አዲስ አበባ፡- ብዝሃነትን እና እኩልነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የኢህአዴግ ውህደት እንደ ጥሩ እድል የሚቆጠር በመሆኑ ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ምሁራን እና የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደገለጹት፤ የኢህአዴግ ውህደት እንደ ተዓምር ባይታይም በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመቀነስ ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። የፓርቲው ውህደት ለእያንዳንዱ ግለሰብም እኩል መብት በመስጠት በኢትዮጵያ ውስጥ ፌዴራሊዝምን እና ብዝሃነትን በማስተናገድ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የኢህአዴግ የውህደት ሀሳቡ እንደ ሀገር ጠቃሚ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰር መረራ፤ ከዚህ አኳያ መሬት ላይ ወርዶ ተግባራዊ እስኪደረግ ድረስ እንደተፎካካሪ ፓርቲ እስከመጨረሻው ውጤቱን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። እቅዱንም ገዥው ፓርቲ ተግባራዊ ካደረገው እንደ ሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተደርጎ ይቆጠራል። ‹‹እኛም ልክ እንደማንኛውም ዜጋ መንግስት በጉዳዩ ላይ የገባውን ቃል ካልጠበቀ ልንሞግተው ዝግጁ ነን በመሆኑም ይህን ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ለውጡን ለማስቀጠል መዋሃዱን ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል።›› ብለዋል።
የኢህአዴግ የፖለቲካ እና ሲቪክ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩ ላቸው እንደገለጹት፤ የኢህአዴግ ውህ ደት ወደጠራ የፌዴራሊዝም መንገድ በመውሰድ እኩልነትን ከማስፈን ባለፈ የቆዩ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ጭምር ለመመለስ እድል ይሰጣል።. በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ የነበሩ የቆዩ አሰራሮችን በመቀየር አካታች እና በዕኩልነት ላይ የተመሰረተ ውክልናን በማስፈን ለተሻለ ውጤት የሚያበቃ መሆኑ ታምኖበታል።
እንደ አቶ ፍቃዱ ከሆነ፤ የኢህአዴግ ውህደት እና የፌዴራል ስርዓት በአንድ ላይ መሄድ የማይችሉ ጉዳዮች አድርጎ መመልከት አይገባም። አንድ ውህድ ፓርቲ መመስረቱ ህገመንግስቱ እና የፌዴራል ስርዓቱን ያስቀይራል ማለት አይደለም። ህገመንግስቱን ወይንም የፌዴራል ስርዓቱን ለመቀየር ቢያስፈልግ እንኳን የህዝቡን ተሳትፎ እና ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ይሆናል።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር መስከረም አበራ በበኩላቸው፤ ውህደቱ በግለሰቦች መካከል የቋንቋ እና የባህል ልዩነት ቢኖር እንኳን ተጠራጣሪነትን በማስቀረት ረገድ ህብረት ለመፍጠር ያስችላል። ይህም የኢህአዴግን ችግር በእራሱ መንገድ ለመፍታት ትልቅ እድል ነው። ውህደቱም እያንዳንዱ ግለሰብ በቀጥታ እና በእኩልነት በሚያገባው ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ስለሚያደርግ ያለፉ ስህተቶችን ለማረም በር ይከፍታል።
እንደ መምህር መስከረም ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም ኢህአዴግ የብሔር ፖለቲካ ላይ በተመሰረተ አካሄድ አጋሮቹን ባገለለ እና ወሳኝ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አግላይ አካሄድን በመምረጡ በሀገሪቱ የሚገኙ በርካታ አጋር ክልሎች ከፖለቲካ ምህዳሩ ርቀው ቆይተዋል። ከለውጡ በኋላ ይህን ለማስተካከል ውህደት እንደሚያስፈልግ መታመኑ ችግሮቹን ለመቅረፍ ዋነኛ አማራጭ ነው። ነገር ግን ይህን ባለመረዳት ውህደቱን የሚቃወም አካል ካለ የእራሱ መጥፎ አጀንዳ ያለው የስልጣን ጥቅም የያዘው መሆኑን ህዝቡ ሊረዳ ይገባል። እድሉም ለአጋር ድርጅቶች እና ለሌላውም አመቺ የዴሞክራሲ መድረክ የሚፈጥር በመሆኑ ውህደቱን መደገፍ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር