ላለፉት ዓመታት በአራት ብሄራዊ ድርጅቶች ይመራ የነበረው ኢህአዴግ የብልጽግና ፓርቲ በሚል ስያሜ ለመዋሀድ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የሰሞኑ መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች ቀዳሚው ነው፡፡ የቀደመውን ስሙንና አደረጃጀቱን በመቀየር ወደ ውህደት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተስፋም ስጋትም እያስተናገደ ይገኛል፡፡
የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና የአጋር ድርጅቶች ሥራ አስፈጻሚ አባላት የፓርቲውን ውህደት፣ ፕሮግራምና ህገ ደንብን በሚመለከት ጥልቅ፣ የሚያግባባና የሚያቀራርብ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) ይጠቁማሉ፡፡ በአቀራረቡም ዴሞክራሲያዊ፣ ሁሉም ሃሳብ የሚንሸራሸርበት ነፃ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎች መተላለፋቸውንም ይናገራሉ፡፡ ሂደቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፓርቲው አባላት ድል መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የውይይቱ የመጀመሪያው ቀን ለየብቻ የነበሩ ፓርቲዎች ተዋህደው የብልጽግና ፓርቲ መባላቸውን ይገልጹና፤ ብልጽግናን ለኢትዮጵያ በቁስ ብቻ ሳይሆን በክብርም፣ በነፃነትም በሁለንተናዊነት እንዲያረጋግጥ መትጋት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ውሳኔው የተበታተነ ጉልበት አሰባስቦ በጋራ መቆምና መምራት እንደሚያስችልም ይጠቁማሉ፡፡
እያንዳንዱ ውሳኔ ህግን የተከተለ እንዲሆንና ውይይቱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈጸም በማድረግ የተሳካ ውጤት ማምጣት መቻሉን የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ የፌዴራል ስርዓቱ የሚያድግና በየጊዜው የሚሻሻል መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ ስህተቶቹን በሚያርም፤ ብዝሃ ቋንቋ፣ ባህልና ፍላጎቶች ያሉባትን አገር ለሁሉም እውቅና በሰጠና ባከበረ፣ ሁሉን ባሳተፈና በሚገባቸው ልክ የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብ በሚያስችል ማንነት እንዲደራጅ መወሰኑንም ያመለክታሉ፡፡ ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ፣ ሶማልኛና አፋርኛ የሥራ ቋንቋዎች እንዲሆኑ መወሰኑንም ይናገራሉ፡፡
ሂደቱ ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የጋራ አገራቸውን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት ያጠናክራል፡፡ እያንዳንዱ ህብረተሰብም በልኩ የሚሳተፍበት ሌላውን የሚያከብርበት የዴሞክራሲያዊ ዓውድ ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ውይይቱ ለኢትዮጵያ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ፣ አገሪቱን በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር የታቀደውን ለማሳካት የሚያግዝም ነው ሲሉም ያብራራሉ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና የሰብዓዊ መብት መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ፤ ኢህአዴግ ላለፉት 31 ዓመታት በግንባርነት መቀጠሉን ፤ በወቅቱ የነበረውን ገዢ ኃይል ማስወገድና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር መንቀሳቀሱንም ያስታውሳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ውህደቱ የሚመለከታቸውን ከአራት በላይ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ሊያቅፍና ሊያካትት በሚችል መልኩ መካሄድ ቢኖርበትም መዘግየቱን ይጠቁማሉ፡፡
ውህደቱ መልካም ነገሩ ይጎላል የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን በአባልነት ማሳተፉ አካታችነቱን እንደሚያሳይ ይጠቅሳሉ፡፡ ቀደም ሲል የኢህአዴግ አባል ለመሆን የአራቱ ድርጅቶች አባል መሆን አስገዳጅነቱ መቅረቱ ተገቢ መሆኑን ያነሳሉ:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ፕሮግራምና አላማውን እስከተቀበለ ድረስ የውህድ ፓርቲው አባል ለመሆን የሚችልበትን ሁኔታ ማስቀመጡ ተገቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ድርጅቱ ሲዋሃድ የውስጥ ድርጅት መመሪያ ማክበሩን፤ ከምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያና የፖለቲካ ፓርቲ ምዝገባ አዋጆች አንጻርም ውህደቱ ግንባር መሆንና ፓርቲ ማቋቋምን የሚፈቅዱ በመሆናቸው ሂደቱ የህግ ችግር እንደሌለበት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ውህደቱ በማንኛውም መንገድ የተሻለ ነገር ያመጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡ አገሪቱን በተሻለ መንገድ ለመምራት፣ አግላይ ከነበረው፣ ወዳጅና ጠላት ከተለየበትና ህብረተሰብን በመደብና በማህበራዊ መሰረት በመከፋፈል ከተፈጠሩ ስህተቶቹ ለመታረም መልካም ይሆናልም›› ይላሉ ዶክተር ሲሳይ፡፡
ዶክተር ሲሳይ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረሬና የጋምቤላ ፓርቲዎች የኢህአዴግ ፓርቲ አባል መሆን እንደማይችሉ በጉባኤ ጭምር በግልጽ ይነገራቸው እንደነበር ያስታውሱና፤ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ አባላት ብቃት ቢኖራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ወሳኝ የሆኑ የሚኒስትር ቦታዎችን የመያዝ ሁኔታው ዝቅተኛ እንደነበር፣ አሁን ይህን በማስቀረት ዜጎችን በብቃት፣ በትምህርት ዝግጅታቸው ሁሉን በእኩል የሚያስተናግድ አደረጃጀት እንደሚኖረው፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን ለመገንባትም አስተዋጽኦው ትልቅ እንደሚሆን ዶክተር ሲሳይ ያስረዳሉ፡፡
የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ያመጣል የሚሉት ዶክተር ሲሳይ፤ ቀድሞ የነበረውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ትቶ ወደካፒታሊስት መርህ እንደሚቀየር፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነትን እንደሚቀንስ፤ የግል ባለሀብትና ኢንቨስትመንት እንደሚያበረታታና ኢኮኖ ሚውን ወደተሻለ እድገት እንደሚያሳድግም ተስፋ እንደሚያሳድር ዶክተር ሲሳይ ይጠቁማሉ፡፡
የውህደቱን አደረጃጀት እንደ አሃዳዊ ስርዓት አድርጎ በመቀስቀስ የተሳሳተ መልዕክት ሲተላለፍ እንደነበር መታዘባቸውን ተናገሩት ዶክተር ሲሳይ፤ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያና ሌሎችም አገራት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች የፌዴራል ስርዓቱን የሚመሩት የተዋሀዱ ፓርቲዎች በመሆናቸው ነው ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ሲሳይ ማብራሪያ የውህደቱን ዓላማና አስፈላጊነት ዜጎች እስኪገነዘቡት ድረስ ማደናገሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ውህደቱ ለአገር መረጋጋትና ለአብሮነት ከሚሰጠው ትኩረት አንጻር መልካም ነገሩ የጎላ ነው:: ህብረተሰቡ ሂደቱን በንቃት መከታተል፣ መጠየቅና መመርመር ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን)ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፤ የኢህአዴግ ድርጅት መተዳዳሪያ ደንብ መቀየሩ ለኢትዮጵያ ችግር እንዳልሆነ ፤ ከህገ መንግሥት፣ ከመመሪያ፣ ከአዋጅና ከሌሎች የአገሪቱ ህጎች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
ዘላለም ግዛው