ሀዋሳ፡- በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ምክ ንያቶች የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከሦስት እስከ 5 ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ። ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅም አንድ ቢሊዮን ብር መመደቡ ታውቋል።
የማዘጋጃ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በ2010 እና በ2011 ለማጠናቀቅ ግብ ተቀምጦላቸው የነበሩ የመንገድ እና የመፋሰሻ ቦይዎች ግንባታ በዲዛይን በወሰን ማስከበር ችግሮች ምክንያት ሳይጠናቀቁ ቆይተዋል።
በቅርቡ በከተማዋ ከንቲባ በአቶ ጥራቱ በየነ መሪነት ፕሮጀክቶቹ በተጓተቱባቸው አካባቢዎች በተደረገው የመስክ እይታና ግምገማ ከነዋሪዎች ቅሬታ ተነስቶ እንደነበር የሚያወሱት አቶ ፍቅሩ፤ ከህብረተሰቡ የተነሳውን ቅሬታ መሰረት በማድረግ ማዘጋጃ ቤቱ የመንገዶቹን ግንባታ በፍጥነት እንዲያጠናቅቅ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል። አቶ ፍቅሩ፤ የተቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግም ማዘጋጃ ቤቱ ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም ሦስቱን መንገዶች በአፋጣኝ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
እንደ አቶ ፍቅሩ ማብራሪያ፤ በፍጥነት እየተከናወኑ ካሉ መንገዶች መካከል በዲዛይንና በድንበር ማስከበር ችግር ምክንያት ተቋርጠው የነበሩት ከሀይሌ ሪዞርት ወደአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ የሚወስደው መንገድ፤ ከዋርካ ወደዌስት ላንድ የሚወስደው መንገድ እና አቶቴ 2 በመባል የሚታወቀው ከሀዋሳ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን ወደአዲሱ ስታዲየም የሚወስደው መንገድ እና የጎርፍ ማስወገጃ ቦዮች ተጠቃሽ ናቸው።
የጎርፍ ማስወገጃ ቦዮቹ ለቀጣይ 20 ዓመታት ሀዋሳ ከተማን ከጎርፍ አደጋ ነጻ ማድረግ የሚያስችሉ ናቸውም ብለዋል። ከዋርካ ወደዌስት ላንድ ከሚወስደው መንገድ ጋር የሚሰራው ስድስት ሜትር ጥልቀትና ሦስት ሜትር ስፋት ያለው የጎርፍ ማስወገጃ ቦይ የከተማዋን የጎርፍ ችግር 50 በመቶ እንደሚያቃልል አብራርተዋል።
ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ዳንኤል እንዳለ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ያለመጠናቀቅ ችግር መኖሩን አንስቷል። አሁን ግንባታቸው መቀጠሉ እንዳስደሰተውም ተናግሯል። ግንባታውን በአፋጣኝ ለማጠና ቀቅም ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የይርጋለም ኮንስትራክሽን የሀዋሳ ፕሮጀክት ማናጀሯ ወይዘሮ ሰላማዊት ሸጉም አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል። ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ አሁንም አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ግን አንስተዋል። እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ እስከ አራት ወር ባለው ጊዜ ለመጨረስ ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የኮሙዩኒኬ ሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መልካሙ ተፈራ በበኩላቸው፤ አስተዳደሩ ለስራ ተቋራጩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል። ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዘው ያሉ ችግሮችም እየተቀረፉ መሆናቸውን አንስተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
መላኩ ኤሮሴ