በአውሮፓዊቷ ሀገር ስፔን ባለፈው ሚያዝያ በተካሄደው ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የሚመራው ገዥው «የስፔን የሠራተኞች ሶሻሊስት ፓርቲ» ያልተጠበቀ አብላጫ ድምፅ ቢያገኝም፣ ብቻውን መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ድምፅ ማግኘት ግን አልሆነለትም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝም ከተቀናቀኝ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ጥምር መንግሥት ለመመስረት ቢደራደሩም፣ መንግሥት መመስረት አልሆነላቸውም፡፡ ይህ በመሆኑም ዳግም ምርጫ ማካሄድ የግድ ሆኖበታል፤ ስፔናውያንም ከቀናት በፊት ቀጣዩን መሪያቸውን ለመምረጥ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
ከሰባት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ምርጫ አስቀድሞ ያሸንፋል የሚል ሰፊ ግምት የተሰጠው በፔድሮ ሳንቼዝ የሚመራው ገዥው ፓርቲ፣ እንደተገመተውም አብዛኛውን የፓርላማ መቀመጫ መያዝ ችሏል፡፡ በዚህም ፓርቲው ከፓርላማው 350 መቀመጫዎች 120 የሚሆነውን ይዟል፡፡ ባለፈው ምርጫ 66 ድምፅ ያገኘው ወግ አጥባቂው «ፒፕልስ ፓርቲ» ፒፒ 88 መቀመጫዎችን ይዟል፡፡ በምርጫው አስደናቂ በሆነ መልኩ ያልተጠበቀ ድምፅ ማግኘት የቻለው ቀኝ አክራሪ ፓርቲው «ቮክስ» ሲሆን፣ ባለፈው ምርጫ ካአገኘው እጥፍ 52 ድምፅ ማግኘት ችሏል፡፡
ገዥው የሶሻሊስት ፓርቲ በዚህ ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ አብላጫ ድምፅ ቢያገኝም፣ ብቻውን መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ጉልበት ግን አላገኘም፡፡ በአገሪቱ ሕግ መንግሥት ለመመስረት አንድ ፓርቲ ማግኘት የሚኖርበትን ዝቅተኛ የሚባለውን 176 መቀመጫ ማሟላት አልቻለም፡፡
የካሊፎርኒያ ቤንትሊ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ጥናት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቦኒ ፊልድ ይህን ክስተት አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ክስተቱ የአገሪቱ ፖለቲካ ውስብስብ እንዲሆን ማድረጉን ሲጠቅሱ፣በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሀተታ ያሰፈረው የስካይ ኒውስ ዘገባ በበኩሉ፣ መሪዋን መምረጥ ያልሆነላት ስፔን ቅጥ አንባሩ በጠፋበት የፖለቲካ ሁኔታ ምናልባትም ለወራት መዝለቅ ግድ ሊላት እንደሚችል አመልክቷል፡፡
ከምርጫው ውጤት ይፋ መሆን በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝም፣ ሁሉም ፓርቲዎች የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ምስቅልቅል ፈር ለማስያዝ ኃላፊነትና አርቆ አሳቢነት በተሞላበት መልኩ እንዲንቀሳቀሱም ጥሪ ከማቅረብ ባሻገር ፓርቲያቸውም የተረጋጋ መንግሥት ለማዋቀር በሚያደርገው ጥረት ለስፔናዊያን ምቹ የፖለቲካ ምህዋር ለመፍጠር ቅድሚያ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
በሁለት ምርጫዎች አዲስ መንግሥት ለመመስረት ያልሆነላቸው የ47 ዓመቱ የማድሪድ ተወላጅና የሕግ ባለሙያ ፔድሮ ሳንቼዝ ፣ እንደ አሁንም ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ ያቀርባሉ ተብለው ቢጠበቅም፣ እርሳቸው ግን ‹‹ይሆኑኛል››ከሚሏቸው ሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመደራደር መንግሥት መመስረትን ምርጫቸው አድርገዋል፡፡
በዚህ ምርጫ ገዥው ፓርቲ እና ፒፒ ፓርቲ ያገኙት ድመፅ ሲደመር 207 እንደመሆኑ ጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚያስችል አቅም ቢኖረውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በምርጫው አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ፓብሎ ኤግሊሲያስ ከሚመራው ዩኒዳስ ፖደሞስ ከተሰኘው ፓርቲ ጋር መስማማትንም መርጠዋል። በቅርቡ ከፓርቲው ጋር ስምምነት ባደረጉበት ወቅትም ‹‹በአሁኑ ወቅት ስፔን የተረጋጋና ጠንካራ መንግሥት ያስፈልጋታል፣ስምምነቱም ለአራት ዓመት ይዘልቃል››ብለዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ካለፈው ምርጫ ማግስት አንስቶ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ለወራት ሲደራደሩ ቢቆዩም፣ከመወራረፍና ከመወነጃጀል ባለፈ አንዳች ስምምነት ላይ ሳይችሉ ቆይተዋል፡፡ አሁን ግን ያለፈውን ታሪክና ቁርሾ ረስተው ሲሳሳቁ፣ ሲጨባበጡ እና ሲተቃቀፉ ተስተውለዋል፡፡
ይህ ያልተጠበቀ ፈጣን የፓርቲዎቹ የአጋርነት ስምምነት ስፔንን ከቀድሞው አምባገነን መሪ ጀኔራል ፍራንኮ ከተፋታችባቸውና ዴሞክራሲን ከተዋወቀችባቸው ከ1970 ዎቹ ዓመታት በኋላ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥምር መንግሥት ጋር አስተዋውቋታል፡፡
ይሁንና አሁንም ቢሆን የስፔን መንግሥት በቅጡ አልተለየም፡፡ በጥምረት አገር እናስተዳድራለን ያሉት የሁለቱ ፓርቲዎች ድምፅ ድምር ውጤት 155 ቢሆንም፣አሁንም ይህ ብቻውን አገር ለማስተዳደር በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም በሌሎች ትናንሽ ፓርቲዎች ድምፅ መደገፍ ግድ ይለዋል፡፡
የፓርቲዎቹ መብዛት ደግሞ በመንግሥታዊ የአስተዳደር ስልጣን በተለይ በካቢኔው ውስጥ ‹‹ማን፣ ምን ዓይነት የአመራር ቦታ ላይ ይቀመጥ›› በሚለው ላይ መወሰኑ እንዲሁም በፓርቲዎቹ መካከል ያለው የአቋም ልዩነት ቀጣዩን የአገሪቱ ፖለቲካ ውስብስብ እንደሚያደርጉት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ያካፈሉ የፖለቲካ ተንታኞች ተስማምተውበታል፡፡
ይሁንና ከአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አንዱ የሆነው ላሴክታ ቴሌቪዚን የግራ ዘመሙ ፓርቲ መሪ ፓብሎ ኤግሊሲያስ ከባለፈው ምርጫ ማግስት አንስቶ ለጥምር መንግሥት ምስረታ ድርድር እንዲደረግ ሲጠይቅ መቆየቱን ጠቅሶ፣የተከለከሉትን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት እንደሚረከቡ ለማወቅ ስለመቻሉ አስመልክቷል፡፡
የወግ አጥባቂው ፒፒ ፓርቲ መሪ ፓብሎ ካስዶ በአሁኑ ወቅት ስፔን የሚያስፈልጋት መንግሥት በዚህ መልክ የተዋቀረ አይደለም፣ በሚል ስምምነቱን ክፉኛ በመንቀፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ጥሪ ስለማቅረባቸው አልጀዚራ አስነብቧል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ መሪዋን ለመምረጥ ድምፅ ብትሰጥም አንድና ሁነኛ የሚያስተዳድራትን ፓርቲ ለማግኘት ያልቻለችው ስፔን፣ በታሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥምር መንግሥት ለመተዳደር በጉዞ ላይ ስለመሆኗ ግን በርካቶች ተስማምተውበታል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 9/ 2012 ዓ.ም
ታምራት ተስፋዬ