስተምሩበታል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙት የአካባቢው ሽማግሌዎች “ተላይ አልጋውን ከታች ለጋውን ጠብቅልን! አዝመራውን አብዛልን!” እያሉ በዝማሬ ጭምር ይጸልዩበታል። በእነርሱ አገላለጽ “አልጋ” ማለት መንግሥትን ሲሆን፣ “ለጋ” ማለት ደግሞ ሕዝብ ነው። እናም በዚህ ጊዜ ስለተቸገረም ይጸለያል።
ይህ ክብረበዓል ሲከናወን የአካባቢው አዝመራ ተሰብስቦ ሰውም ከየአካባቢው መጥቶ አንድ ቦታ ላይ በመገናኘት ሲሆን፤ በጋራ የሚበሉበትም ባህል ነው። በዓሉ ለሳምንት ይቆያል። ስለዚህ እሸት ያለው እሸት፣ ወተት ያለው ወተት፣ ቅቤ፣ ጥንቅሽ ያለው ጥንቅሽ፣ እንጀራ፣ ቂጣ… ወደ መሰብሰቢያ ቦታው ይመጣና በጋራ ይመገቡታል። ባዲገዝ ማሳ የሌላቸውና ያላረሱ ሰዎች ሁሉ እሸት የሚቀምሱበት፣ የመተሳሰብ፣ የመተዛዘንና የመዋደድ በዓል ነው። ከየማሳው ያለው የእሸት ዓይነት ሁሉ ቀርቦ እየተበላ እስከ ምሽት ድረስ ጨዋታና ምርቃቱ ይቀጥላል።
የእሸት በዓል (ባዲገዝ) ‹‹ምቀኛ ሟርተኛን አላህ ይያዝልን፣ የመጣ እንግዳ ሁሉ በሰላም ይስተናገድ፣ ሰላም ይዞ፣ ሙሃባን ይዞ፣ ጤናን ይዞ የሚሄድ ይሁን። በዚህ ወጣ በዚህ ገባ እያለ የሚያበጣብጠንን ያርቅልን። ለሰውም ዘር ለእህል ዘር እንዲሁም ለእምነታችንም አይበጅም›› እያሉ አባቶች ይመርቃሉ።
ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ ማህበረሰቡ ይህንን የጋራ ባህል አጠናክሮ መቀጠሉን የሚናገሩት የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፤ በበዓሉ የአካባቢ ነዋሪዎች መሬት ያበቀለቻቸውን የእህል ዘሮች ሁሉ በእሸት ወቅት ይቀርቡበታል። የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችም እንዲሁ ለምግብነት የሚቀርቡበት ጊዜ ነው። ይህ ከሆነ በኋላ በነዋሪዎች ሀብት መጠን፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በጾታና በዕድሜ ሳይከፋፋል በጋራ መመገብ እንደሚጀመር ያስረዳሉ።
በዓሉ ሌላ ስያሜም አለው። “ዲልበት” እያሉ ይጠሩታል። በዚህ ወቅት የሚቀርበው አዝመራ ቃሪያ፣ ጥንቅሽ፣ በቆሎ ወዘተ ሲሆን፤ በየዓመቱ በጥቅምት ወር ይከናወናል። የአካባቢ ነዋሪዎች በዓሉን በሠላም ካጠናቀቁ በኋላ ዓመቱ የሠላም እንዲሆን ዱዓ (ጸሎት) ያደርጋሉ፤ ለሚቀጥለው የባዲጋዝ በዓል ይዘው የሚመጡትን እሸትም ቃል በመግባት ይለያያሉ።
የእሸት በዓል በጎፋ
በጎፋ ብሔረሰብ ዘንድ የእሸት ቀመሳ ቀን የሚከበረው በተለያየ መንገድ ነው። የመጀመሪያው በቤት ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፤ ሁለተኛው በቤተ እምነት ግቢ ውስጥ ይከናወናል። በቤት ውስጥ በቤተሰብ አማካኝነት የሚከናወነው የእሸት መቅመስ ጊዜ ሲሆን፤ በቅድሚያ በቤት ውስጥ ቡና ይፈላል፣ ቀጥሎም በቆሎው ይጠበስና ለአባወራው ይሰጣል። ከዚያ አባወራው የተሰጠውን በቆሎ የተወሰነ ከፈለፈለ በኋላ ለራሱ ቀምሶ አንድ አንድ ፍሬ ለሚስቱና ለልጆቹ ያቀምሳቸዋል።
ይህንን ያየች እማወራ ደግሞ ‹‹እንኳን አደረሰን›› በማለት መሬቱን ትስማለች። አምላኳንም ታመሰግናለች። ከዚያ ቡናውን ቀድታ ለቤተሰቡ ትሰጣለች። ቡናው ተጠጥቶ ሲያልቅ የእሸት መቅመሱ ሥርዓት ተጠናቋልና ሁሉም ወደየሥራቸው ይሄዳሉ። ከዛ በኋላ እሸት እየተቆረጠ በማንኛውም ጊዜ እንዲበላ ይፈቀዳል።
ሁለተኛው ሥርዓት የክርስትና እምነት የተቀበሉት የብሔረሰቡ አባላት የሚያከናውኑት የእሸት መቅመስ ሥርዓት ሲሆን፤ ከላይኛው በሰፊው የሚለይ ነው። እሸቱ እንደደረሰ ቆርጠው ባሉበት አጥቢያ ለሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ሳይሰጡ ቤት ውስጥ የሚከናወን ነገር አይኖርም። የእሸቱን መጀመሪያ ለቤተክርስቲያኗ ከሰጡ በኋላ ሁሉ ነገር ተቀድሷል ብለው ስለሚያምኑ እሸቱን መብላት ይጀምራሉ፣ በቆሎው እንደተሰበሰበ ደግሞ ወደ ጎተራ ከመግባቱ በፊት በአስራት መልክ ለቤተክርስቲያን ይሰጣሉ።
ጨባል
የቤንች ብሔረሰብ አባላት የእሸት ወራትን ጠብቀው ምርት ከሰበሰቡ በኋላ ነው እሸት እንቀማመስ የሚሉት። እንዴት ይቀምሳሉ ካላችሁ ደግሞ በአዛውንቶች ወይም ቃልቻ ቤት በመሰብሰብ ነው። በቦታውም ምስጋና ወይም ምርቃት የሚቀርብ ሲሆን፤ በዓሉን ጨባል እያሉ ይጠሩታል። ሥነ ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ ባስና ናይኬስ የሚባሉ የክራር (ሸንጎ) ጨዋታዎችን በቀን ያከናውናሉ። ምሽት ሲሆን ደግሞ በቶሪ፣ ቶህ፣ ዛክ፣ ፍረግን በሚባሉ የድምፅና የትንፋሽ መሣሪያዎች በመታጀብ ናሪ፣ ኪያርኪያም፣ ባባ፣ ኖጲ የተባሉ ዘፈኖችን ሴቶችና ወንዶች በአንድነት ይጫወታሉ። ከዚያ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።
የትከሻ በዓል
የሸኮ ብሔረሰብ የእሸት ቀመሳቸውን ‹‹የትከሻ በዓል›› እያሉ ያከብሩታል። አዝመራ ሲደርስ ምርቱ ከአውሬና ካልታሰበ ዝናብ ተጠብቆ በሰላም እንዲገባ በመጸለይ የሚከናወን ባህላዊ የእምነት በዓል ነው። ሸኮዎች በባህላቸው መሰረት የበቆሎና የማሽላ እሸት ሲደርስ ወዲያውኑ አይመገቡትም፤ ከደረሰው የሰብል ዓይነት ተቆርጦ ምግብ ተዘጋጅቶና ቦርዬ (ጠጅ) ተጠምቆ ለበዓሉ ማድመቂያ ያቀርባሉ። ይህ የተዘጋጀው ምግብ የሚቀርበው ደግሞ በአካባቢው ባሉ የጎሳ መሪዎች ፊት ነው። ከዚያ የአካባቢው የጎሳ መሪ በዓሉን ባርኮ ምግቡ እንዲቀመስ የአካባቢውን የሃይማኖት መሪ (ቡርዣብን) ያዛል።
ርዣቡ ‹‹አምላክ ነፋሱን ጠብቅ፣ አውሬውን ጠብቅ፣ በሽታ ወደኛ አይምጣ ሩቅ አገር ይሄድ›› በማለት የመጀመሪያውን ቦርዴ ከቀመሰ በኋላ ጥቂት ወደ መሬት ያፈሳል፤ ከዚህ በኋላ እንደየማኅበራዊ ደረጃው መጀመሪያ የጎሳ መሪው፣ በመቀጠል የአገር ሽማግሌዎችና ጎልማሳዎች ከቀመሱ በኋላ ወጣቶች ቀምሰው በይፋ የምግብና የመጠጡ ሥነ- ሥርዓት ይጀመራል።
እስከ አራት ቀን ድረስ ባህላዊ ጨዋታዎችን እየተጫወቱ የሚቆዩት የትከሻ በዓሉ፤ ከመከበሩ ቀደም ብሎ በብሔረሰቡ የተጣላ የሚታረቅበት፣ አለመግባባቶች በሽማግሌዎች የሚፈቱበትና ሰላም የሚሰፍንበት በዓል ነው። ይህ ደግሞ ሰብል በሰላም እንዲሰበሰብ፤ በሽታ እንዲርቅ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል። እኛም ይህ ባህል ይጎልብት ይጠበቅ እያልን ለዛሬ በዚህ ቋጨን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 14/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው