ማረቆ ወረዳ፡- የማረቆ በርበሬ በቫይረስ በሽታ ምክንያት ከፍተኛ የምርት መቀነስ ማሳየቱን የወረዳው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ::
የጽህፈት ቤቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎች ቡድን መሪ አቶ ማስረሻ አሰፋ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ‹‹ፉዘርያም›› በተባለ ቫይረስ ምክንያት የማረቆ በርበሬ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ በአምራች ገበሬው ላይም ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
እንደ አቶ ማስረሻ ገለጻ፤ በአሁን ወቅት ምርቱ እያጋጠመው ካለው ችግር የተነሳ አርሶ አደሩ ወደ ሌላ ምርት ፊቱን አዙሯል፡፡ ይህንንም በመረዳት አዳዲስ ዝርያዎችን ለማምረት ሙከራ እየተደረገ ቢሆንም በሽታውን መቋቋም አልተቻለም፡፡
‹‹አማዶ›› የተባለ ድቃይ የበርበሬ ዝርያ የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ አርሶ አደሩ እንዲጠቀመው ግንዛቤ ቢፈጠረም፤ አንዳንዱ ዘር ገና ሙከራ ላይ እያለ መጥፋቱንም አብራርተዋል፡፡
ቡድን መሪው ቫይረሱ ለስድስት ዓመታት በምርቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱንና የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ቢረባረቡበትም መከላከል እንዳልተቻለ ጠቅሰው፤ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ረገድም ክፍተቶች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
ዝናብ በማይበዛበት ደረቅ አካባቢ ላይ በአንጻራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ቢደረግ ቫይረሱን መከላከልና ማጥፋት አለመቻሉን የገለጹት አቶ ማስረሻ፤ የበርበሬ ምርት የበልግ ወቅትን ጠብቆ የሚሠራ በመሆኑ፤ አርሶ አደሩ ወደ መኸር የአዝመራ ወቅት አዘዋውሮ እንዲሠራና በጥቂቱም ቢሆን የተሻለ ምርት እንዲያመርት ወረዳው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
ሥፍራው በበርበሬ ምርት የተሻለ ውጤት የሚገኝበት በመሆኑ የተከሰተውን ቫይረስ በዞንም ሆነ በክልል ደረጃ መፍትሔ በመፈለግ አርሶ አደሩ እንዲጠቀምበትና ከምርቱና ከገበያው እንዳይወጣም የተለያዩ ጥረቶች እንደሚደረጉ አቶ ማስረሻ አስታውቀዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በማረቆ ወረዳ የበርበሬ ምርት 860 ሄክታር የሸፈነ ሲሆን፤ ከአንድ ሄክታር 9 ኩንታል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አምና ከአንድ ሄክታር እስከ 14 ኩንታል ምርት ይገኝ እንደነበረ የወረዳው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ምርት ትመና መረጃ ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
አዲሱ ገረመው