– 160 ሚሊዮን አንበጣ በየቀኑ ወደ ኢትዮጵያ እየገባ ነው
– በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰብል አውዳሚ ግሪሳ ወፍ ተከስቷል
አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢ ዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እና ሰብል አውዳሚ የግሪሳ ወፎች ስጋት እስከ ታህሳስ ወር ሊቀጥል እንደሚችል ተገለፀ።በየቀኑም 160 ሚሊዮን የአንበጣ መንጋ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብድዮስ ሰላቶ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የበረሃ አንበጣ በየአራት ወይንም አምስት ዓመቱ እንደሚከሰት ይታወቃል። ምስራቅ አፍሪካ ደግሞ የአንበጣ ወረራና መራቢያ የሚከሰትበት ስፍራ ነው። ኤዥያ እና ሰሜን አፍሪካ ይህ ክስተት የሚስተዋልባቸው ሲሆን ኢትዮጵያም አንዷ ተጠቂ ናት። ኢትዮጵያ የአየር ጸባይ ለእፅዋት፣ እንስሳትና ነፍሳት ለመራባት ምቹ የሆነ አየር ጸባይ ስላላት የአንበጣ መንጋ መዳራሻ ሆናለች፤ እርጥበቱና የአየር ሙቀቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም ሱማሌ ክልል፣ ምስራቅ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ምስራቅ አማራ፣ ድሬዳዋ ዙሪያና ደቡባዊ ትግራይ ከሰኔ ጀምሮ የአንበጣ መንጋ መከሰቱ ይታወቃል። የአንበጣ መንጋው ወደ ሀገሪቱ ከመግባቱ በፊት የተጠናከረ ዓለም አቀፍ መረጃ ነበር። ከዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ ማዕከልም ለአገራት መረጃ ይሰጣል። በመሆኑም አንበ ጣው ከመግባቱ በፊት በመታወቁ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በማድረግ ለመከላከል ሙከራ ተደርጓል። ይሁንና በተከታታይ ከሶማሌ ላንድ እና የመን ከፍተኛ የሆነ የአንበጣ መንጋ ይገባ ስለነበር አንዳንድ አካባቢዎች ከመልክዓ ምድር አቀማመጥ አስቸጋሪነትና የፀጥታ ሁኔታ መደፍረስ አኳያ መከላከሉን አስቸጋሪ አድርጎታል።
እንደ አቶ ዘብድዮስ ከሆነ፤ አነስተኛ መንጋ ከአንድ እስከ አምስት ስኩየር ኪሎ ሜትር በአንዴ የሚሸፍን ሲሆን ከፍተኛ መንጋ ደግሞ ከ10 እስከ 40 ስኩየር ኪሎ ሜትር ወይንም አንድ ወረዳ ያክል የሚሸፍን ነው። በመሆኑም መከላከሉን አስቸጋሪ አድርጎታል።
አንበጣው የምግብ እጥረት ሲገጥመውና ለመራባት ምቹ ቦታ ካላገኘ ወዲያውኑ የነበ ረበትን ቦታ ይለቃል። አንበጦች በአንቴናቸው ወቅታዊ የአየር ሁኔታን የሚያውቁ በመሆ ናቸው ምቹ ስፍራ በመምረጥ በቀላሉ መስፋፋት ይችላሉ። በተጨማሪም በሱማሌና አፋር ክልል የህዝብ አሰፋፈር የተበታተነ ስለሆነ ከህብረተሰቡ ወዲውያኑ መረጃ ማግኘት አልተቻለም። በመሆኑም በየሸለቆ የሚራቡትን በቅፅበት ማቆም አዳጋች ሆኗል። በዚህም ላይ ደግሞ አንበጣ በአንዴ በከፍተኛ ደረጃ የሚራባ በመሆኑም ቁጥጥሩን ፈታኝ አድርጎታል።
አንድ መንጋ እስከ 80 ሚሊዮን አንበጣ የሚይዝ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህም ሆኖ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ከፍተኛ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁ መዋል። እስካሁን በሱማሌ በኩል ሁለት መንጋ እየገባ ነው። አገር ውስጥም የአንበጣ መንጋ በተለያዩ አካባቢዎች ይገኛል፤ መከላከሉም ቀጥሏል ብለዋል። አንድ መንጋ እስከ 80 ሚሊዮን አንበጣ እንደሚይዝ የሚገመት ሲሆን፤ በየቀኑ ሁለት ተጨማሪ መንጋ ሊገባ እንደሚችል ይገመታል። በመሆኑም ከሱማሌ ላንድ ወሰን ላይ ባለሙያዎች ቦታ ይዘው አንበጣው ወደ መሃል አገር እንዳይገባ በአውሮፕላን ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች በተለይም ኦጋዴን አካባቢ ያሉ ሦስት ዞኖች አንበጣው የሚያመራበት ሥፍራ እንደሚሆን ይገመታል። የመንንና የሳውዲ አረቢያ ባህር ዳርቻ አካባቢም የአንበጣ መንጋ የሚራባበት ስለሆነ አሁንም ጥንቃቄው ይቀጥላል ብለዋል። አቶ ዘብድዮስ እንዳሉት፤ መንጋውን በአንድ ቅጽበትም ማጥፋት ከባድ ነው። በዚህም ሁኔታ እስከ ታህሳስ ድረስ የአንበጣ መንጋው በስፋት ወደ ሀገራችን ሊገባ እንደሚችል ጠቁመዋል። ከኢትዮጵያ ውጭ በቀይ ባህር ዳርቻዎችም አንበጣው የሚራባበት ሥፍራ ሲሆን ይህን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሥራ ይከናወናል ነው ያሉት።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ከአንበጣ መንጋ በተጨማሪም ግሪሳ ወፍ በየዓመቱ ይከሰታል። በተለይም ከሰኔ ጀምሮ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ ኦሮሚያ ክልልና አማራ ክልል ይከሰታል። በዚያው ልክ መከላከል እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም የግሪሳ ወፎች በብዛት የታዩበት አካባቢ መኖሩን ጠቁመዋል። በተለይም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ቀወት ወረዳ 400ሺ፤ ሌላ ቦታ ደግሞ 500ሺ መከላከል ተደርጓል። ጅሌ ጥሙጋ አካባቢ ደግሞ 500ሺ ግሪሳ ወፍ ያለ ሲሆን በማደሪያቸው አካባቢ የኬሚካል ርጭት ይካሄዳል።
ግሪሳ ወፎች መነሻው በተለይም ታንዛኒያ ሲሆን፤ ከዚያም ኬኒያ ኤርትራ፣ የመንና ሱማሌ እየተንቀሳቀሱ ጉዳት ያደርሳሉ። የግሪሳ ወፍ በ33 የአፍሪካ ሀገራት በመንቀሳቀስ ጉዳት በማድረስ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ የአንበጣ መንጋውም ሆነ የግሪሳ ወፍ ሰብል ሲደርቅ ምቹ ስለማይሆንለት አካባቢውን ለቆ ይወጣል። ሆኖም ግሪሳ ወፍ እስከ ህዳር 20ዎቹ ድረስ ይቆያል ብለዋል።
ምንም እንኳን የአንበጣው መንጋና ግሪሳ ወፍ የሚያደርሱት ጉዳት ቢኖርም በአጠቃላይ የአገሪቱ ምርት ላይ የከፋ ጉዳት ያደርሳል የሚል ግምት የለንም ብለዋል። ሆኖም የአንበጣ መንጋው ከሱማሌ ላንድ ወደ ሀገራችን አሁንም እየገባ ስለሆነ ህብረተሰቡ ሰብሎችን በፍጥነት እንዲሰበስብና የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳቦችን እንዲተገብር አሳስበዋል። በአንበጣ መንጋውና በግሪሳ ወፍ አማካኝነት በሰብል ምርት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ የግብርና ሚኒስቴር ጥናት እያካሄደ መሆኑን አቶ ዘብድዮስ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ በበኩላቸው፤ እስካሁን በአምስት ዞኖች 73ሺ የሚጠጋ ሄክታር መሬት ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቶ 63ሺ500 ሄክታር መሬት ላይ የመከላከል ሥራ ተከናውኗል። በተለይም በሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች የአንበጣ መንጋው መከሠቱን አስረድተዋል። በአጠቃላይ 2ሺ501 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ ውሏል።
እንደ ኃለፊው ገለፃ፤ የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ እስካሁን 400ሺ ግሪሳ ወፍ ውስጥ 99 ከመቶ መግደል ተች ሏል። ጅሌ ጥሙጋ አካባቢ ደግሞ ግሪሳ ወፍ መኖሩንና እርምጃ እንደሚወሰድ አስገን ዝበዋል። የአንበጣ መንጋው ሆነ የግሪሳ ወፍ ክስተት አሳሳቢ መሆኑንና በክልሉ ዓመታዊ ምርት ላይም ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል።
የአንበጣ መንጋው መከሰቱ ከተሰማበት ጊዜ አኳያ በቂ የመከላከል ሥራ አልተደረገም ያሉት አቶ ተስፋሁን፤ የግንዛቤ እጥረት፣ ከክልሎች ጋር በቅርበት አለመነጋገርና ፈጣን እርምጃ አለመውሰድ ችግሩን የከፋ አድርጎታል። መከላከል ሥራ እየተካሄደ ቢሆንም አሁንም ሥጋት መኖሩን አብራርተዋል። በተለይም የአንበጣ መንጋ አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች በመኖሩ በእንጭጩ ካልተገታ አደጋው የከፋ እንደሚሆን አስገንዝበዋል። በተያያዘም ወቅ ቱን ያልጠበቀ ዝናብም ምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎችን ሊሰበስብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ህዳር 6/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር