አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታኅሳስ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በታሪፍ ማሻሻያና ሌሎች ገቢዎችን በማሳደግ 13 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ::
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ባለፈው ዓመት ሰባት ነጥብ 18 ቢሊዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ ይህም በ2010 ከተሰበሰበው ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሬ አለው። በ2012 በጀት ዓመት ደግሞ ከኃይል ሽያጭ 13 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ከባለፈው ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር ተጨማሪ ስድስት ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያው በወር 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ መቶ በመቶ፣ 100 ኪሎ ዋት 75 በመቶ፣ 200 ኪሎ ዋት 25 በመቶ ይደጎማሉ። ከዚህ በላይ ያሉት ተጠቃሚዎች በታሪፍ ማሻሻያው መሰረት ይከፍላሉ። የታሪፍ ማሻሻያው በጥናት ላይ የተመሰረተና የታችኛውን የህብረተሰብ ክፍል በትክክል የሚደጉም ነው። ታሪፉ ከ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ ለተከታታይ አራት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ፣ ታስቦ የተጀመረ ነው።
ከተቋሙ ደንበኞች መካከል የመኖሪያ ቤት ደንበኞች 85 ነጥብ ስምንት በመቶ ሲሆኑ፣ ከሚቀርበው ኃይል 42 በመቶውን ይጠቀማሉ። ድጎማ ከሚደረግላቸው መካከልም መቶ በመቶ የሚደጎሙ 11 ነጥብ ሦስት በመቶ፣ 75 በመቶ የሚደጎሙ 10ነጥብ ሰባት በመቶ እንዲሁም 25 በመቶ የሚደጎሙት 33 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ሲሆኑ፤ የታሪፍ ማሻሻያው የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ድጎማ ከማይደረግላቸውም መካከል 24 በመቶውን ኃይል የሚጠቀሙት ተቋማት ሲሆኑ፣ 33 በመቶ ኃይልን የሚጠቀሙት ደግሞ ኢንዱስትሪዎች ናቸው። ከሚሸጠው ኤሌክትሪክ 60 በመቶውን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚሰጥና ለአገልግሎቱ ቀሪውን 40 በመቶ ብቻ እንደሚጠቀም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
አገልግሎቱ ሥራውን ለማከናወን የሚገዛቸው እቃዎች ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆኑት በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ናቸው ያሉት አቶ መላኩ፤ አገር ወስጥ የሚገጣጠሙትም ቢሆኑ ግብዓታቸው ከውጭ ገብተው የሚመረቱ ናቸው። ገቢውም የገበያውን ወጪ ሊሸፍን በሚያስችል ደረጃ የተቃኘ አይደለም። ከ12 ዓመት በፊት በነበረው ዋጋ ዛሬ ላይ ገቢ መሰብሰብም ፍትሐዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሽፋን አሁን ላይ 59 ነጥብ 57 በመቶ ነው። ይህ ማለትም ከአገሪቱ ዜጎች ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ያለ ኤሌክትሪክ ብርሃን ኑሯቸውን ይገፋሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ