አዲስ አበባ፡- ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆችን፣ የትምህርት ጥራትን የማያስጠብቁ ባለሙያዎችንና ኃላፊዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ አዋጅ መረቀቁን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
በትምህርት ሚኒስቴር የአገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዬሴፍ ሽፈራው፤ረቂቅ አዋጁ በህመም፣ በትምህርት ተቋማት አለመኖር ወይም መፈናቀል ካልሆነ በስተቀር ልጅን ወደ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዳይገባ የሚያደርግ ወላጅ ወይም አሳዳጊ፣ የትምህርት ጥራት የማያስጠብቁ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች በወንጀል ሕጉ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
መንግሥት ማንኛውም ሕፃን አጠቃላይ ትምህርት እንዲያገኝ ተቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት የተናገሩት አቶ ዮሴፍ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የትምህርት ጥራት ከተጠበቀው በታች መውረዱ ሲረጋገጥ ከፌዴራል እስከ ታችኛው እርከን ያሉት የአስተዳደር ኃላፊዎች፣ ርዕሰ መምህሩና መምህራን ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።
ርዕሰ መምህሩ ለትምህርት ዕደሜያቸው የደረሱ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መከታተላቸው እና አለማቋረጣቸውን፣ እንዲሁም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ተማሪዎችን መዝግቦ የመያዝ ግዴታ እንዳለበትም ረቂቁ እንደሚያብራራ አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።
እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ፤ የረቂቅ አዋጁ ዓላማ ተማሪዎች ለመጪው ህይወታቸውና ለቀጣዩ የትምህርት እርከን በዝንባሌ፣ በፍላጐትና በእውቀት ማዘጋጀት። የማኀበራዊ ኃላፊነት መንፈስ፣ የሥራ ክቡርነት፣ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ልዩነቶችን የማክበር አስተሳሰብን፣ የሰብዓዊ መብትንና የዴሞክራሲን አስተሳሰብን ማስረጽ። ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን እንዲሁም በጐ የሰው ልጅ ሥራ ውጤቶችን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አላማ ያደረገ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፤ የትምህርት አቅርቦት ማሻሻል፣ ጥራት ያለው ትምህርትን በፍትሐዊነት ተደራሽ ማድረግ፣ እያንዳንዱ ሕፃን ነፃና ግዴታ ትምህርት ማግኘት፣ የትምህርት አስተዳደርን ማሻሻል፣ የሀብት አጠቃቀምን ወጪ ቆጣቢ ማድረግ፣ የተማሪዎችን የማሰብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ጥረት ማበረታታት በረቂቅ አዋጁ የተካተቱ መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ዮሴፍ ‹‹ረቂቅ አዋጁ በህግ መንግሥቱ የተቀመጠና አገሪቱ የፈረመቻቸውን ድንጋጌዎች ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል። እስከአሁን የአጠቃላይ ትምህርት በተበታተኑ ሕጎችና ደንቦች ሲመራ ነበር። መንግሥት የሚከተለውን የትምህርት ልማት አቅጣጫ ተቃኝቶ የወጣ ሁለንተናዊ የአጠቃላይ ትምህርት ህግ አልነበረም። ረቂቁ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ የህገ መንግሥቱን ድንጋጌና የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል›› ብለዋል።
የአዋጁ ረቂቅ ፍኖተ ካርታው የሚያመላክታቸውን ተጨማሪ ሃሳቦች አጣጥሞ ለመሄድ ተብሎ መዘግየቱን ጠቅሰው፤ የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ካመላከታቸው ጉዳዮች ዋናዎቹ የአጠቃላይ ትምህርት ህግና የፖሊሲ ማሻሻያ ዋናዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ዮሴፍ ማብራሪያ ህጉ ተማሪዎች መሰረታዊ እውቀትና ስብዕና እንዲገነቡ ያደርጋል። መንግሥት በህገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ የገባውን ቃል ለመተግበር እና ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር ያስችላቸዋል። ፍትሐዊ የትምህርት ተደራሽነት፣ የትምህርት ጥራትንና ያልተማከለ የትምህርት አስተዳደርን ለማዘመን ያስችላል።
ረቂቅ አዋጁ 111 አንቀፆች እንዳሉት ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራሮች ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል። ከፍተኛ አመራሮቹ ከተወያዩበት በኋላ በቀጣይ የትምህርት ተቋማትና የትምህርት ባለሙያዎች እንዲወያዩበትም ይደረጋል። በመጨረሻም በጠቅላይ ዐቃቢ ህግ ከታየ በኋላ ለህግ አውጪው ቀርቦ እንደሚጸድቅም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ