ፈጠራ አዲስ ነገር ማስገኘትና መፍጠር በውስጥ ያለን እሳቤ ተግባር ላይ ማዋልን ይጠይቃል። መፍጠር ጥበብ ነው፤ በቀመር የሚለካ። መፍጠር ክህሎት ነው፤ የተለየ ተሰጥዖን የሚጠይቅ። ውስጣዊ ልዩ ፍላጎት፤ አዲስ የሆነ ሀሳብ ማመንጨት፤ የራስ የሆነን ከፍተኛ ጥረትና ተደጋጋሚ ሙከራ የፈጠራ ባለሙያዎች የሁልጊዜ ተግባር ያለሙትን ለማሳካት የሚጠቀሙበት ስንቅ የሚጓዙበት መንገድ ነው።
በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ አዳዲስ ግኝቶች መነሻቸው ፈጠራ ነውና የፈጠራ ባለሙያዎች አሻራ ትልቁን ቦታ ይይዛል። የዓለም ገፅታ መሐንዲሶቹ የፈጠራ ባለሙያዎች የምናየው የቴክኖሎጂ ውጤት መነሻ የምንጠቀመው ሥራ ማቅለያ ቁሳቁስ ሁሉ ምክንያት መሆናቸው መካድ አይቻልም። ቴክኖሎጂ መሠረት ያደረጉ የፈጠራ ውጤቶች ዘመኑን ባገናዘበ መልኩ እየተሻሻሉ አዲስ ነገር እየታከለባቸውና በአገልግሎት ዘርፍ ብዙ ሆነው በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
አገር በቀል የሆኑ ችግር ፈቺ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች መነሻቸው አካባቢያዊ ችግር ነውና ተግባራዊ ሲደረጉ የሚያመጡት ውጤት ከፍተኛ ነው። የፈጠራ ባለሙያዎቹ ለሚያውቁት ችግር ትክክለኛ መፍትሄ ማስቀመጣቸው እና በመፍትሄነት የሚያቀርቡት የፈጠራ ሥራቸው በራሱ በችግሩ እየሞከሩና እያሻሻሉት ስለሚቀጥሉ የተሻለ ውጤት መገኘቱ መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል። ቴክኖሎጂን ከመቀበል፣ ከማላመድና ከመተግበር ባለፈ አዳዲስ ፈጠራዎችን እንዲፈልቁ ማድረግ የአገራት ዋንኛ ትኩረት ሊሆን የሚገባውም ለዚሁ ነው።
በአገሪቱ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች በፈጠራ ሥራ ውስጥ ትልቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለፈጠራ ባለሙያዎች በተለይም ለወጣት የምርምርና ፈጠራ ባለቤቶች የተፈለገውን ያህል ድጋፍ የማድረጉ ልምድ የጎለበተ ባይሆንም የተወሰኑ ጥረትች ግን በመደረግ ላይ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ተካሂዶ በነበረው የፈጠራ ሥራ አውደ ርዕይና ውድድር ተካፋይ የነበሩ ወጣቶች የፈጠራ ሥራ ማቅረባችን ይታወሳል። ዛሬም ሌሎች በመድረኩ ላይ ተገኝተው የነበሩ ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራና ወደፊት ሊሰሩ ያቀዱት የፈጠራ ሥራ ምንነት ልናስቃኛችሁ ወደናል።
በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ የፈጠራ ሥራቸውን ለማስተዋወቅ ብሎም ለመወዳደር ሥራቸውን ካቀረቡ ወጣት የፈጠራ ሥራ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናሆም ታረቀኝ መኖሪያው መቀሌ ከተማ ሲሆን የ12 ክፍል ተማሪ ነው። የናሆም የፈጠራ ሥራ የአገሪቷ ኢኮኖሚ መሠረት የሆነው ግብርናን ለማዘመን የተመቸ በአንድ ማሽን ሦስት የተለያየ ተግባር ለመከወን የሚጠቅም ዘመናዊ የግብርና መሣሪያ ነው።
ገና ልጅ ሳለ የፈጠራ ሥራዎችን መመልከትና አዲስ ነገር መፍጠር ሁሌም ይመኝ የነበረው ተማሪና የፈጠራ ባለሙያው ናሆም፤ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታየውን ችግር የሚፈታበት መንገድ ሁሌም ያሳስበዋል። አርሶ አደሩ ከልፋቱ ያነሰ ዋጋ ማግኘቱ፤ ድካሙን ያገናዘበ አኗኗር ውስጥ አለመሆኑ ለምን የሚል ጥያቄ ይፈጥርበታል። አሁን ላይ ያሉትን የእርሻ መሣሪያዎች ምንነት መለየት፤ ሊሻሻሉ የሚችሉበትን መንገድ ማሰብና ደጋግሞ መሞከር የዘወትር ተግባሩ አደረገ በቆይታም ያሰበውን አገኘ።
አሁን ያሉት የእርሻ መሣሪያዎች በመጠን የገዘፉናለሁሉም የመሬት አቀማመጥ ምቹ አለመሆናቸው በቀላሉ ለመጠቀም የማያስችሉ ናቸው። በናሆም የፈጠራ ሥራ ደግሞ የእርሻ መሣሪያዎች እየለዋወጡ መጠቀም ሳያስፈልግ በአንድ መሣሪያ ብቻ ማረስ በመስመር መዝራትና ማጨድ ያስችላል። ይህ የፈጠራ ሥራ ለማረስ ትራክተር፤ ለመዝራት ሌላ መሣሪያ እንዲሁም በምርት ስብሰባ ወቅት ደግሞ ሌላ የማጨጃ መሣሪያ ከመቀያየርና ገበሬውን ከወጪ ለመታደግ ያግዛል።
በፊት በተለያዩ አገራት ተመርተው አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት የእርሻ መሣሪያዎች፤ በመጠን የገዘፉና ለአጠቃቀምም ሰፊ መሬት ላይ ካልሆነ በቀር አስቸጋሪዎች ነበሩ። በወጣት ናሆም የተፈጠረው መሣሪያ በመጠን በማነስ ነገር ግን በአገልግሎት ከፍ ያለ በመሆኑ በምርት ሂደት አልፎ አርሶ አደሩ ጋር ቢደርስ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት ይችላል።
አሁን ያለው የፈጠራ ሥራ በፋብሪካ ደረጃ በብዛት አምርቶ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ፍላጎት እንዳለውና ይህን ለማድረግ የሚረዳው አካል እንደሚፈልግም ይናገራል። ናሆም ወደፊት በፈጠራ ሥራ ውስጥ ይበልጥ በመሳተፍ ሌሎች አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳለው ይገልፃል። ለዚህ ሦስት የተለያዩ የፈጠራ ሥራ ሞዴሎች ማዘጋጀቱንና ወደ ተግባር ሊለውጣቸው መሰናዶ ላይ መሆኑን ያስረዳል።
በውድድሩ ላይ ለመካፈል በሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከተገኙት ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች መካከል አፋር ክልልን በመወከል የተገኘው ካሚል አብዱ፤ ከአዋሽ ሰባት ኪሎ አካባቢ የመጣ የ12 ክፍል ተማሪ ነው። የካሚል የፈጠራ ሥራ ውሃን ማሰራጨት የሚያስችል የውሃ መሳቢያ ሲሆን ከዚህ በፊት በአገር ውስጥ መሰል ምርት እንደሌለና በአካባቢው ባለ ማህበረሰብ ትልቅ ተቀባይነት አግኝቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሆነ ይናገራል።
ለውድድር ካቀረበው የውሃ መሳቢያ መሣሪያው በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ ውድድሮች ላይ የተለያዩ ሞዴል ሥራዎች በማቅረብ መሳተፉን የሚናገረው የፈጠራ ባለሙያው ካሚል ከልጅነቱ ጀምሮ ለተመለከታቸው የፈጠራ ሥራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት መመልከቱ መነሳሳት እንደፈጠረበት ይህም ወደ ፈጠራ ሥራ እንዲያተከር እንዳደረገውና ለሙያው ትልቅ ፍቅር እንዳሳደረበት ይናገራል።
በውሃ ኃይል የሚሰራው ይህ የውሃ መሳቢያ ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል መተዳደሪያ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋንኛ መሠረት የሆነው ግብር የተሻለ ውጤት ላይ ያደርሰዋል የሚል እምነት እንዳለው የፈጠራ ባለሙያው ካሚል ያስረዳል። በውሃ እጥረት ምክንያት በዓመት አንዴ ብቻ የሚመረትበትን ሂደት ለመለወጥና ውሃ ካለበት አካባቢ መሣሪያውን በመጠቀም በማሰራጨት የግብርና ሥራ ማዘመንና በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ማምረት የሚያስችል ይሆናል።
‹‹የፈጠራ ሥራው ድጋፍ አግኝቶ በስፋት ማምረትና ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ከተቻለ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ያለው ሚና የላቀ ነው›› የሚለው የፈጠራ ባለሙያው ካሚል፤ ሥራው ወደ ፋብሪካ ገብቶ በተሻለ መልክ እንዲመረት ድጋፍ እንደሚፈልግና የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቋል።
ወጣቶች የሚያደርጉትን የፈጠራ ሥራ ስኬታማ በሆነ መልክ ተግባራዊ እንዲሆንና ማህበራዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ለፈጠራ ባለሙያዎቹ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ከባለ ድርሻ አካላት የሚጠበቅ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በመሆኑም በፈጠራ ሥራ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ትኩረት መስጠት ያሻል መልዕክታችን ነው። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ኅዳር 12/2012
ተገኝ ብሩ