በሀገራችን ባለው አሠራር ሕፃናት ቅድመ መደበኛ ትምህርት መከታተል የሚጀምሩት በአራት ዓመታቸው እንደሆነ ይታወቃል፤መደበኛ ትምህርት እንዲጀመሩ የሚጠበቀው ደግሞ በሰባት ዓመታቸው ነው፡፡ ይህ በከተሞች እየተሠራበት ሲሆን፣ በገጠር እና በአንዳንድ ከተሞች ግን የቅድመ መደበኛ ትምህርት ጉዳይ በቄስ ትምህርት ቤት እና ቁርአን ትምሀርት ቤቶች የሚሸፈን እንደ መሆኑ የአጸደ ሕፃናት ትምህርት አለ የሚባል አይደለም፡፡
አንዳንድ ሕፃናት ግን ከሰባት ዓመታቸው በፊት ትምህርት እንዲጀምሩ ሲደረግ ይስተዋላል፡፡ ትምሀርት የጀመሩት በአምስት ዓመታቸው መሆኑን የሚገልጹ ያጋጥማሉ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች 12ኛ ክፍልን መቼ ጨርሰው መቼ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደሚይዙ መገመት አይከብድም፡፡ በአምስት ዓመታቸው አንደኛ ክፍል ቢገቡና ብርቱ ሆነው አስራ ሁለተኛ ክፍልን በሰዓቱ ቢያጠናቅቁ ከ21 ዓመታቸው በፊት የመጀመሪያ ዲግሪ ለመያዝ አይችሉም፡፡ በ7 ዓመታቸው የሚገቡት ደግሞ መቼ ሊጨርሱ እንደሚችሉ እናስብ፡፡ በእኛ ሀገር አንዳንዶች ትምህርት ቤት ሊገቡ በሚችሉበት ዕድሜ የመጀመሪያ ዲግሪ የያዙ ታዳጊዎች ያጋጥማሉ፡፡
ኤንዲቲ የተሰኘው ድረ ገጽ በቅርቡ ይዞት የወጣ ዘገባ እንዳመለከተው የአምስተርዳም ነዋሪው የዘጠኝ ዓመት ሕፃን የመጀመሪያ ዲግሪውን በቅርቡ እንደሚይዝ ይጠበቃል። በዚህም በዓለም የመጀመሪያ ዲግሪ ያየዘ በሕፃንነቱ መያዝ የቻለ ብቸኛው ሕፃንም ለመባል በቅቷል።፡
በኤይንሆቭን ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ሲከታተል የቆየው ለውረንት ሲሞንስ የተባለው ይህ ሕፃን የመጀመሪያ ዲግሪውን የሚይዘው በኤሌክትሪካል ምህንድስና ነው፡፡ ሕፃኑ የመጀመሪያ ዲግሪውን በሚቀጥለው ወር እንዳጠናቀቀም ፣ከሦስት ወራት በኋላ ሦስተኛ ዲግሪውን ለመያዝ ትምህርት እንደሚጀምርም ተናግሯል፡፡
እናቱ ሊዲያ የልጁ አያቶችና መምህራን ልዩ ተሰጥኦ እንዳለው ሁሌም ይናገሩ እንደነበር ስትገልጽ፣ አባቱ አሌክስንደር ሲሞንስ በበኩሉ ልጁ በእርግጥም መረጃ በመያዝ በኩል ማንም አይደርስበትም ሲል ገልጿል፡፡
ሎውረንት ገና ምኑ ተይዞ ይላል፡፡ ለዘ ቴሌግራፍ በሰጠው አስተያየትም ወደ ካሊፎርኒያ በመሄድ ትምህርቱን ለመቀጠል ይፈልጋል፤አባቱ ግን እንግሊዝ ሄዶ ቢማርለት እንደሚመርጥ አስታውቋል፡፡ የ37 ዓመቱ የጥርስ ሀኪም የሆነው አባቱ ‹‹ኦክስፎርድና ካምብሪጅ በአንግሊዝ ዋና ዋናዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከእነዚህ ዩኑቨርሲቲዎች በአንዱ ገብቶ ቢማር ምርጫው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ላውረንት ሲሞንስ ለሲኤንኤን በሰጠው አስተያየት በቀጣይም ማጥናት የሚፈልገው ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መሆኑን ጠቅሶ፣ በተወሰነ ደረጃ የህክምና ትምህርት መማርም ይፈልጋል፡፡
ቤተሰቦቹ በሕፃንነቱና በእውቀቱ መካከል የሆነ ሚዛናዊ ነገር እንደሚፈልጉ ሎረንት ገልጾ፣ እሱ ደግሞ ለትምህርቱ ከሚሰጠው ትኩረት በተጓዳኝ የተለየዩ ጨዋታዎችን መጫወት፣ ከጓደኞቹ ጋር መሆን እንደሚወድ ይናገራል፡፡ በኢንስታግራም በኩል ከ11 ሺህ በላይ ተከታዮች አንዳሉት ተናግሮ፣ በዚህም አማካይነት የህይወትን የተለያዩ ጎኖች እንደሚመለከት ያብራራል፡፡
እስከ አሁን ባለው መረጃ መሰረት በዓለም በልጅነቱ የመጀመሪያ ዲግሪ በመያዝ የሚታወቀው ሚካኤል ኬርኒይ የተባለ ታዳጊ ሲሆን ፣ዲግሪውን የያዘውም በአስር ዓመቱ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 9/ 2012 ዓ.ም
ዘካርያስ