አዲስ አበባ፡- በመተማ በኩል ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘውን የባቡር መስመር ግንባታ የአዋጭነት ጥናት የሚያካሂድ ድርጅት መረጣ እየተካሄደ መሆኑን ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ኃላፊ አቶ የኋላሸት ጀመረ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ሁለቱ አገራት የጋራ የቴክኒክ ቡድን አቋቁመው እየሠሩ ናቸው። አገራቱን በባቡር መሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ገንዘብ የአዋጭነት ጥናት ለማካሄድ በጋራ ጨረታ አውጥተው አሸናፊውን የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ጥናቱ የባቡር መስመሩ በየት እንደሚያልፍ፣ የግንባታው አዋጭነት፣ በሁለቱ አገራት ኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊ ተጽዕኖ፣ መስመሩ በመዘርጋቱ የሚያመጣው ገቢና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የአዋጭነት ጥናት ይካሄዳል።
ኢትዮጵያን ከኬንያ ላሙ ወደብ ጋር ለማገናኘት በአገራቱ አማካኝነት ፋይናንስ የማፈላለግ፣ የባቡር መስመሩን ዲዛይንና በኢትዮጵያና – በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ሰላም በጋራ ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኃላፊው ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ዕደገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን አምስት ሺ ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር በመገንባት በስምንት ኮሪደሮች የአገሪቱን የተለያዩ ክፍሎች ለማስተሳሰርና ከጎረቤት አገራት ወደቦች ጋር ለማገናኘት ዓላማ ያደረገ ቢሆንም፣ ከተያዘው እቅድ ውስጥ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ያለው በአራት ቢሊዮን፤ እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 34 ኪሎ ሜትር 475 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 690 ኪሎ ሜትር ተጠናቆ ሥራ ጀምሯል።
የአዋሽ ወልዲያ 398 ኪሎ ሜትር በአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን እንዲሁም ወልዲያ መቀሌ 220 ኪሎ ሜትር በአንድ ነጥብ ሰድስት ቢሊዮን ወጪ እየተገነባ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ