አዲስ አበባ፡- የተቋማት የፍትሐዊ ተደራሽነት አለመሆን እና የስልጠና ጥራትና አግባብነት ጉድለት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፉ ተግዳሮቶች እየሆኑ መምጣታቸው ተጠቆመ፡፡ ችግሩን ለመፍታት የግል ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ችግሮች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ትናንት ሲካሄድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር አብዲዋሳ አብዱላሂ፣ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተከፈቱ ቢሆንም የተቋማት ፍትሐዊ ተደራሽ አለመሆንና የስልጠና ጥራትና አግባብነት ጉድለት ተግዳሮቶች እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ ችግሮቹን እያባባሰ የመጣው ደግሞ የግሉ ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ላይ በበቂ ሁኔታ ተሳትፎ ባለማድረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሕብረተሰቡ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርት ያለው አመለካከት ዝቅተኛ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው፤ ወደ ስልጠናው የሚገቡት ሰልጣኞችና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ አመራሮች ብቁ አለመሆን እንዲሁም የተግባር መስጫ መሳሪያዎች አለመሟላት ዘርፉ ለውጥ እንዳያመጣ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በቀጣይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ለመከታተል ተማሪዎች በምርጫ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ስለቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አስፈላጊነት ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ ላይ በስፋት የሚሳተፍበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡
በምክክር መድረኩ ‹‹የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ከየት ወዴት›› በሚል ርዕስ የመወያያ ፅሑፍ ያቀረቡት አቶ ኃይለ ሚካኤል አስራት በበኩላቸው፤ የተቋማት ፍትሐዊ ተደራሽ አለመሆን እና የስልጠና ጥራትና አግባነት ጉድለት የመጣው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ባለመሥራታቸውና የስልጠና ጥራትና አግባብነት ጉድለትን ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ አመራሮች፣ ሰልጣኞችና የሰልጣኝ ወላጆች እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ችግሩን ለማቃለል ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ አለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲገመገም የበጀት አጠቃቀሙ በጥልቀት መታየት እንዳለበትም አቶ ኃይለሚካኤል አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 10/2012
መርድ ክፍሉ