– የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ያደርጋል
– ህብረ ብሄራዊ አገራዊ አንድነትን ያጠናክራል
አዲስ አበባ፡- አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሄራዊ አገራዊ አንድነትን በማጠናከርና አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን በመገንባት የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን እንደሚያደርግ የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢህአዴግንና የአጋር ድርጅቶችን ውህደት አስመልክቶ ትላንት ከሰዓት በኋላ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሄራዊና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር በህዝቡ ዘንድ አገራዊ አስተሳሰብ እንዲዳብር ጠንክሮ ይሠራል።
የለውጡን ስርዓት በተደራጀ ተቋማዊ አሠራር በመምራት አሁን አገሪቱ የተወጠረችባቸውን የጽንፈኛ ብሄርተኝነት አመለካከት አሰላለፎች እንዲሁም በአገራዊ አንድነት ስም የብዝሃነት ጉዳዮችን ተገቢ ግምት ያለመስጠት አተያዮች በማስተካከል አዲሱ ፓርቲ አገራዊ አንድነት የሚጠናከርባቸው ሁኔታዎች ላይ እንደሚሠራ አቶ ደመቀ አብራርተዋል።
ፓርቲው ጠንካራ አገራዊ አስተሳሰብን የመገንባት ሥራ በትኩረት እንደሚሄድበት የተናገሩት አቶ ደመቀ፣ ለዚህም ያለፉትን ጠንካራ ጎኖች በማጎልበትና ስህተቶችን በማረም እንደሚሠራ ገልጸዋል። ኢህአዴግ ካጋጠመው ችግር አውጥቶ አገሪቱን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር ይተጋል የተባለው አዲሱ ፓርቲ ዋና ግቡ አገሪቱን ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ በማመቻቸትና በማፋጠን የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ እንደሆነ አቶ ደመቀ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
አቶ ደመቀ አዲሱ ፓርቲ ህብረ ብሄራዊ ፌዴራሊዝምን አጠናክሮ ማስቀጠል፣የግለሰብንና የቡድን መብቶችን አጣጥሞ ማስኬድ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን በህብረተሰብ ተሳትፎ መመለስ፣ የብሄር ማንነትንና አገራዊ አንድነትን ማጣጣምና ብዝሃነትን ማጠናከር ምሰሶዎቹ መሆናቸውን፤ የዜጎችንና የህዝቦችን ክብር መጠበቅ፣ ፍትሕን ማንገስና ህብረ ብሄራዊ አንድነት የፓርቲው ዕሴቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ፓርቲው የዳበረና አሳታፊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት፣ የሚመዘገበውም ልማት ጥራት ያለውና ዘለቄታዊነቱን ያረጋገጠ በማድረግ በእያንዳንዱ ህብረተሰብ ኑሮ ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ተደርጎ እንደሚሠራ ጠቅሰው፣ በማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ዕሴትን የማበልጸግ ዝርዝር ዓላማዎች እንዳሉትም አመልክተዋል።
አቶ ደመቀ በመግለጫቸው ውህደቱን በተመለከተ የሚነሱ የተሳሳቱ አመለካከቶች በህዝቦች መካከል ግጭትን የሚቀሰቅሱ በመሆናቸው መታረም እንደሚገባቸው ያነሱ ሲሆን፣ አገርን ለመምራት የሚደረግ ምንም ድብብቆሽ የለም ብለዋል።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባካሄደው ስብሰባ ውህደቱን ያልተቀበሉ የህወሓት አመራሮች ያሳዩት አቋም አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ የተሻሉ አማራጮች ካሉ እንደሚታዩ ፍንጭ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
ድልነሳ ምንውየለት