የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚመሠረቱት የርዕዮተ ዓለም፤ የአስተሳሰብና የአመለካከት ተመሳሳይነት ባላቸው ጥቂት ልኂቃን አማካኝነት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ እነዚህ ልኂቃን የመጀመሪያ ሥራቸው የፓርቲ ፕሮግራም መቅረጽ ይሆናል፡፡ የፓርቲው ፕሮግራም ይዘት ሰፊ ሊሆን ይችላል፤ ቢሆንም መቅረት የሌለባቸው ጉዳዮች የፓርቲው ዓላማ፤ የአፈጻጸም ሥልት፤ የፓርቲው ተግባራት፤ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕይታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በችኮላና በልምድ ማጣት የተነሳ ልኂቃኑ የሌሎች ፓርቲዎችን ፕሮግራሞች ሙሉ ለሙሉ ለመቅዳት ይፈልጉ ይሆናል ግን ትዕግሥትና ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የፓርቲውን ዓላማና ተግባራት ለማስፈጸም የፓርቲው መሥራች አባላት የሥራ ክፍፍል ያደርጋሉ፡፡ ጊዜያዊ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይመርጣሉ፡፡ ይህ ጊዜያዊ ኮሚቴ በጠቅላላ ስብሰባ በተመረጠ ቋሚ ኮሚቴ እስከሚተካ ጊዜ ድረስ የፓርቲውን ተግባራት ያካሂዳል፡፡ የጊዜያዊውም ሆነ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ተግባር የፓርቲ አባላት ምልመላ ይሆናል፡፡ የአባላት ምልመላ በፓርቲው አመራር በተዘጋጀ የምልመላ መስፈርት ብቻ ይሆናል፡፡ መስፈርቱ የሚያስፈልገው ፓርቲው የቤተሰቦች፤ የመንደርተኞች፤ የጎጠኞች፤ የጥቅመኞች መጠራቀሚያ እንዳይሆን ለመከላከል ነው፡፡ መስፈርቱም ኖሮ ቀዳዳ እየተፈለገ ለፓርቲው ተልዕኮ፤ ዓላማና ተግባራት ተስማሚነት የሌላቸው አባላት ሊመለመሉ ስለሚችሉ የአባላት ክትትልና ቁጥጥር ኮሚቴ ከመነሻው መቋቋም ይኖርበታል፡፡ የክትትልና የቁጥጥር ኮሚቴው የአባላትን ታማኝነት ማረጋገጥ ግዴታው ነው፡፡
የክትትልና የቁጥጥር ኮሚቴ የፓርቲ አባላት የፓርቲውን ዓላማ በማንኛውም ጊዜና ቦታ ለማሳካት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረጋቸውን ሥልት አውጥቶ ይከታተላል፡፡ አፈንጋጮች ከተገኙ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ፓርቲውን ያጸዳል፡፡
ፓርቲውን ሊገጥሙት ከሚችሉ አደጋዎች ዋናው ሰርጎ ገብነት ነው፡፡ ሰርጎ ገቦች ከሌላ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ወይም ከገዢው ፓርቲ ለስለላ የሚላኩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የሰርጎ ገቦች ተልዕኮ የጠንካራ ፓርቲን ምስጢር መልቀምና ለላካቸው ክፍል ማቅረብ ሊሆን ይችላል፡፡
ፓርቲዎች ከአባላት ሊደርስባቸው ከሚችለው ጉዳት አንዱ የአባላት መክዳት ነው፡፡ አባላት የሚከዱበት ምክንያት አንዱ በሰርጎ ገቦች ስብከት ሊሆን ይችላል፡፡ ከሚከዱ አባላት ውስጥ የፓርቲውን ምስጢር የሚያውቁ ከሆኑ ፓርቲውን ሊጎዳ እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ፓርቲውን ለመክዳት የሚያስብ አባል ፍላጎቱ እንዳይታወቅበት ስለራሱ ማንነት ፍጹም ምስጢረኛ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የክትትልና የቁጥጥር ኮሚቴን ለማታለል የጠንካራ አባልነት ጭምብል በማጥለቅ ታማኝ የፓርቲ አባል መስሎ ይታያል፡፡ በመሆኑም ለኮሚቴው አስቸጋሪ አወናባጅ ሆኖ ይቆያል፡፡
ይህ ዓይነቱ የፓርቲ አባል ብዙውን ጊዜ በገዢው ወይም በተቀናቃኝ ፓርቲ በገንዘብ የሚገዛ፤ ፓርቲውን የማፍረስ ተልዕኮ የሚሰጠው ሰው ነው፡፡
ሌላው አስከፊ የፓርቲ አባል ፀባይ ደግሞ ዋልጌነት ነው፡፡ ዋልጌነት በሥነ-ምግባር ያልታነጸ ግለሰብ መገለጫ ነው፡፡ ሲያመርና ሲቀልድ አይታወቅበትም፤ ሰዎችን አሳስቶና አዘናግቶ ስሜታዊነቱን ያንፀባርቃል፤ ይተነኩሳል፤ እጀ-መናኛነትም አያጣም፡፡ የፓርቲውን ገንዘብና ንብረት ለመመዝበር ቀዳዳ ይፈልጋል፡፡ ለፓርቲው መዋጮ ላይከፍል ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ የዋልጌነት መገለጫዎች ከፓርቲው የክትትልና የቁጥጥር ኮሚቴ ዕይታ ውጭ በሚሆኑበት ጊዜ ፓርቲው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፤ የዋልጌዎች መጠራቀሚያ ይሆናል ማለት ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዋልጌዎች ፓርቲያቸውን ቦርቡረው ለገዢው ፓርቲ ጭዳ ወይም መስዋዕት ያደርጉታል፡፡
ፓርቲው በየጊዜው ራሱን ከከጂዎች፤ ከሠርጎ ገቦችና ከዋልጌ አባላት አጥርቶ ጠንካራ አባላት ያሉት መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የሚቀጥለው ዋናው ተግባሩ መደራጀት ነው፡፡ ለዚህም የፓርቲ አባላትን መዋጮ በሚገባ መሰብሰብ፤ እርዳታ ማሰባሰብ፤ ዕርዳታ ለሚሰጡ ወገኖች የመተማመኛ ቃል መግባትና ቃልንም ወደ ተግባር መለወጥ፤ የአባላት ሥልጠና፤ የመረጃ ቅብብሎሽ አስፈላጊ ይሆናሉ፡፡ እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎችንም የፓርቲ አቅም ግንባታ እርምጃዎች ፓርቲው ከወሰደ በኋላም አቅሙና ዓላማው የማይጣጣሙ ሆነው ከተገኙ ሌሎች የመደራጀት ሥልቶችን መቀየስ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ከነዚህም ሥልቶች አንዱ ከሌላ በዓላማ ከሚመሳሰል ፓርቲ ጋር ውህደት መፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡በአንፃሩ ከልምድ እንደታየው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንጃ ፈጥረው ሊገነጠሉ ይችላሉ፡፡
ፓርቲው እየጠነከረ ቢሄድም በአንጀኞች ሊፈተን ይችላል፡፡ አንጃን የሚፈጥሩት የሥልጣን ጉጉት ያለባቸው የፓርቲ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንጃውን ቀስ በቀስ ከፓርቲው እንዲገነጠል ያደርጉታል፡፡ ተገንጣዩ አንጃ ፓርቲ መሥርቶ በምርጫ ቦርድ ይመዘገባል፡፡ ፓርቲዎች በዚህ መልኩ እየተበተኑ ይሄዳሉ ገዢው ፓርቲም ይፈነድቃል፡፡
ከመገንጠልና ከመበተን የተረፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገጠማቸው ችግር ራሳቸውን ለመከላከል በውስጣቸው የአባላትን ጥራት በድጋሚ ማረጋገጥ ግድ ይሆንባቸዋል፡፡በተለይም የወገንተኝነት፤ የጥቅመኛነት፤ የሙሰኝነት ዝንባሌ የሚታይባቸውን አባላት ፓርቲዎቹ ማረቅ ወይም ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ የማጥራት ሥራ በኋላ ፓርቲዎች ለምርጫ ውድድር ዝግጅት ሊጀምሩ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
ፓርቲዎች ለምርጫ ሲዘጋጁ የሚያከናውኗቸው ልዩ ልዩ ተግባራት አሉ፡፡ ከነዚህም ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የእጩዎች ዝግጅት፤ ለሚዲያ የሚቀርብ የጽሑፍና የማቴሪያል ዝግጅት፤ የሕዝብ ቅስቀሳ ፕርግራምና የመሳሰሉት በቅድሚያ ይዘጋጃሉ፡፡ የእጩዎች ዝግጅት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው፡፡ የእጩ መመልመያ መስፈርት ማዘጋጀትና በዚሁ መሠረት እጩዎች በልዩ ልዩ አካባቢ ሊወዳደሩ የሚችሉበትን ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ አንድ እጩ የሚፈጥረው ስህተት ሊታረም የማይችል ጉዳት በፓርቲው ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለዚህ የእጩ ምልመላ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያሚያሻው ተግባር ነው፡፡
ጥንቃቄ ለማድረግ ከሚረዱት እርምጃዎች ውስጥ እጩዎች የፓርቲውን ፕሮግራም በጥልቀት እንዲያውቁትና እንዲያጠኑት ማድረግ በዚህም ተመስርቶ እጩዎችና አባላቱ ውይይት እንዲያደርጉ፤ ከሕዝብ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን በመገመት በማንሳትና በመከራከር እጩዎችን ማዘጋጀት ይቻላል፡፡እጩዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ብቃታቸው ሲረጋገጥ ፓርቲው ሕዝብን መቀስቀስ ይጀመራል፡፡ እጩዎች የፓርቲያቸውን ፕሮግራም ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ፓርቲው ፕሮግራም ያወጣል፡፡ ይህ የቅስቀሳ ፕሮግራም አገሪቱን በሙሉ ወይም በከፊል የሚያዳርስ መሆኑ በቅድሚያ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
ቀደም ሲል ስለ ፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታና ስለ አባላት ምልመላ ችግሮች መግለጽ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት እስከ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ባለው 27 ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ የታየው የአገዛዝ ስልት ፓርቲዎችንም ሆነ አባሎቻቸውን በመከፋፈል፤ በማጋጨት፤ በማፍረስ፤ በማሰር፤ በመግደል ገዢው ፓርቲ ያደረሰውን ጥቃት ለማሳየት ነው፡፡ የጥቃቱ ዓላማ ፓርቲዎቹንና አባላቱን የገዢው ፓርቲ ጥገኛና ተለጣፊ ለማድረግ ነበር፡፡ የገዢው ፓርቲ በሥልጣን ለመቆየት ሲል ጠንካራ ተቀናቃኝ የመሰሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና አባላቱን በማጥቃት እንዲጠፉና ከአገርም እንዲሰደዱ በማድረግ በምትካቸው አድርባዮችንና ተለጣፊዎችን አስርጎ በማስገባት የፖለቲካውን ምኅዳር በማጥበብ ሥልጣንን አጥብቆ መያዝ ዋናው ዓላማው ነበር፡፡ ፖለቲካውን በብቸኝነት ለማሽከርከርና የአገሪቱን ሀብት ሙሉ በሙሉ ለመያዝና ለመመዝበር ገዢው ፓርቲ ችሎ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሀብት አሁን በአገሪቱ ከሚገኘው ሕዝብ ከእጥፍ በላይ ለሚሆነው ይበቃል፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሥራት ከተቻለ አገሪቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሁሉ የምትበቃ ናት፡፡ ግን በስግብግብና ጠባብ ፖለቲከኞች ምክንያት አገሪቱ ለሕዝቦቿ ሳትሆን ቀርታለች፡፡ሕዝቦቿ በገዢዎቿ እየተበደሉ፤ እየተራቡ፤ እየታረዙና ጤናቸው እየታወከ፤ ሕፃናትና እናቶች በሞት እየተቀጠፉ ይገኛሉ፡፡በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሲመጣ አለአንዳች ጥርጥር ሕዝቡ ቢያንስ እንደሰው መኖር ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በባርነት ተተብትቦ ኖሯል፡፡ ባርነቱ የሚታየው በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳይ ሁሉ ነበር፡፡ በፖለቲካው መስክ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብት ለይስሙላ በሕገመንግሥቱ ላይ ቢጻፍም በተግባር ግን ተተርጉሞ አያውቅም፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን ተለጣፊ ካልሆነ በቀር ሕዝቡ የበይ ተመልካች ሆኖ ኖሯል፡፡ በማኀበራዊ ዘርፍም ቢሆን ትምህርቱም ሆነ ጤናው እጅግ የዘቀጠ ነበር፡፡ በግብር ከፋይነቱ መጠን ያገኘው መንግሥታዊ ግልጋሎቶች እጅግ አነስተኛ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከባርነቱ የሚያወጣው መንግሥታዊ ለውጥ እየታየ ነው፡፡
የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በተለይም ከመጋቢት ወር 2010ዓ.ም ጀምሮ ሥር ነቀል ለውጥ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለውጡ ሕዝቡን ከባርነት ለማውጣት የሚያስችል የነጻነት ፋና ወጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለስሙ ነፃ አገር ነበረች፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው 27 ዓመታት አገሪቱ የባርነት ቀንበር ተጭኖባት ኖሯል፡፡ ይህ የባርነት ጠባሳ ለብዙ ዘመን ከአገሪቱ የሚወገድ አይመስልም፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በአገሪቱ የሰፈነው የባርነት ሥርዓት እጅግ አሳፋሪ ሆኖ ይኖራል፡፡ ጥቂት የገዢው ፓርቲ አስኳል የሆኑ አረመኔዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያደረሱት በደል በቀላሉ ከታሪክ የሚሰረዝ ወይም የሚረሳ አይሆንም፡፡
የለውጥ አመራሩ ያፈለቀው የመደመር፤ የፍቅር፤ የነጻነትና የአንድነት መርህ ለሕዝቡ ዕፎይታ ሰጥቶታል፡፡ ይህ አዲስ አመለካከት ሕዝቡን እጅግ ያስደሰተው ሲሆን፣ ለውጡን ዕውን ያደረጉት ግለሰቦች በተለይም ዶ/ር አብይ አህመድ፤ አቶ ለማ መገርሣ፤ አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኢሕአዴግ የውስጥ ትግል አካሂደው አዲሱን ለውጥ ለሕዝቡ አቅርበውለታል፡፡ ለለውጡ እነዚህ የቁርጥ ቀን ልጆች ሕይታቸውን ሰውተዋል ቢባል ከእውነት የራቀ አይደለም፡፡ በዚህም መስዋዕትነት በአገሪቱ ውስጥ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጭላንጭል መታየት ጀምሯል፡፡
ዴሞክራሲን የተጠማና ሰብዓዊ መብቱ የተገፈፈ ሕዝብ የዴሞክራሲንና የሰብዓዊ መብት ጭላንጭል ሲያይ በደስታ ብዛት የሚያደርገውን ሊያጣ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት ሕዝባዊ ልሂቃን ሕዝቡን በትክክለኛው አቅጣጫ የመምራት ግዴታ አለባቸው፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት አንድ ጊዜ ከተቀመሰ ሱስ ስለሚሆን የሕዝብን ፍላጎት የፖለቲካ ኃይሎች የማርካት ልምዱ ስለማይኖራቸው የመብት አያያዙ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት አማካኝነት መብቱ ሲገፈፍ የነበረ ሕዝብም ሆነ ከውስጡ የወጡ ልኂቃን ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አያያዝ እንግዳ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ምናልባት ልኂቃኑ በንባብ እንጂ በተግባር ላያውቁት ስለሚችሉ በድፍረት ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩ ኢትዮጵያ ድጋሚ የርዕዮተ ዓለም መሞከሪያ ላቦራቶሪ ልትሆን ትችላለች፡፡
አንድ ጊዜ የኮሚኒስት እንዲሁም የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሌላ ጊዜ ደግሞ መርህ-አልባ ሥርዓት እየተፈጠረ ወደፊት በመሄድ ፋንታ ወደኋላ መቅረት ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ስለዚህ የአገሪቱ የፖለቲካል ሳይንቲስቶችና ፈላስፎች እንዲሁም ሌሎች ምሁራን ለአገሪቱ ተስማሚነት ያለው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ሥርዓት የሚተከልበትን ሥልት ሊቀይሱ ይገባል፡፡ አስፈላጊ አማራጭ ከሆነም እነዚህ ምሁራን የሕዝብ ተቆርቋሪ አምባገነንነት (benevolent dictatorship) ያለው መንግሥት ሊመሠረት የሚችልበትን ሥልት ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡
ከላይ በተጠቀሱት አማራጮች ላይ ተመሥርቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊደራጁና አባላቱም በጥንቃቄ ተመርጠው በፕሮግራሞቻቸው መሠረት ሕዝብን ሊቀሰቅሱና ለምርጫ ሊዘጋጁ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
ጌታቸው ሚናስ
This blog is a great mix of informative and entertaining content It keeps me engaged and interested from start to finish
Your positivity and optimism are contagious It’s impossible to read your blog without feeling uplifted and inspired Keep up the amazing work