• ከ210 ቢሊየን ብር በላይ ለኃይል አቅርቦት ወጪ በማድረግ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሠርቷል፤
• ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ለቤት ልማት ፕሮግራም ወጪ አድርጓል፤
አዲስ አበባ፡- በዛሬው ዕለት በስምንተኛው የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሐ ግብሩ ለአምስት የመኖሪያ ቤት ባለዕድለኞች ቁልፍ እንደሚያስረክብ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ፡፡ ከ210 ቢሊየን ብር በላይ ለኃይል አቅርቦት እንዲሁም ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ለቤት ልማት ፕሮግራም ወጪ በማድረግ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሲሠራ መቆየቱንም ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ የአብስራ ከበደ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ባንኩ ላለፉት ስምንት ዓመታት የቁጠባ ባህልን የሚያሳድጉ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ የቁጠባ ባህል እንዲዳብር በማድረግም ከ 10 ዓመት በፊት 53 ቢሊየን ብር የነበረውን አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በአሁኑ ወቅት 542 ቢሊየን ብር አድርሶታል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ለማደጉ ከባንኩ የሠራተኞች እንቅስቃሴ ባሻገር የቁጠባ ባህል ላይ የተሠራው ሥራ የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በዘንድሮ ስምንተኛው የይቆጥቡ ይሸለሙ መርሐግብር አምስት የመኖሪያ አፓርታማዎችን ለደንበኞቹ አቅርቦ ዕጣው መውጣቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ፤ በዛሬው ዕለት በተለምዶ ኃይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚኖረው መርሐ ግብር ላይ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቤት ለወጣላቸው ዕድለኞች የቁልፍ ርክክብ ሥነስርዓቱ ይካሄዳል፡፡ አምስቱ አፓርታማዎችም ባለዕድለኞች በድጋሚ ዕጣ ወጥቶላቸው በሚደርሳቸው ወለል ላይ የቤታቸውን ቁልፍ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ይህም በቀጣይ ሌሎች ዜጎች ለመቆጠብ እንዲነሳሱ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡
ባንኩ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እንኳ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ከ210 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአገሪቱ የኃይል አቅርቦት ላይ የራሱን አሻራ በማሳረፍ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መሥራቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
መንግሥት ትኩረት በሚሰጥበት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የወጪ ንግዱ ላይ በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝም ሲያበረክት የቆየው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቤት ልማት ፕሮግራም ላይ ከ76 ቢሊየን ብር በላይ ፤ እንዲሁም ባለፈው ዓመት በተደረገው ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት በመደገፍ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 77 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በጉዞው አጠቃላይ ሀብቱ 712 ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡ 40 ሺህ የሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞችና ከአንድ ሺህ 500 በላይ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በእነዚህ ቅርንጫፎቹ ከ20 በላይ የባንክ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ዜጋ የባንክ አገልግሎትን እንደማይጠቀም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
ፍዮሪ ተወልደ