አዲስ አበባ (ኢዜአ)፡- ምክንያታዊ በመሆን ነገሮችን መመርመር አለመቻላችን የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ አድርጎናል ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ መምህር ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው እንደገለጹት፤ ግጭቶችን ለመከላከልና ለመፍታት የሃሳብ ልዩነቶች ላይ ውይይት ማድረግና ሁሉም ሰው ስለሰላም ያገባኛል የሚል አመለካከት መያዝ አለበት። በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስልጣን ጥም ያለባቸው ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የተሳሳቱ ወሬዎች ሲናፈሱ ምክንያታዊ በመሆን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።
የአገሪቱ የትምህርት ጥራት እየወደቀ መምጣቱን የተናገሩት ፕሮፌሰር ዳንኤል፤ ትውልዱ ምክንያታዊና አመዛዛኝ እንዳይሆን ማድረጉ አሁን ላይ እየታዩ ላሉ ግጭቶች መነሻ መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎችን የሚቀርጹ መምህራን ብቃት በሚፈለገው ልክ አለመሆንና ከዚህ መውጣት አለመቻሉ ተማሪዎች በግጭቶች እንዲሳተፉና ከአገርና ከቀጠና እንዲሁም አህጉር ይልቅ ጠበው ስለጎሳቸው ብቻ እንዲያስቡ ማድረጉንም አስረድተዋል። ትምህርት ቤቶች ራስን አሳልፎ መስጠትን የሚሻው የልብ ትምህርት ላይ አለማተኮራቸው እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መሆኑ አንዱ የሌላውን ቁስል እንዳይረዳና መተሳሰብ መቀነሱን አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም ልዩነት የሚፈታው በውይይትና በመነጋገር እንደነበር ፕሮፌሰር ዳንኤል አስታውሰው፤ ዩኒቨርሲቲዎች ሀገርን የሚለውጡ የምርምርና አዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የብጥብጥና ግጭት ማዕከል ሆነው እንዲታሰቡ ማድረጉን ተናግረዋል። እሴቶቻችን መሸርሸራቸውና ምክንያታዊነትን ማጣታችንም ለፖለቲከኞች ቁማር መጫወቻ አድርጎናል ይላሉ።
የአማራ ብሔራዊ ክልል ምሁራን መማክርት ፕሬዚዳንት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ሀኪምና መምህር በበኩላቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት ተማሪዎች መወያየትን መልመድ እንዳለባቸውና መምህራንም የው ይይት መድረኮችን ማመቻቸት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲዎች ከአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ሰዎች በአንድ ላይ የሚሰባሰቡባቸው መሆኑ ለግጭት ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሳይሰፉ ለመቆጣጠር ተቋማቱ ከፀጥታ አካላትና ከኀብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንዲሰራም ዶክተር ገበያው ጠይቀዋል። እንደእርሳቸው፤ ሀገሪቷን ለመጉዳት አቅደው የሚሰሩ የውጭ ኃይሎች መኖራቸውንና እነሱንም እየደገፉ ያሉ የውስጥ ኃይሎች መኖራቸውን ልብ በማለት የህዝቡን ጥያቄ በማወያየትና በመለየት መፍትሄ መስጠት ይገባል። የፖለቲካ ቁማርተኞች በሚጭሩት ግጭት ተጎጂ ደሃው ኀብረተሰብ በመሆኑ ህዝቡ ዝምታውን ሰብሮ ያገባኛል ማለት አለበት።
በግል ሙያ የተሰማሩት አቶ ካሌብ ተስፋዬ፤ በግጭት የፈረሱ አገሮች የችግራቸው መፍቻ ያደረጉት ውይይት መሆኑን ጠቁመው አገር ሳይፈርስ በፊት ውይይትን ማስቀደም ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል። መንግሥትም በመዋቅሩ ውስጥ ሆነው ግጭት የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን መፈተሽ እንዳለበትና የህግ የበላይነትን ለማስከበርም ከህዝቡ ጋር ተባብሮ መስራት እንዳለበት ገልፀዋል። የተሳሳቱ አረዳዶችን ለማጥራትና የአንዱን ቁስል አንዱ እንዲረዳ ለማድረግም መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል። <<ኀብረተሰቡ አገሪቱን እስካሁን አፅንቶ ያቆያትን የመተሳሰብና የመከባበር እንዲሁም ሌሎች እሴቶች ለወጣቶች ማስተማር መቻል አለበት>> ብለዋል።
ምሁራኑም የውይይት ባህል እንዲያድግና የህዝብ ጥያቄዎች መፍትሄ እንዲያገኙ መድረክ መፍጠርና ሃሳብ በማፍለቅ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012