አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 190 የጦር መሳሪያዎች ፣62 ሺ 183 ጥይቶች መያዙን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገጹት፤ በሩብ ዓመቱ 74 ልዩ ልዩ ጠመንጃዎች፣ 115 ሽጉጦችና አንድ ቦንብ በድምሩ 190 የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል::
አቶ ጄይላን እንዳብራሩት፣ በቁጥጥር ስር ከዋሉት 62 ሺ 183 ጥይቶች መካከል አንድ ሺ 570 የብሬንና ስምንት ሺ 484 የኤም 14 (M14) ጥይቶች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 52 ሺ 129 ደግሞ ልዩ ልዩ ጥይቶች ናቸው:: ኢትዮጵያ ባልተረጋጉ አገራት መካከል መገኘቷና ግርግር መብዛቱ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያያዎች ዝውውር እንዲባባስና የመተላለፍ ዕድላቸው ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን አቶ ጄይላን አብዲ ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የሰላም እጦት ምክንያት የጦር መሳሪያ ስርጭት ሊጨምር መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የነፍስ ወከፍ ብቻ ሳይሆን የቡድን መሳሪያዎች ጥይቶች የተያዙበት ሁኔታ ለጦርነት የተዘጋጀ ኃይል ያለ ያስመስለዋል፤አገሪቱ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ያልተረጋጋ መሆኑ እንደአባባሽ ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
አቶ ጄይላን በቦሌ ኤርፖርት በኩል የጦር መሳሪያ ሊገባ ሲል መያዙን አስታውሰው፤ ‹‹መሳሪያዎቹ ራስን ለመከላከል አንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል ፤ ህገ ወጥ ዝውውሩን ያባባሰው ፍላጎቱና ምቹ ሁኔታው በመሆኑ ግርግር መብዛቱ አዘዋዋሪዎች ሕገ ወጥ ተግባሩን ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል›› ብለዋል፡፡
አሁን ባለው አጠቃላይ ሁኔታ ጠበቅ ያለ አሠራር ስለሌለ ችግሩን እንዳባባሰው ፤ሌላው ቀርቶ በመንግሥት እጅ ያለው መሳሪያ የት እንዳለና በየሆቴሎች ለጥበቃ ተብሎ የተወሰደ መሳሪያ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እንኳ እንደማይታወቅና በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ አስተዳደሩ ችግር ላይ እንዳለም አቶ ጄይላን ጠቁመዋል፡፡
ወንጀሉ በጣም አደገኛ፣ ለአገርና ለሕዝብም አስጊ ነው ያሉት አቶ ጄይላን፤ በወንጀል ድርጊቱ በሚሳተፉት ላይ ሕጉ የሚጥለው ቅጣት አነስተኛ ስለሆነ በማስረጃ እጥረት ተጠርጣሪዎች በዋስ እንዲለቀቁ ምክንያት መሆኑንና አስተማሪ ቅጣት እንደማይጥልም አብራርተዋል፡፡
ወንጀሉን መቀነስ እንጂ ከስር መሰረቱ ማድረቅ አይቻልም፤ችግሩን ለመቀነስም ራሱን የቻለ ህግ ያስፈልጋል፤ እንደ ፌዴራል የተከማቸውን ጦር መሳሪያ ወደ አንድ ቋት ለማሰባሰብ የሚያስችል ሕግ ሊኖር ይገባልም ብለዋል፡፡
አቶ ጄይላን በፖሊስ ሥራ ብቻ የጦር መሳሪያ ዝውውሩን መከላከልና መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው፤ ወቅቱ ሰላም ነው ብሎ ተረጋግቶ መቀመጥ የሚቻልበት ጊዜ እንዳልሆነ፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና ምሁራንም ህብረተሰቡን በወንጀል ድርጊት እንዳይሳተፉ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ሕግ ቶሎ ማጽደቅ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል፡፡ አቶ ጄይላን የፌዴራል ፖሊስ በየኬላዎች የጦር መሳሪያ እንዳያልፍ ከፍተኛ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን፣ በየከተሞችም ድንገተኛ ፍተሻ ሲያደርግም የተያዙ የጦር መሳሪያዎች መኖራቸውን አመልክተው፤ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎቹን ለማዘዋወር የሚጠቀሙበት ስልት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፣
ኮሚሽኑ ከ2009 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም አንድ ሺ 917 ልዩ ልዩ የጦር መሳሪዎች፣ 196 ሺ 474 ጥይቶች፣ አምስት ሺ 954 ሽጉጦች፣ 117 የእጅ ቦንቦች፤ እንዲሁም አንድ ብሬን፣ አንድ ኤም 14 እና አንድ ላውንቸር የቡድን መሳሪያዎች ተይዘዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
ዘላለም ግዛው