• በ2012 ሩብ ዓመት 700 ሚሊዮን ዶላር ቀጥታ ኢንቨስትመንት አግኝታለች
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አገር እየሆነች በመምጣቷ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ ፤ ከአፍሪካ ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ መሆኗን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ፡፡
አገሪቱ በ 2012 ሩብ ዓመት ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን አግኝታለች፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የዓለም ባንክ በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ከሆኑ አገሮች መካከል አንዷ በመሆን ከምሥራቅ አፍሪካ የመሪነቱን ስፍራ ይዛለች ፤ ከአፍሪካ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ኮንጎና ሞሮኮን በመከተል አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህም ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ሃገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን የሚያመላክት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ “ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መኖሩ፣ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱና በቀላሉ ሊሰለጥን የሚችል የሰው ኃይል መኖሩ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል” ብለዋል፡፡
የህዝብ ቁጥሯ ከፍተኛ መሆኑ በራሱ ለኢንቨስተሮች ሰፊ የገበያ ዕድል የሚፈጥርና ተመራጭ እንድትሆን ተጨማሪ ዕድል የፈጠረላት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያላት ተመራጭነት እየጨመረ በመምጣቱ በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሰባት መቶ ሚሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትምንት መሳብ መቻሏንም ገልጸው፣ ይህ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 15 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም ተናግረዋል፡፡
የተመዘገቡ ስኬቶች የሚያበረታቱ ቢሆንም የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኃይል አገልግሎት መቆራረጥና የመሰረተ ልማት አውታሮች በበቂ ሁኔታ አለመሟላት የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ችግሮቹን ለመቅረፍና ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በመሳብ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ውስጥ ዘርፉ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ መሠራት እንዳለበትም
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
ይበል ካሳ