አዲስ አበባ፦ አንድ አላማና ተመሳሳይ የፖለቲካ መስመር ያላቸው ፓርቲዎች መዋሃዳቸው ተገቢና ወቅታዊ እርምጃ መሆኑን አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተናገሩ::
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፣ ኢህአዴግ ለ28 ዓመት ግንባር ነኝ እያለ መቆየቱ አግባብ አለመሆኑንና አጋር የተባሉት ፓርቲዎችም ይህንን ሁሉ የተፈጥሮ ሀብትና አቅም ይዘው ምንም ድምፅ ማጣታቸው በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር:: አሁን ላይ እነዚህ ፓርቲዎች ወደ አንድ መጥተው መዋሃዳቸው ተገቢ ነው::
አጋር ድርጅቶች የመዋሃድን ጥያቄ ያነሱት ዛሬ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር በየነ ፤ ከዚህ ቀደም ሲሰጣቸው የነበረው መልስ አግላይ እንደነበር፤ ‹‹ማህበራዊ መሰረታችሁ ቋሚነት የለውም ሌላም ሌላም እየተባለ አርፋችሁ ቁጭ በሉ የሚለውም አካሄድ አዋጭ ባለመሆኑ እነዚህን አካላት ማሰባሰቡ ተገቢም መሰረታዊም ነው›› ብለዋል::
ፕሮፌሰር በየነ ‹‹ውህደት የሚለውን አጀንዳ ኢትዮጵያውያን የምንፈልገው የአገርና የህዝቦች አንድነት ስለሚያመጣ ነው፤ ሆኖም አፍራሽ አስተሳሰብ ያላቸው አካላት እጃቸውን መሰብሰብ የኖርባቸዋል›› ብለዋል፡፡ ውህደቱ መልካምና ተቀባይነት ያለው ቢሆንም የአገሪቱን ሰላም የሚያናጋበት ሁኔታ እንዳይፈጠር በተቻለ መጠን ሁሉን ያቀፈና የሁሉንም ይሁንታ ያገኘ ሊሆን ይገባል፡፡ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል::
ፕሮፌሰር በየነ ‹‹ምን ያህል እርግጠኛ እንደሆነ ባላውቅም የህወሓት ኩርፊያ ረጅም መንገድ የሄደ ነው:: እንደምሰማውም የራሳችንን አማራጭ እንወስዳለን እያሉም ነው፤ ይህ ግን የኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ ሊሆን አይገባም›› ብለዋል:
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ገለጻ ፤ ውህደቱ ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር ይጋጫል ሲሉ ይሰማል፣ አንድን ነገር ማጋጨት ከተፈለገ ቀላል ነው፣ ሆኖም የፌዴራል ስርዓቱን ከ25 ዓመት በላይ ጥቅምና ጉዳቱ ታይቷል፤ ችግሩን አስተካክሎ እንሂድ ማለት ተገቢና አዋቂዎች የሚያደርጉት ተግባር ነው፤ ሆኖም በደፈናው ይጋጫል ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም::
ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ የማዕዘን ድንጋይ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ህዝብን ይዞ ችግሮቹን እያስተካከሉ አስፈላጊ ሲሆንም ህዝበ ውሳኔ እያሰጡ መቀጠል ይቻላል፣ ሆኖም “እኔ ያልኩት ካልሆነ” የሚለው አካሄድ አገሪቱን “ከለውጥ ወደ ነውጥ ” ያሸጋገራት ይሆናል እንጂ የትኛውም ባለስልጣንም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ቢመጣ ለውጥ እንደማይመጣ አስረድተዋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
እፀገነት አክሊሉ